ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፑቲን ለሰሜን ኮሪያው መሪ ቅንጡ መኪና መስጠታቸው ከደቡብ ኮሪያ ተቃውሞ ገጠመው
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በአገራቸው የተሠራ ቅንጡ መኪና በስጦታ ማበርከታቸውን ደቡብ ኮሪያ ተቃወመች።
የሰሜን ኮሪያ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የፑቲን ስጦታ የሆነው ሊሞዚን፣ ፒዮንግ ያንግ ውስጥ ለፕሬዝዳንቱ ከፍተኛ ረዳቶች የተሰጠው እሁድ ዕለት ነው።
የፑቲን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ስጦታው መበርከቱን አረጋግጠው፣ አውረስ ከተባለ ቭላድሚር ፑቲን ከሚጠቀሙት ጋር ተመሳሳይ ቅንጡ መኪና መሆኑን ተናግረዋል።
ከምዕራባውያን ጋር ሆድ እና ጀርባ የሆኑት ሁለቱ አገራት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች በኋላ ግንኙነታቸውን አጠናክረዋል።
በሁለቱ አገራት ላይ ማዕቀብ የተጣለባቸው ቢሆንም፣ ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ መድፍ፣ ሮኬት እና ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን እያስታጠቀች ነው ቢባልም፣ አገራቱ ግን ያስተባብላሉ።
ባለፈው መስከረም ወር ኪም ሩሲያን በጎበኙበት ጊዜ በፑቲን መኪና በተጓዙበት ወቅት በቅርበት ተመልከተውት ነበር። የሰሜን ኮሪያው ፕሬዝዳንት ለመኪኖች የተለየ ፍቅር ያላቸው ሲሆን፣ ቅንጡ የውጭ አገራት መኮንኖችን የመሰብሰብ ልምድ አላቸው።
የኪም እህት ዮ ጆንግ “ስጦታው በሁለቱ አገራት መሪዎች መካከል ያለውን ልዩ ግንኙነት የሚያሳይ ነው” ማለታቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ነገር ግን የደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስጦታው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅንጡ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ሌሎችንም ወደ ሰሜን ኮሪያ እንዳይገቡ የተጣለውን ዕቀባ የሚጥስ ነው ብሏል።
ሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ ፑቲን በቅርቡ ፒዮንግያንግን እንደሚጎበኙ አመልክተዋል።
ሰሜን ኮሪያ በምታካሂደው የኑክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታ እና በተወንጫፊ ሚሳኤሎች ያልተቋረጠ ሙከራ ምክንያት ከጎረቤቶቿ እና ከምዕራባውያን ጋር ሆድ እና ጀርባ ስትሆን፤ ሩሲያ ደግሞ ሁለት ዓመት ሊሞላው በተቃረበው የዩክሬን ወረራ ምክንያት ከምዕራባውያኑ ጋር ተፋጣለች።