ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፈረንሳይ በስደተኛው ግለሰብ በስለት የተወጉት ሕጻናት እያገገሙ ነው ተባለ
በሶሪያዊው ስደተኛ በስለት ተወግተው ክፉኛ የቆሰሉት አራት ሕጻናት በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ተባለ።
ትናንት በፈረንሳይዋ አነሲ ከተማ በስደተኛው ግለሰብ በስለት የተወጉት ከአንድ እስከ ሦስት ዓመት ድረስ ያሉት አራት ሕጻናት ሲሆኑ የጤና ክትትል በሆስፒታል እየተደረገላቸው ይገኛል።
ተጠርጣሪው በፓርክ ውስጥ ባለ የመጫወቻ ስፍራ ገብቶ ጥቃቱን ካደረሰ በኋላ በፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውሏል።
ከአራቱ ሕጻናት በተጨማሪ ሁለት አዋቂ ሰዎችም በስለት ጥቃቱ ተጎድተዋል። ከእነዚህ አዋቂዎች መካከል አንዱ ለሕይወት አስጊ የሆነ ጉዳት ገጥሞታል ተብሏል።
ፖሊስ ጥቃት አድራሹ የ31 ዓመት የሶሪያ ዜግነት ያለው እና በሰዊድን ስደተኛ ተብሎ የተመዘገበ ነው ብሏል።
ጥቃቱን የሚያሳዩ ማሕብራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቁ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ግለሰቡ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በመጫወቻ ስፍራ ላይ ያሉ ሕጻናትን እየፈለገ በስለት ሲወጋ አሳይተዋል።
ግለሰቡ የሕጻናት ጋሪ ላይ የነበረ ጨቅላን ጭምር አጥቅቷል።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኤማኑኤል ማክሮን ክስተቱን “የፈሪ ጥቃት” ሲሉ የገለጹት ሲሆን የአገር ውስጥ እና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ወደ ጥቃት ስፍራው አምርተዋል።
የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚንስትር ኤሊሳቤት ቦርን ጥቃቱን በተመለከተ ምርመራዎች እየተደረጉ መሆኑን በመግለጽ ጸጥታ አስከባሪዎች አሁን ላይ ያላቸው መረጃ ውስን ነው ብለዋል።
ጥቃት አድራሹ የአእምሮ ሕመም ሆነ የወንጀል ሬኮርድ እንደሌለበት ገልጸዋል።
በስዊድን የተመዘገበ ስደተኛ የሆነው ግለሰብ የትዳር አጋሩን እና የሦስት ዓመት ሴት ልጁን ስዊድን ጥሎ ከመጣ በኋላ በፈረንሳይ አዎንታዊ ምላሽ ያላገኘ የጥገኝነት ጥያቄ መጠየቁም ተመልክቷል።
ክርስቲያን ነኝ የሚለው ጥቃት አድራሽ፤ ቤት አልበ በመሆኑ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠልሎ ሲኖር እንደነበረ እንዲሁም ጥቃቱን ሲፈጽም ‘በኢየሱስ ስም’ እያለ ነበር ተብሏል።
የቀድሞ ባለቤቱ ነች የተባለች ሴት ቢኤፍኤም ቲቪ ለተሰኘ የቴሌቪዥን ጣቢያ ስትናገር፤ “ከደወለልኝ አራት ወር አልፎታል። እኛ ስዊድን ስለምንኖር ግንኙነታችን ተቋርጧል። እሱ ስዊድን መኖር አይፈልግም” ካለች በኋላ የቀድሞ የትዳር አጋሯ የአመጽ ባሕሪ እንደሌለበት ተናግራለች።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፈረንሳይ በስለት የሚፈጸሙ ጥቃቶችን መስማት የተለመደ እየሆነ መጥቷል። እነዚህ ጥቃቶች የወንጀል ሬኮርድ ባለቸው ወይም ከጽንፈኛ እስላማዊ እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት ባላቸው ወንዶች በብዛት ሲፈጸሙ ተስተውለዋል።
በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ለማሰብ በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች የጸሎት ሥነ-ስርዓቶች ተካሂደዋል።
ፕሬዝዳንት ኤማኑኤል ማክሮን በትዊተር ገጻቸው ጥቃቱን ተከትሎ መለው ሕዝብ “ከፍተኛ ድንጋጤ” ውስጥ መግባቱን ገልጸው ጥቃቱን “የፈሪ ተግባር ነው” ብለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ሪሺ ሱናክ ደግሞ በጥቃቱ የተጎዱትን እናስባቸዋለን ካሉ በኋላ በጉዳዩ ላይ ከፕሬዝዳንት ማክሮን ጋር ተነጋግረናል ያሉ ሲሆን አገራቸው የተቻላትን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ናት ብለዋል።