ናፖሊ በቲክቶክ በአጥቂው ቪክተር ኦሲምሄን ላይ አሹፏል በሚል ሊከሰስ ነው

የጣልያኑ ናፖሊ ቡድን በአጥቂው ቪክተር ኦሲምሄን ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አሹፏል በማለት የተጫዋቹ ወኪል በቡድኑ ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ዛተ።

እሁድ ዕለት ናፖሊ ከቦሎኛ ጋር በነበረው ግጥሚያ አጥቂው ቪክተር ኦሲምሄን የፍጹም ቅጣት ምት የሳተበትን ቪዲዮ በሚያሾፍ ሁኔታ “ፍጹም ቅጣት ምት ስጡኝ” ከሚል ከድምጽ ጋር በማቀናበር በቡድኑ የቲክቶክ አካውንት ላይ አጋርቶ ነበር።

ነገር ግን ቡድኑ ኋላ ላይ ቪዲዮውን ከይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ እንዲሰረዝ ተደርጓል።

ይህንንም ተከትሎ የተጫዋቹ ወኪል ሮቤርቶ ካሌንዳ በኤክስ (ትዊተር) ላይ “ሕጋዊ እርምጃ የመውሰድ መብት እና የቪክተርን መብት ለማስጠበቅ የትኛውንም አይነት ጠቃሚ መንገድ እንከተላለን” ብሏል።

ወኪሉ ጨምሮም በናፖሊ የቲክቶክ ይፋዊ ገጽ ላይ የታየው ነገር ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በማመልከት “ቪክተር ላይ የሚያሾፈው ቪዲዮ ለሕዝብ ከቀረበ በኋላ ዘግይቶ ተሰርዟል። ይህም በተጫዋቹ ላይ ቀደም ሲል በመገናና ብዙኃን እና በሐሰተኛ ዜና ምክንያት የደረሰበትን ጉዳት የበለጠ የሚያባብስ ነው” ሲል ተቃውሟል።

ቪክተር ኦሲምሄን እሁድ ዕለት በነበረው ከቦሎኛ ጋር ካለግብ በተለያዩበት ጨዋታ ላይ በ86ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በወጣበት ጊዜ ከአሠልጣኙን ሩዲ ጋርሺያ ጋር ሲነጋገር ታይቶ ነበር።

ናይጄሪያዊው ዓለም አቀፍ ተጫዋች ቪክተር ኦሲምሄን ናፖሊን የተቀላቀለው ለክለቡ ከፍተኛ በተባለው 81.3 ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ ከሦስት ዓመታት በፊት ነበር።

ቪክተር ኦሲምሄን ባለፈው ዓመት ለናፖሊ በ32 የሊግ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 26 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ቡድኑ ከ33 ዓመታት በኋላ የጣሊያን ከፍተኛ ሊግ ሴሪ አ ዋንጫን እንዲያነሳ ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጉ ይነገራል።

የ24 ዓመቱ ናይጄሪያዊ አጥቂ ባለፈው የዝውውር ወቅት ከእንግሊዞቹ ክለቦች ቼልሲ እና ማንችስተር ጋር በተያያዘ ስሙ በስፋት ሲነሳ ነበረ።

ነገር ግን ከናፖሊ ጋር ያለው ስምምነት ሳይቋረጥ እዚያው ጣልያን ውስጥ እየተጫወተ ሲሆን፣ አዲስ በተጀመረው የውድድር ዘመንም በስድስት ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ሦስት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።