በአዲስ አበባ የነበረው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ በረራዎችን አስተጓጎለ

ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 04/2014 ዓ.ም. ጠዋት በአዲስ አበባ የነበረው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አውሮፕላኖች እንዳያርፉ እና እንዳይነሱ በማድረግ በረራ እያስተጓጎለ ነው።

አሁናዊ የበረራ መረጃዎችን የሚያጋሩት ፍላይት ራዳር 24 እና ፍላይት አዌር ድረ-ገጾች አውሮፕላኖች ቦሌ አየር ማረፊያ ማረፍ ተስኗቸው በአዲስ አበባ ሰማይ ላይ እየተሽከረከሩ አሳይተዋል።

አየር መንገዱም በይፋዊ የቴሌግራም ገጹ፤ በቦሌ አየር ማረፊያ በተፈጠረው ጭጋጋማ አየር ሁኔታ ሳቢያ ከአዲስ አበባ በሚነሱና በሚያርፉ በረራዎች ላይ መዘግየት መፈጠሩን ገልጿል።

ከቻይናዋ ጓዋንዡ ተነስቶ አዲስ አበባ ማረፍ የነበረበት የበረራ ቁጥር ኢቲ607 አውሮፕላን አዲስ አበባ ደርሶ ቦሌ አየር ማረፊያ ማረፍ ተስኖት በአዲስ አበባ ዙሪያ ሰማይ ላይ እየተሸከረከረ ነው።

በተመሳሳይ መነሻውን ቶሮንቶ ካናዳ ያደረገው ኢቲ607 ኤርባስ ኤ350 አውሮፕላን በተመሳሳይ የአየር ሁኔታው እስኪሻሻል ድረስ በአዲስ አበባ ሰማይ ላይ እየተሸከረከረ ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪ ከቤይሩት ሌባኖስ እና ከዩናትድ አረብ ኤሜሬትስ ዱባይ የተነስተው ወደ አዲስ አበባ ሲበሩ የነበሩ አውሮፕላኖች የበራራ አቅጣጫቸውን ለመቀየር ተገደዋል።

በጭጋጋማው የአየር ንብረት ለማረፍ ከተሳናቸው አውሮፕላኖች በተጨማሪ፤ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሊነሱ የነበሩ በርካታ በረራዎች በመጥፎው አየር ሁኔታ በራራቸው ዘግይቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጭጋጋማው አየር ንብረት ምክንያት ምን ያህል በረራዎች እንደተስተጓጎሉበት ያለው ነገር የለም።

በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያዎች በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ በራራዎች ሲስተጓጎሉ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በተመሳሳይ ከአንድ ዓመት በፊት በአየር ማረፊያ የነበረው ጭጋጋማ አየር አውሮፕላኖች በክልል ከተሞች እና ጎረቤት አገራት አየር ማረፊያዎች እንዲያርፉ አስገድዶ ነበር።

በአዲስ አበባ ዛሬ ጠዋት ከባድ ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ መኖሩን በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየገለጹ ፎቶ ግራፎችንም እኣጋሩ ነው።