በናይጄሪያ እርዳታ ለመቀበል በተፈጠረ መረጋገጥ የ31 ሰዎች ሕይወት አለፈ

በደቡባዊ ናይጄሪያ ፖርት ሃርኮርት ከተማ በሚገኝ አንድ ቤተክርስቲያን የእርዳታ እህል ለመቀበል በርካታ ሰዎች በሰበሰቡበት ቦታ መረጋገጥ ተፈጥሮ የ31 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።

ባለፈው ቅዳሜ ጠዋት አንድ ቤተ-ክርስትያን በስፖርት ሜዳ ላይ ሊያከፋፍል ያቀደውን የእርዳታ እህል ለመቀበል አንዳንዶች ሌሊቱን እዚያው አድረው ጠብቀዋል።

በጉዳዩ ላይ ምርመራ መክፈቱን የገለጸው ፖሊስ፤ አስተባባሪዎች በቦታው የተፈጠረውን ግርግር መቆጣጠር እና ሕዝቡን ለማረጋጋት ሳይችሉ ቀርተዋል ብሏል።

በአደጋው ሕወታቸውን ካጡት መካከል አብዛኞቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውም ተገልጿል።

የዓይን እማኞች ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ከፍተኛ መገፋፋት መፈጠሩን እና ወደ መግቢያው ለመጠጋት የሚሞክሩ ሰዎችን ወደ ኋላ ለማስመለስ በተደረገው ጥረት መካከል መረጋገጥ ተፈጥሯል ሲሉ ተናግረዋል።

"ከውስጥ ያሉ ሰዎች 'ተመለሱ፣ ተመለሱ፣ ተመለሱ' ይሉ ነበር" ሲል ቺሶም የተባለ አንድ የዓይን እማኝ ተናግሯል። “ከዚያም ከውጪ ወደ ውስጥ ለመግባት ሲጋፉ የነበሩ ሰዎች በእነሱ ላይ ወጡባቸው’’ ሲልም አክሏል።

ሁኔታውን በቁጥጥር ስር ለማዋል የፀጥታ እና የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ወደ ስፍራው ተሰማርተው እንደነበረም ተዘግቧል።

ከተጎዱት ሰዎች መካከል የተወሰኑት በፖርት ሃርኮርት ወታደራዊ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛል።

'ኪንግስ አሰምብሊ' የሚሰኘው ይሄው ቤተክርስቲያን በአደጋው “በጣም አዝኛለሁ” ሲል መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ እንዲህ አይነት አደጋዎችን ለማስቀረት የሚያስችሉ የውስጥ ፖሊሲ ማሻሻያ ለማድረግ ግምገማ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

ቤተ ክርሰቲያኑ እ.ኤ.አ. በ2014 ነበር ዓመታዊ የበጎ አድራጎት ተግባሩን የጀመረው። ነገር ግን በዚህ ዓመት የተካሄደው የድጋፍ ፕሮግራም ላይ የተሳተፈው የሰው ቁጥር በፍጹም ያልተጠበቀ መሆኑን እና የፀጥታ ኃይሎች በቦታው ከመገኘታቸው በፊት ሕዝቡ መሰባሰብ መጀመሩን ገልጿል።

የግዛቲቷ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢቦካ ፍራይዴይ የሃይማኖት እና የበጎ አድራጎት ቡድኖች ለወደፊቱ እንደዚህ አይነት ፕሮግራሞችን በሚያዘጋጁበት ወቅት "ከፖሊስ ጋር በመተባበር ለሕዝብ ደኅንነት መስራታቸውን እንዲያረጋግጡ" ጥሪ አቅርበዋል።

ናይጄሪያ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በርካታ ተመሳሳይ አሳዛኝ ክስተቶችን ያስተናገደች ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት በቦርኖ ግዛት አንድ የእርዳታ ድርጅት ተመሳሳይ የምግብ ማከፋፈል ፕሮግራም በማካሄድ ላይ ሳለ በተፈጠረ መረጋገጥ 7 ሴቶች ሕይወታቸው አልፏል።

አሁን አደጋው ያገጠመባት ፖርት ሃርኮርት ከተማ የናይጄሪያ ዋነኛ የነዳጅ ዘይት ማዕከል ናት። ናይጄሪያ ከፍተኛ የነዳጅ ሃብት ቢኖራትም 40 በመቶ የሚሆኑት ዜጎቿ ከድህነት ወለል በታች ይኖራሉ።