ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ እስር ቤት ከተነሱት ጉርድ ፎቶ ሽያጭ 7 ሚሊዮን ዶላር አፈሱ
የትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ከጉርድ ፎቶ ማስታወቂያ ሽያጭ ብቻ 7.1 ሚሊዯን ዶላር መሰብሰቡን ገለጸ።
ዶናልድ ትራምፕ ይህን ጉርድ ፎቶ የተነሱት በጆርጂያ ግዛት ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላ እስር ቤት ውስጥ ነው።
በግዛቲቱ ሕግ አንድ ተጠርጣሪ እስር ቤት ሲገባ አሻራውን ከሰጠ በኋላ የእስረኛ ጉርድ ፎቶ የግድ መነሳት ይኖርበታል።
ዶናልድ ትራምፕም ወደ ፖሊስ ጣቢያ ቀርበው እጅ ከሰጡ በኋላ ነው አትላንታ ከተማ በሚገኝ እስር ቤት ቀርበው ጉርድ ፎቶ እንዲነሱ የተገደዱት።
ትራምፕ የምርጫን ውጤትን በሕገ ወጥ መንገድ ለመቀልበስ ሞክረዋል በሚል ነው ክስ የተመሠረተባቸው።
ትራምፕ ከእስር ቤት የወጡት 200ሺህ ዶላር የገንዘብ ዋስ ከፍለው ነው።
የዶናልድ ትራምፕ ተቃዋሚዎች ይህ የእስር ቤት ጉርድ ፎቶ ለሰውየውና ደጋፊዎቻቸው የውርደት ማቅ ያከናንባል ብለው በጉጉት ሲጠብቁት የነበረ ሲሆን ውጤቱ ግን የተገላቢጦሽ ሆኗል።
የጉርድ ፎቶው መለቀቅን ተከትሎ የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ይህንኑ ፎቶ በስፋት በኩባያዎች፣ በቲሸርቶችና ኮፍያዎች ላይ በማተም ለገበያ አቅርቦት ከፍተኛ ገቢ ማግኘት ችሏል።
የጆርጂያን ክስ ተከትሎ ትራምፕ ከፍተኛ የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ የከፈቱ ሲሆን በሦስት ሳምንት ብቻ 20 ሚሊዮን ዶላር ብር መሰብሰብ ችለዋል።
ባለፈው ዐርብ ትራምፕ እስር ቤት በገቡ በ24 ሰዓት ውስጥ ብቻ 4.18 ሚሊዮን ዶላር የተሰበሰበ ሲሆን ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገኘ ትልቅ ገቢ ሆኖ ክብረ ወሰን ሰብሯል።
ትራምፕ ከጥር 2021 ጀምሮ ዞር ብለው ያላዩትን ትዊተር ገጻቸውን (አሁን ኤክስ ተብሎ የተሰየመውን ማኅበራዊ ሚዲያ) ለመጀመርያ ጊዜ የተጠቀሙበት ሲሆን ከዚህ የእስረኛ ጉርድ ፎቶ ሥር “መቼም እጅ አንሰጥም’ ከሚል መልዕክት ጋር አጋርተውታል።
ዶናልድ ትራምፕ በአራት ግዛቶች በድምሩ 91 ክሶች ቀርበውባቸዋል። እርሳቸው ግን ክሶቼ ሆን ብለው የተቀነባበሩና ፖለቲካዊ ናቸው ይላሉ።