ጥምቀት በመላው ዓለም እንዴት ይከበራል?

ዛሬ ጥር 11/2017 ዓ. ም. የጥምቀት በዓል በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።

የጥምቀት በዓል ከዋዜማው ጥር 10 ጀምሮ ጥር 11 የሚከበር ሲሆን ጥር 12 ደግሞ የቃና ዘገሊላ በዓል እንዲሁ በድምቀት ይከበራል።

ከጥምቀት በዓል ዕለት ቀደም ብሎ ባለው ቀን በሚከበረው የከተራ በዓል ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት ታቦታት በመውጣት የጥምቀት በዓል ወደሚከበርባቸው ቦታ በሕዝብ ታጅበው ይጓዛሉ።

አዲስ አበባ የሚገኘው ጃን ሜዳ እና ጎንደር ጥምቀት በተለየ ሁኔታ የሚከበርባቸው ሥፍራዎች ሲሆኑ ከምዕመናን በተጨማሪ የተለያዩ ሀገራት ቱሪስቶች በዓሉን ለመታደም ይመጣሉ።

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ጥምቀት በተለያየ ሥነ ሥርዓት በተለያዩ አገራትም ይከበራል።

የገና በዓልን ታኅሣሥ 29 የሚያከብሩ አገራት ጥምቀትን ጥር 12 ያከብራሉ። ጥር 6 በዓሉ የሚከበርባቸው አገራትም አሉ። ቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ ስጦታም ይለዋወጣል።

በዓሉ 'ስሪ ኪንግስ ደይ' ተብሎም ይከበራል።

ሰባ ሰገል በኮከብ ተመርተው ኢየሱስ ክርስቶስን የጎበኙበትን በማስታወስ ነው በዓሉ የሚከበረው።

በእንግሊዘኛው Epiphany የሚለው ቃል ግሪክ ሲሆን 'መታየት' ማለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም የታየበትን ምክንያት በማድረግ ነው ስያሜው የተሰጠው።

በሩሲያ እና በሌሎች የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት አብዛኛውን ጊዜ ጥምቀት የሚከበርበት ወቅት የብርድ ወራት በመሆኑ ምዕመናን በጣም ቀዝቃዛ በሆነ ቅዱስ ውሀ ውስጥ በመግባት ነው በዓሉን የሚያከብሩት።

የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በኦርቶዶክስ እምነት ባሕል መሠረት በየዓመቱ በቀዝቃዛ ውሀ በመጠመቅ የጥምቀት በዓልን ያከብራሉ።

በስፔን ጥምቀት እንደ ገና በድምቀት ነው የሚከበረው። El Dia de los Reyes በሚል ስያሜ ይጠራል።

በዋዜማው ልጆች ለሰባ ሰገል የሚሆን መጠጥ ያስቀምጣሉ። በበዓሉ ርችት እየተተኮሰ የአደባባይ ትርዒት ይታያል።

በቼክ ሪፐብሊክ በዓሉ የሚከበረው እጅግ ቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ በመዋኘት ነው። ዋናው የሚካሄደው በፕራግ በሚገኘው ቭላታ ወንዝ ነው።

እንደ ሰባ ሰገል በመልበስ ግመል የሚጋልቡ ትዕይንት ያሳያሉ።

በሜክሲኮ ጥምቀት ሲከበር ጣፋጭ ዳቦ የሆነው ሮስካ ዴ ሬይስ ይበላል።

በዳቦው ውስጥ አነስተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅርጽ ይቀመጣል። ዳቦው ሲቆረስ ቅርጹ የደረሰው ሰው እንደ ዕድለኛ ይቆጠራል።

ቅርጹ የደረሰው ሰው ምግብ አብስሎ ቤተሰብ የመጋበዝ ግዴታም ይጣልበታል።

በስዊዘርላንድ ባህል Dreikönigskuchen የተባለ ዳቦ ተጋግሮ ጥር 6 ይበላል።

በግሪጎሪያን ቀን አቆጣጠር ገና ከተከበረ ከ12 ቀናት በኋላ በዓሉ ስለሚመጣ Twelfth Night ተብሎ ይጠራል።

የገና ዛፍ የሰቀሉ ሰዎች የሚያወርዱትም በዚህ ቀን ነው።

የኢትዮጵያ ጥምቀት ክብረ በዓል በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ሆኖ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መመዝገቡ ይታወቃል።

ጥምቀት በኢትዮጵያ ውስጥ በድምቀት ከሚከበርባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል አዲስ አበባና ጎንደር ይገኙበታል።