ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሰሜን ኮሪያ በጃፓን ላይ ያለፈ የባለስቲክ ሚሳኤል ማስወንጨፏ ተነገረ
ሰሜን ኮሪያ ሚሳኤል ሳይሆን እንዳልቀረ የተገመተ መሳሪያ በሰሜን የጃፓን ላይ አሳልፋ አስወነጨፈች።
ሰሜን ኮሪያ ሚሳኤሉን መተኮሷን ተከትሎ የጃፓን መንግሥት በአካባቢው ያሉ ዜጎቹ በመጠለያ እንዲሸሸጉ ማስጠንቀቂያ መልዕክት ለመላክ ተገዷል። የባቡር እንቅስቃሴም በጊዜያዊነት እንዲቋረጥ ተደርጓል።
ሰሜን ኮሪያ በጃፓን ድንበር ላይ ያለፈ ሚሳኤል ለመጨረሻ ጊዜ የተኮሰችው ከ5 ዓመታት በፊት እአአ በ2017 ነበር።
ሰሜን ኮሪያ የባለስቲክ እና የኒውክለር ሙከራ እንዳታደርግ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ታግዳለች።
“ሰሜን ኮሪያ ሚሳኤል አስወንጭፋለች። ራሳችሁን ወደ ህንጻዎች ወይንም ከምድር በታች ወደ ሚገኙ ስፍራዎች ሸሸጉ” ሲል የጃፓን መንግሥት ብዙም ያልተለመደ መልዕክት ለዜጎቹ አስተላልፏል።
ባለስልጣናት እንዳሉት ሚሳኤሉ ከጃፓን 3 ሺህ ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ ወድቋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ምንም ጉዳት አለመመዝገቡ ታውቋል።
የጃፓኑ ጠቅላይ ሚንስትር ፉሚዮ ኪሺዳ ድርጊቱን “ጠብ አጫሪ ባህሪ” ሲሉ አጥብቀው ኮንነዋል። የጃፓን መንግሥት ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ስብሰባ ለመቀመጥም ተገዷል።
ድርጊቱ የሰሜን ኮሪያውን መሪ ኪም ጆንግ-ኡንን ችላ ያሉትን ጃፓንን እና አሜሪካን ትኩረት ለመሳብ ሆን ተብሎ የተደረገ ሊሆን ይችላል ተብሏል።
አገራትን ሳያስጠነቅቁ ወይም ሳያማክሩ በላያቸው ላይ ሚሳኤል ማስወንጨፍ ዓለም አቀፍ ሕግን የሚቃረን ነው።
ብዙ አገራትም ጥቃት ሊመስል ይችላል በሚል እንዲህ ዓይነት ድርጊት አይፈጽሙም።
አሜሪካ በምስራቅ ኢሲያ ዲፕሎማቷ ዳንኤል ክሪተንበሪንክ በኩል ድርጊቱን “ተገቢ ያልሆነ” ብላዋለች።
የፒዮንግያንግ ሊያስቆጣ ይችላል የተባለለት የጃፓን፣ የአሜሪካ እና የደቡብ ኮሪያ የሦስትዮሸ ወታደራዊ ልምምድ የተደረገው ከቀናት በፊት ነው።
የሚሳኤል ማስወንጨፉ ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ ለአምስተኛ ጊዜ የተደረገ ነው። ቅዳሜ ዕለት ሁለት ሮኬቶች ተተኩሰው በጃፓን አቅራቢያ በሚገኝ ውሃ ላይ አርፈዋል።