አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሆነው ተሰየሙ

አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሆነው በሕዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተሾሙ። አምባሳደር ታዬ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት ሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ የመክፈቻ ስብሰባ ላይ ነው።

አምባሳደር ታዬ ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጥር 30/2016 ዓ.ም. ጀምሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል። ታዬ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት የሥራ ዘመናቸው በዚህ ዓመት የተጠናቀቀውን አንጋፋዋን ዲፕሎማት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ተክተው ነው።

የፓርላማው አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የዕጩ ፕሬዝዳንቱን የትምህርት ደረጃ እና ሥራ ልምድ ለሁለቱ ምክር ቤቶች አባላቶች በንባብ አሰምተዋል።

በሕገ መንግሥቱ መሠረት ለፕሬዝዳንትነት ዕጩ የማቅረብ ሥልጣን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። በዚህ መሠረት “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት በዝግ ባካሄደው ስብሰባ የወሰነው ውሳኔ” መሆኑን ገልጸዋል።

የቀረቡት ዕጩ በሕዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ሁለት ሦስተኛ ድመጽ ካገኙ ፕሬዝዳንት እንደሚሆኑ ሕገ መንግሥቱ ላይ ሰፍሯል። በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ከተገኙት 487 አባላት መካከል የአምባሳደር ታዬ ሹመት በአምስት ድምጸ ተዓቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።

ላለፉት ስድስት ዓመታት የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሆነው ያገለገሉት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ነበር።

ተሰናባቿ ፕሬዝዳንት በስብሰባ አዳራሽ ተገኝተው አምስተኛው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሆነው ለተሰየሙት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ ሕገ መንግሥቱን አስረክበዋል።

የቀድሞዋ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የሥልጣን ዘመናቸው በዚህ ዓመት የሚጠናቀቅ የነበረ ሲሆን፣ ከቀናት በፊት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ያስተላለፉት መልዕክት መነጋገሪ ሆኖ ቆይቶ ነበር።

ቢቢሲ ያናገራቸው የቀድሞዋ ፕሬዝዳንት የቅርብ ሰዎች እንዳሉት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ባሉበት ሁኔታ ደስተኛ አለመሆናቸውን እና የሥልጣን ዘመናቸው መጠናቀቅን ሲጠባበቁ እንደነበር ገልጸዋል።

ሕገ መንግሥቱ ለፕሬዝዳንቱ ከሰጠው ሥልጣን መካከል የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶችን ዓመታዊ የጋራ ስብሰባ መክፈት ቀዳሚው ነው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቃቸውን ሕጎች እና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በነጋሪት ጋዜጣ ማወጅም የፕሬዝዳንቱ ሥልጣን ነው። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ እና አገሪቱን በውጭ አገራት የሚወክሉ አምባሳደሮችና እና ሌሎች መልዕክተኞችን መሾም እንዲሁም የውጭ አገር አምባሳደሮች እና የልዩ መልዕክተኞችን የሹመት ደብዳቤ የመቀበል ሥልጣን አላቸው።

ፕሬዝዳንቱ በሕገ መንግሥት የተሰጣቸው ሌላኛው ሥልጣን በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት “በሕግ በተወሰነው መሠረት” ከፍተኛ የውትድርና ማዕረጎችን መስጠጥ እና “በሕግ መሠረት” ኒሻኖችን እና ሽልማቶችን መስጠት ነው።

ሕገ መንግሥቱ አክሎም “[ፕሬዝዳንቱ] በሕግ መሠረት ይቅርታ ያደርጋል” ይላል።

አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ ማን ናቸው

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ደባርቅ ውስጥ የተወለዱት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ የረጅም ጊዜ ልምድ ካላቸው ሙያተኛ ዲፕሎማቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱ መሆናቸው ይነገራል።

ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና በዲፕሎማቲክ መስክ አገራቸውን ያገለገሉት አምባሳደር ታዬ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በተለያዩ አገራት እንዲሁም በመንግሥታቱ ድርጅት በሙያቸው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

አምባሳደር ታዬ ከአገሪቱ ዋነኛ የትምህርት ተቋም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፣ ከእንግሊዙ ላንካስተር ዩኒቨርስቲ ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና በስትራተጂክ ጥናቶች አግኝተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ሆነው በመሥራት ላይ የቆዩት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ ከፍተኛ ኃላፊነቶች ላይ የሠሩት ዲፕሎማቱ ከአሜሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተርነት አስከ ምክትል ሚኒስትርነት ድረስ አገልግለዋል።

ከዚያ ባሻገር ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ፣ ለሁለት ዓመት ደግሞ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት ለዓመታት በዘለቀ ውዝግብ ውስጥ ባለችው ግብፅ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ሠርተዋል።

ለረጅም ዓመታት በዲፕሎማትነት ባገለገሉባት አሜሪካ ውስጥ ከተባበሩት መንግሥታት በሻገር በሎስ አልጀለስ ዋና ቆንስላ፣ በዋሽንግተን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር እንዲሁም በስዊዲን ስቶክሆልም ውስጥ ደግሞ ቆንስላ ሆነው አገለልግለዋል።

በተጨማሪም በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ አገራቸውን በመወከል የተሳተፉ የካበተ ልምድ ያዳበሩ ጉምቱ ዲፕሎማት ናቸው።

አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በተለይም ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር ውዝግብ በገባችበት ጊዜ እንዲሁም በትግራዩ ጦርነት ወቅት ጉዳዩ በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ሲቀርብ ከፊት ቀድመው የታዩ ዲፕሎማት ናቸው።

አምባሳደር ታዬ ለዓመታት በዋሽንግተን በኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ በሎስ አንጀለስ በኢትዮጵያ ቆንስላ እና በኒው ዮርክ በተባበሩት መንግሥታት አገራቸውን በመወከል ከቆዩባት አሜሪካ የወጡት ባለፈው ዓመት ወደ አዲስ አበባ ሲዘዋወሩ ነበር።

አምባሳደር ታዬ ከጥር 10/2015 ዓ.ም. ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ሚኒስትር ሆነው የነበሩ ሲሆን፣ በፕሬዝዳንትነት ከመሰየማቸው በፊት ለስምንት ወራት ያህል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሠርተዋል።