የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች በሩሲያ የታገዱ ንብረቶች ላይ ሲወስኑ ዜሌንስኪ ከባድ ማስጠንቀቂያ ሰጡ

የፎቶው ባለመብት, JOHN THYS/AFP
ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች የዩክሬን ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶችን ለመደገፍ እገዳ የተጣለበት በብዙ ቢሊዮን ዩሮ የሚገመት የሩሲያ ገንዘብ ብድር ላይ በአስቸኳይ እንዲስማሙ ጥሪ አቀረቡ።
ዩክሬን ያላት የገንዘብ ክምችት እየተመናመነ ሲሆን በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ተጨማሪ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚዋ የማይገባ ከሆነ "የድሮን ምርት መቀነስ ይኖርባታል" ሲሉ ዜሌንስኪ ተናግረዋል።
በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ ያለው አብዛኛው የሩሲያ 245 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሀብት በቤልጂየም በሚገኘው ዩሮክሊር ድርጅት የተያዘ ነው።
እስካሁን ድረስ ቤልጂየም እና ሌሎች አንዳንድ አባል አገራት ገንዘቡን እንደ "የካሳ ብድር" መጠቀምን እንደሚቃወሙ ተናግረዋል።
ሩሲያ የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች ገንዘቧን እንዳይጠቀሙ አስጠንቅቃለች፤ ነገር ግን የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ "አጋጣሚውን መጠቀም አለብን" ብለዋል።
የብራስልስ ጉባኤ በጦርነቱ ወሳኝ ወቅት ላይ የተከሰተ ሲሆን ሩሲያ ገንዘቧን ለማስመለስ በዩሮክሊር ላይ በሞስኮ ፍርድ ቤት ክስ መስርታለች።
ዜሌንስኪ ዩክሬን በሚቀጥለው ዓመት በእርግጠኝነት ከ45-50 ቢሊዮን [ዩሮ] የበጀት ጉድለት እንደሚገጥማት ተናግረዋል።
የአውሮፓ ኮሚሽን ኃላፊ ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን ደግሞ "መፍትሄ ላይ ሳንደርስ ጉባኤውን ለቅቀን አንወጣም" ሲሉ ቃል ገብተዋል።
አንድ የአውሮፓ መንግሥት ባለሥልጣን ስምምነት ላይ እንደሚመደረስ "ጥንቃቄ የታከለበት ብሩህ ተስፋ እንደሚታያቸው፣ ነገር ግን የተለጠጠ ተስፋ እንደማያደርጉ" ገልጸዋል።
ሁሉም ዓይኖች የቤልጂየም ጠቅላይ ሚኒስትር ባርት ደ ዌቨር ላይ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሙስ ዕለት ለቤልጂየም ፓርላማ እንደተናገሩት ሁሉም ነገር በቀሪው የአውሮፓ ኅብረት አባላት ተቀባይነት ካገኘ እና ከተስማማን "ከሌሎቹ አውሮፓውያን ጋር አብረን ወደ ጥልቁ እንዘልላለን እና መቅዘፊያው ይሸከመናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል የሚካሄደውን ጦርነቱን ለማስቆም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለስምምነት መቃረባቸውን ተናግረዋል።
የአሜሪካ እና የሩሲያ ባለሥልጣናት ቅዳሜና እሁድ በማያሚ የሰላም ዕቅድ ላይ ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ እንደሚገናኙ የዋይት ሐውስ ባለስልጣን ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
የክሬምሊን ልዑክ ኪሪል ዲሚትሪቭ ከትራምፕ ልዑካን ስቲቭ ዊትኮፍ እና ጃሬድ ኩሽነር ጋር በማያሚ እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል።
የዩክሬን ባለሥልጣናትም ወደ አሜሪካ እያመሩ ነው። በብራስልስ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ኪየቭ ጦርነቱ ከቀጠለ ጦሯን ለመደገፍ ወይም ሙሉ በሙሉ ለመልሶ ግንባታ ለማዋል ገንዘቡን እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።
"የሞራል ጉዳይ ነው፣ ፍትሃዊ ነው እና በብዙ ባለሙያዎች የተረጋገጠ ነው።"
ሩሲያ ለአዲሱ የሰላም ሀሳብ እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም።
ነገር ግን ክሬምሊን ዩክሬን በአሜሪካ የሚደገፍ የአውሮፓ ኅብረት ጦር ለማቋቋም የምታደርገው ዕቅድ ተቀባይነት እንደሌለው አፅንዖት ሰጥታ ተናግራለች።
በቤልጂየሙ ዩሮክሊር ባንክ የሚገኘው 185 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የሩሲያ ሃብት ላይ ዘላቂ እገዳ ተጥሏል።
የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች ይሄንን ሃብት ለዩክሬን ለማበደር ውይይት እያደረጉ ነው።
የአውሮፓ ኅብረት እገዳ የጣለበትን ሃብት ለዩክሬን እርዳታ ለማዋል ይፈልጋል። ሆኖም ግን ቤልጂየም ገንዘቡን ጥቅም ላይ ማዋልን በተመለከተ በግልጽ ድጋፍ አላሳየችም።
የገንዘብ ክምችቷ እየተመናመነ ያለው ዩክሬን በቀጣይ ሁለት ዓመታት 119 ቢሊዮን ዶላር ትፈልጋለች። የአውሮፓ አገራት ሁለት ሦስተኛውን ለመሸፈን አቅደዋል።
ሩሲያ የአውሮፓ ኅብረትን በምዝበራ ወንጅላለች። በብራሰልስ እየተካሄደ ያለው የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች ውይይት ላይ የሚተላለፈው ውሳኔ እየተጠበቀ ነው።
እገዳ የተጣለበት የሩሲያን ገንዘብ ለዩክሬን በማበደር ላይ ስጋት ያላት ቤልጂየም ብቻ አይደለችም። የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ ለሕዝብ አንደራሴዎች ስምምነቱ "ሕጋዊ መሠረቱ ጠንካራ ከሆነ" እንደሚደግፉ ተናግረዋል።
ሕጋዊ መሠረቱ ጠንካራ ካልሆነ ግን ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ለሩሲያ እውነተኛ ድልን በእጇ እንድትጨብጥ ማድረግ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ማልታ፣ ቡልጋሪያ እና ቼክ ሪፐብሊክ በአወዛጋቢው ምክረሃሳብ ሙሉ በሙሉ እንደላመኑበት ተናግረዋል።
ምክረሃሳቡ የአውሮፓ መንግሥታትን ተቀባይነት አግኝቶ ገንዘቡ ለዩክሬን የሚሰጥ ከሆነ ፍርድ ቤት ቤልጂየም ገንዘቡን ለሩሲያ እንድትሰጥ ሊወስን ይችላል።
አንዳንድ አገራት ቢሊዮን ዩሮዎችን በዋስትና መልክ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ያሳወቁ ቢሆንም ቤልጂየም ግን ይህንን ዋስትና የሚሰጡ አገራት ቁጥር እንዲበዙ ትፈልጋለች።















