በኦሮሚያ ኢሉ አባ ቦራ እናቱን ጨምሮ 4 ሰዎች በእሳት ተቃጥለው እንዲሞቱ ያደረገው በእስራት ተቀጣ

በኦሮሚያ ክልል ኢሉ አባ ቦራ ዞን ዳሪሙ ተብሎ በሚጠራ ወረዳ አንድ ግለሰብ ወላጅ እናቱን ጨምሮ 4 የቤተሰብ አባላትን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ካደረገ በኋላ በጽኑ እስራት ተቀጣ።

በዳሪሙ ወረዳ ቤና 3ኛ ተብላ በምትጠራ መንደር አሕመድ ኡስማን የተባለው ወንጀለኛ ወላጅ እናቱን፣ እህቱን እና የ8 ወር ጨቅላ የሆኑ መንትያ የእህቱን ልጆች በእሳት ተቃጥለው ሕይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጉ ተገልጿል።

የኢሉ አባ ቦራ ዞን ዐቃቤ ሕግ የተለያዩ ወንጀሎች የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ጉታ ዱጉማ ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ ግለሰቡ በአራት የገዛ የቤተሰብ አባላቱ ላይ አሰቃቂ ወንጀሉን የፈጸመው ሰኔ 29/2016 ዓ.ም. ነው።

“ወንጀሉ በተፈጸመበት ዕለት ግለሰቡ ከእናቱ የጠየቀውን የገንዘብ ብድር ባለማግኘቱ የቂም በቀል ይዞ እስከ እኩለ ለሊት ድረስ ተደብቆ ቆየ” ይላሉ።

የዞኑ የዐቃቤ ሕግ ባልደረባ እንደሚሉት ከሆነ ከለሊቱ 7 ሰዓት ሲሆን፤ አሕመድ ኡስማን የተባለው ግለሰብ ወደ ወላጅ እናቱ ቤት በመመለስ አራቱ የቤተሰብ አባላት ያሉበትን የሳር ክዳን ቤት ላይ እሳት አያይዟል።

“ወደ እናቱ ቤት ተመልሶ አራቱ ሰዎች ከውስጥ እያሉ ከውጪ በሩን ዘግቶት እሳት አያያዘ” በማለት የወንጀል ድርጊቱ የተፈጸመበትን ሁኔታ አቶ ጉታ አስረድተዋል።

በዚህም ምክንያት የፍርደኛው እናት፣ እህት እና የ8 ወር ዕድሜ ያላቸው የእህቱ መንትያ ልጆች ሕይወታቸው ማለፉን ጨምረው ተናግረዋል።

የወንጀል ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ ተደርጎ የክስ ሂደቱ በኢሉ አባ ቦራ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲታይ መቆየቱን ተናግረዋል።

በፍርድ ሂቱ ላይ ተከሳሹ ከዚህ ቀደም የወንጀል ክስ እንደሌለበት፣ አካል ጉዳተኛ መሆኑን እና ባለቤቱ ነብሰ ጡር መሆኗን በመግለጽ የቅጣት ማቅለያ እንዲደረግለት ጠይቋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ተከሳሹ ይህን አሰቃቂ ወንጀል በገዛ የቤተሰብ አባላቱ ላይ የፈጸመው በበቀል ተነሳስቶ እና አስቦበት በመሆኑ ከባድ ቅጣት እንዲተላለፍበት ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኝ ክርክሩን ሰምቶ ነሐሴ 28/2016 ዓ.ም. በዋለው ችሎት አሕመድ ኡስማን በ25 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

ይሁን እንጂ አቶ ጉታ በበቀል ተነሳስቶ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ጨቅላ ሕጻናትን ጨምሮ 4 ሰዎችን በገደለው ሰው ላይ የተላለፈው ቅጣት አነስተኛ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“እንደ ዐቃቤ ሕግ የተላለፈው ቅጣት በቂ ነው ብለን አናምንም። ፍርድ ቤቱ በምን ላይ ተመርኩዞ ይህን ውሳኔ እንደሰጠ ለማወቅ ግልባጭ እንዲሰጠን ጠይቀናል። በሕጉ መሠረት በቀጣይ ይግባኝ የምንጠይቅ ይሆናል” ሲሉ የዞኑ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ ባልደረባ ለቢቢሲ ተናግረዋል።