የፋኖ ኃይል በአንድ ዕዝ ሥር አለመሆን ከመንግሥት ጋር ለሚደረግ ድርድር እንቅፋት መሆኑን አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ተናገሩ

በአማራ ክልል ከመንግሥት ጋር ውጊያ ላይ ያለው የፋኖ ኃይል በአንድ ዕዝ ሥር አለመሆኑ መንግሥት ከኃይሉ ጋር ለሚደረግ “ንግግርም ሆነ ድርድር” አመቺ እንዳልሆነ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ተናገሩ።

አምባሳደር ተሾመ፤ ከአማራ ክልል የሚነሳው የአካባቢ ይገባኛል ጥያቄ እና የኤርትራ ሠራዊት በድንበር አካባቢ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በትግራይ ክልል እና በፌደራል መንግሥት መካከል ያለውን መተማመን “ሊሸራርፍ” እንደሚችልም ገልጸዋል።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ይህንን የተናገሩት ባለፈው ሳምንት አርብ ኅዳር 28፣ 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ከሆኑት ኧርቪን ማሲንጋ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ነው።

ባለፈው ሳምንት በትግራይ እና አማራ ክልሎች በጉብኝት ላይ የነበሩት የአሜሪካው አምባሳደር፤ ከሁለቱ ክልሎች ባለሥልጣናት እና የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የአሜሪካ ኤምባሲ አስታውቆ ነበር።

አምባሳደር ኧርቪን ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ከትግራይ ክልል አመራሮች ጋር በፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸም ዙሪያ ንግግር ማድረጋቸው ተገልጾ ነበረ።

በአማራ ክልል ባደረጉት ውይይት ደግሞ በክልሉ የተፈጠረው “ቀውስ” የተቋማት እንቅስቃሴ ላይ ምን አይነት ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሆነ መነሳቱ ተጠቅሷል።

ከዚህ ጉብኝት ከሁለት ቀናት በኋላ በአዲስ አበባ ከተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ጋር ውይይት ያደረጉት አምባሳደር ኧርቪን፤ በአማራ ክልል ያለውን ግጭት ማንሳታቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

በክልሉ እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት የተፈናቃዮች ቁጥር ሊጨምር የሚችል መሆኑ በትግራይ ክልል አመራሮች ላይ የፀጥታ ስጋት እንደፈጠረ ለአምባሳደር ተሾመ ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ከአማራ ክልል የሚነሳ የይገባኛል ጥያቄም በተመሳሳይ እንዳሳሰባቸው እንደገለጹላቸው አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

አምባሳደር ኧርቪን፤ ይህ የይገባኛል ጥያቄ እና በኤርትራ በኩል የሚታዩ “ሁኔታዎች” የትግራይ ክልል ከፌደራል መንግሥት ጋር ያለውን “የመተማመን ደረጃ የሚቀንሱ” ድርጊቶች እንደሆኑ ማስተዋላቸውን እንደገለጹም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

አምባሳደሩ አክለውም የትግራይ ክልል አመራሮች “በኤርትራና በአማራ ክልል በሚታዩ ሁኔታዎች የተነሳ ትጥቅ የመፍታቱ ጉዳይ ፈታኝ ሁኔታ እንደሆነባቸው” ማንሳታቸውን ለአምባሳደር ተሾመ ነግረዋቸዋል ተብሏል።

ከአሜሪካው አምባሳደር ለተነሱት ሐሳቦች ምላሽ የሰጡት የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር፤ በአማራ ክልል የተነሳውን ግጭት ለማርገብ “ማኅበረሰብ ተኮር ምክክሮች እየተካሄዱ” እንደሆነ ገልጸዋል።

በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን የፋኖ ኃይል እና በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኘው የኤርትራ ሠራዊት ጉዳይን የፌደራል መንግሥት በባለቤትነት መያዙን ለአሜሪካው አምባሳደር ተናግረዋል።

ሁለቱን ጉዳዮች በበላይነት ከያዘው ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር በመሆን መፍትሄ ለማምጣት እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል።

ይሁንና “ፋኖ በአንድ ዕዝ ሥር አለመሆኑ እንደ አንድ ኃይል ለመነጋገርም ሆነ ለመደራደር አመቺ ሁኔታ አለመፍጠሩን” አምባሳደር ተሾመ መግለጻቸውን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስታውቋል።

