ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአውሮፕላን ቲኬት ዋጋ “ያለጥርጥር” የበለጠ መጨመሩ የማይቀር ነው ተባለ
የአየር ጉዞ ቲኬቶች “ያለጥርጥር” ዋጋቸው መጨመሩ አይቀርም ሲሉ የዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር ዳይሬክተር ጄኔራል አሳሰቡ።
የቀድሞ የብሪቲሽ ኤየርዌይስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ዊሊ ዎልሽ፤ ኮቪድ ካስከተላቸው ጫናዎች መላቀቅ ጀምሮ የነበረው ዘርፉ፣ በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እንዲሁም የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት የአውሮፕላን ቲኬት ዋጋ እንዲጨመር ያደርጋል ብለዋል።
ዎልሽ ተጓዦች የአውሮፕላን ቲኬት ዋጋ እንደሚጨምር ከግምት በማስገባት ለጭማሪው ዝግጁ መሆን አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል።
“ለተጓዦች የአውሮፕላን ቲኬት ዋጋ የበለጠ ውድ እንደሚሆን ምንም ጥርጣር የለውም” ብለዋል። ለአየር ጉዞ ዋጋ መጨመር ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ የነዳጅ ዋጋ መጨመሩ መሆኑን አመልክተዋል።
“ከፍተኛው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ፤ የቲኬት ዋጋ ጭማሪ ላይ ይንጸባረቃል” ብለዋል።
ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምጣሄ ሃብታቸው እያገገመ በነበሩ አገራት ላይ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እያሳየ ይገኛል። የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ደግሞ የበለጠ ነዳጅ እንዲወደድ ምክንያት ሆኗል።
ምዕራባውያን በሩሲያን ነዳጅ ላይ እቀባ እየጣሉ ነው። አሜሪካ ሙሉ በሙሉ ከሩሲያ ነዳጅ ማስገባት እንደምታቆም ይፋ አድርጋለች።
የአውሮፓ ኅብረት ደግሞ በእአአ 2022 ማጠናቀቂያ ላይ ከሩሲያ ወደ ኅብረቱ አገራት የሚገባው የነዳጅ መጠንን ዜሮ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
የሩሲያ ነዳጅ ከገበያ እንዲወጣ መደረጉ በሌሎች ነዳጅ አምራቾች በኩል ለገበያ የሚቀርበውን የነዳጅ ዋጋ ከፍ እንዲል ያደርጋል።
ዎልሽ እንደሚሉት ከሆነ የአየር መንገዶች ከፍተኛው ወጪ ነዳጅ ነው። “ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ተጓዦች ለአየር ቲኬታቸው ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉ ማስገደዱ የሚቀር አይደለም” ሲሉ የዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር ዳይሬክተር ጄኔራል ዊሊ ዎልሽ ተናግረዋል።