ተመራማሪዎች ከሰው ዐይነ ምድር የአውሮፕላን ነዳጅ ፈጠሩ

በእንግሊዝ ተመራማሪዎች ከዐይነ ምድር የአውሮፕላን ነዳጅ (ኬሮሲን) ፈጠሩ።

ፋየርፍላይ ግሪን የተባለው ተቋም ሥራ አስፈጻሚ ጃምስ ሃይጌት ለቢቢሲ እንተናገሩት “በርካሽ የሚገኝ ኬሮሲንን የሚተካ ነገር ስንፈልግ ነበር። ዐይነ ምድርን አግኝተናል፤ ዐይነ ምድር በርካሽና በስፋት ይገኛል” ብለዋል።

ይህ የሰው ልጆች ዐይነ ምድር ረዥም የቤተ ሙከራ ሂደቶች ካለፈ በኋላ ነው አውሮፕላን ለማብረር የሚችል ነዳጅ (ኬሮሲን) ሊተካ የሚችል አቅም የሚፈጥረው።

የአቪየሽን ኩባንያው እንደሚለው ከአውሮፕላን ነዳጅ ጋር ሲነጻጸር ዐይነ መድር በ90% ያነሰ የካርበን ልቀት ነው ያለው።

ይህ ምርምር ላለፉት 20 ዓመታት ሲካሄድ ነበር። አዲሱ ከዐይነ ምድር የሚመረተው ነዳጅ ልክ እንደ ኬሮሲን ዐይነት ባህሪ ያለው ቢሆንም ነገር ግን ከፎሲል ነጻ ነው።

ዐይነ ምድሩ በላቦራቶሪ ከአውሮፕላን ነዳጅ ጋር ተቀይጦ የሚዘጋጅ ቢሆንም በዚህ አዲሱ ዘዴ ግን የአካባቢ ብክለትን የማያስከትል፣ ለዓለም ሙቀት መጨመር አስተዋጽኦ የማያደርግ የአውሮፕላን ነዳጅ ይመረታል ተብሏል።

በዓለም ላይ 2 እጅ የሚሆነው የካርቦን ልቀት የሚከሰተው ከአውሮፕላን በረራዎች ነው።

ይህ አሐዝ ትንሽ ቢመስልም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በፍጥነት እየጨመረ መሆኑ ለምድራችን ሙቀት መጨመር ስጋት ሆኖ ቆይቷል።

በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አውሮፕላኖችን ለመሥራት ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም፣ ጥረቱ ፍሬ እስኪያፈራ ረዥም ዓመታትን መውሰዱ አይቀርም።

ለዚህም ነው ነዳጅን የማይፈልግ ኬሮሲን ለመፍጠር ሙከራዎች በስፋት የቀጠሉት።

ግሪን ፊዩልስ ኩባንያ ዐይነ መድርን እንደ አማራጭ ኬሮሲን ከመሞከሩ በፊት የተለያዩ ተረፈ ምርቶችን፣ ተረፈ ምግቦችን እና ዝቃጭ አገልግሎት ላይ የዋሉ ዘይቶችን ሲሞክር ነበር።

በመጨረሻ የሰው ልጆች ዐይነ ምድር የአውሮፕላን ነዳጅን ለመተካት የተሻለ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል።

በዚህ ሂደት ውስጥ መጀመርያ ልክ እንደ ነዳጅ ሁሉ ድፍድፍ የሆነ ነገር ይፈጠራል፣ ከዚያ ወፍራም ጥቁር ፈሳሽ ሆኖ ከኬሚካሎች ጋ ተቀላቅሎ ነው ወደ ነዳጅነት የሚቀየረው።

ይህ ግኝት ገና በላቦራቶሪ ደረጃ ያለ ሲሆን ወደ ተግባር ለመሄድ በጣም ረዥም ዓመታት ሊወስድ ይችላል።

እያንዳንዱ የሰው ልጅ በዓመት በአማካይ 5 ሊትር የአውሮፕላን ነዳጅ መሥሪያ የሚሆን ዐይነ ምድር ያስወግዳል።

ይህ ግን አቪየሽን ከሚፈልገው እጅግ ያነሰ ነው።

ለምሳሌ ከለንዶን ተነስቶ ኒውዮርክ የሚሄድ አውሮፕላን የ10ሺህ ሰዎችን የአንድ ዓመት ዐይነ ምድር ክምችትን ይሻል።

ሌላ 10ሺህ ሰዎች ዐይነ ምድር ደግሞ ከኒው ዮርክ ወደ ለንደን ያስፈልጋል ማለት ነው።

የዩኬ ጠቅላላ የተወገደ ዐይነ ምድር ቢሰበሰብ የአገሪቱን 5 ከመቶ የአውሮፕላን ነዳጅ ፍላጎትን እንኳ መሸፈን አይችልም።

የአካባቢ ተቆርቋሪዎች የሰው ልጆች በአውሮፕላን መጓዛቸውን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ እንዳለባቸው ያሳስባሉ።

ምናልባት ከሰው ዐይነ ምድር የሚገኝ ኬሮሲን የሰው ልጅ እስካለ ድረስ የሚቀጥል መሆኑ ተመራጭ ያደርገው ይሆናል።

የዓለም አቀፍ የኢነርጂ ኤጀንሲ በቀጣይነት የሚገኝ ከካርበን ልቀት ነጻ የሆነ አስተማማኝ ኃይል ያስፈልጋል ይላል።

ይህን ለማሳካት በየፊናው ጥናትና ምርምሩ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ሰር ሪቻርድ በራንሰን በቅርቡ ከለንደን ወደ ኒውዮርክ የበረሩትም ይህን ለማስገንዘብ ነው። የበረሩበት አውሮፕላን እንደ ነዳጅ የተጠቀመው ከዘይት ዝቃጭ እና ከበቆሎ ዝቃጭ በተሰናዳ ነዳጅ ነበር።

ይሁንና ይህንን የኃይል አማራጭ አስተማማኝና ዘላቂ አማራጭ ለማድረግ ሰፊ ሥራ እንደሚቀር ተመራማሪው ይናገራሉ።