ከዚህም በተጨማሪ የፋኖ ኃይሎች በፌደራል መንግሥት ላይ እምነት እንደሌላቸውን መግለጻቸውን አንስተዋል።

እንደ አምባሳደር ተሾመ ገለጻ የፋኖ ኃይሎች በፌደራል መንግሥት ላይ “ሙሉ መተማመን” እንደሌላቸው የሚናገሩት ”የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ወገኖች ጋር ሰላም ለመፍጠር ሲንቀሳቀስ በአማራው ላይ ግን ጦርነት አውጇል” በማለት ነው።

ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገው የነበሩት የአማራ ሕዝባዊ ኃይል ፋኖ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ አስረስ ማረ ዳምጤ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የተለያየ መጠሪያ ያላቸው የፋኖ አደረጃጀቶች እንዳሉ ተናግረው ነበር።

“በአንድ መሪ፣ በአንድ መዋቅር፣ በአንድ አደረጃጀት ውስጥ አልገባም” ያሉት አቶ አስረስ፤ ሁሉም አደረጃጀቶች ግን “አንድ ዓላማ” እንዳላቸው እና “በትብብር” እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የድርድር ጉዳይ ተነስቶላቸው የነበሩት የፋኖ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊው፤ ከመንግሥት ጋር ድርድር ለማድረግ መከላከያ ሠራዊት ክልሉን ለቆ መውጣቱ በቅድመ ሁኔታነት እንደሚቀመጥ ተናግረዋል።

ቡድኑ በድርድር ወቅት የሚቀርብ የታጣቂ ቡድኑን “ቀይ መስመሮች” የያዘ ሰነድ ማዘጋጀቱንም ገልጸው ነበር። ይሁንና እስካሁን ደረስ ከመንግሥት በኩል ይፋዊ የእንደራደር ጥያቄ እንዳልቀረበ አክለዋል።

ከአማራ ክልል በኩል የሚነሳ የይገባኛል ጥያቄ በትግራይ ክልል እና በፌደራል መንግስት መካከል ያለውን መተማመን ሊሸረሽር ይችላል የመባሉን ጉዳይ አምባሳደር ተሾመ እንደሚስማሙበት መገለጻቸውን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስታውቋል።

አምባሳደር ተሾመ ይህ ጥያቄ እና የኤርትራ ሠራዊት የድንበር ላይ እንቅስቃሴ የፕሪቶሪያ ስምምነት በተፈረመበት ወቅት የትግራይ ክልል አመራሮች በፌደራል መንግሥት ላይ የነበራቸውን የመተማመን ደረጃ “ሊሸራረፍ የሚችልበት ሁኔታዎች” መስተዋላቸውን ገልጸዋል ተብሏል።

አምባሳደር ተሾመ፤ ከትግራይ በኩል የሚነሱ “የፀጥታ ስጋቶች እየጨመሩ መምጣታቸው እና [በሁለቱ አካላት መካከል] የነበረው የመተማመን ደረጃ እየቀነሰ መሄድ” የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ፕሮግራምን ለመተግበር “አንድ እክል” እንደሆነ መጥቀሳቸውም ተገልጿል።

በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የሚመራው የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ፕሮግራም ባጋጠመው የፋይናንስ እጥረት ምክንያት እንደዘገየው ከአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ጋር በተደረገው ውይይት ላይ እንደተነሳም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

በፕሮግራሙ ትግበራ መዘግየት ምክንያት ከቀድሞ ተዋጊዎች መካከል “ጥቂቶቹ ሜዲትራንያን ባሕርን ለማቋረጥ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመራቸውን” ተናግረዋል ተብሏል።

ይህ የቀድሞ ተዋጊዎች እንቅስቃሴ ካልተገታም “በአውሮፓ ባለው የስደት ቀውስ ተጨማሪ ስጋት ሊሆን እንደሚችል” ኮሚሽነሩ አምባሳደር ተሾመ ለአሜሪካ አምባሳደር እንደነገሯቸው ተገልጿል።

ለዚህ ፕሮግራም ትግበራም ኮሚሽኑ የአሜሪካ መንግሥት ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እንዲሁም የፋይናንስ ድጋፍ “በወሳኝነት እና በከፍተኛ ደረጃ የሚጠበቅ” እንደሆነ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ላይ የተቋቋመው የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ 274,000 የቀድሞ ተዋጊዎችን በተሃድሶ ፕሮግራም ውስጥ ለማሳለፍ ዕቅድ አለው።

ይሁንና የዚህ ፕሮግራም ትግበራ የሚጠይቀው በጀት ከፍተኛ በመሆኑ ኮሚሽኑ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ሊጀመር የነበረውን የመጀመሪያ ዙር የተሃድሶ ፕሮግራም ትግበራ በተደጋጋሚ አራዝሟል።