ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ተርጓሚዎችና አሳታሚዎች የተጎዱበት መጽሐፍ ደራሲ በስለት ተወግቶ በአስጊ ሁኔታ ላይ ነው
‘ዘ ሳታኒክ ቨርስስ’ [ሰይጣናዊ ጥቅሶች] በሚባለው መጽሐፉ ምክንያት ለሦስት አስርት ዓመታት በጥቃት ስጋት ስር የቆየው ሳልማን ሩሽዲ ለሕይወቱ አስጊ ጥቃት ተፈጽሞበታል።
የዚህ መጽሐፉ ዳፋ በእሱ ላይ ብቻ ሳይሆን መጽሐፉን ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች በተረጎሙ እና ባሳተሙት ላይ ጭምር ሞትና ጉዳትን አስከትሏል።
አሁን ደግሞ በመጽሐፉ ሰበብ በተሰነዘረበት የግድያ ዛቻ ምክንያት ለዓመታት በከባድ የደኅንነት ጥበቃ ስር የኖረው ሳልማን ሩሽዲ ኒውዮርክ ውስጥ በስለት ተወግቶ ከባድ ጉዳት ደርሶበታል።
ቡከር የተሰኘው የፀሐፊዎች ሽልማት አሸናፊ የሆነው የ75 ዓመቱ ሩሽዲ፣ አሜሪካ ኒው ዮርክ ውስጥ በሚገኝ በአንድ ተቋም ውስጥ መድረክ ላይ ንግግር እያደረገ ሳለ ነበር ጥቃቱ የተፈጸመበት።
የኒው ዮርክ ግዛት ፖሊስ ፣በጥቃት ፈጻሚነት የተጠረጠረው ከኒው ጀርሲ ግዛት የመጣው የ24 ዓመቱ ወጣት ሐዲ ማታር ነው ብሏል።
ፖሊስ የጥቃቱ ምክንያት ምን እንደሆነ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ አስፈላጊ መረጃዎችን በማሰባሰብ ምርመራ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ወጣቱ ሩሽዲን ቢያንስ አንድ ጊዜ አንገቱ ላይ በተጨማሪም ሆዱ ላይ በስለት የወጋው ሲሆን፣ ወዲያው በሄሊኮፕተር ለህክምና ተወስዷል። ጥቃት ፈጻሚው በቁጥጥር ስር የዋለ ቢሆንም እስካሁን የጥቃቱ ምክንያት ምን እንደሆነ አልታወቀም።
የሳልማን ሩሽዲ ወኪል፣ ደራሲው አሁን ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ እንደተናገረው፣መናገር እንደማይችልና በሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ ድጋፍ እየተደረገለት ሲሆን፣ ከተፈጸመበት ጥቃት የተነሳ አንድ ዓይኑን ሊያጣ እንደሚችል ስጋት አለ ብሏል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1988 ሳልማን ሩሽዲ ‘ዘ ሳታኒክ ቨርስስ’ የተሰኘ መጽሐፉን ካሳተመ በኋላ የእስልምና እምነትን አንቋሿል በሚል በግድያ ዛቻ ስር ከ30 ዓመታት በላይ ኖሯል።
ደራሲው በደረሰበት የስለት ጥቃት ወደ ሆስፒታል ከገባ በኋላ ወኪሉ አንድሩ ዋይሊ፣ “ሳልማን አንድ ዓይኑን ሊያጣ ይችላል፣ በክንዱ ላይ ያለው ነርቭ ተጎድቷል፣ ጉበቱም በስለት ተወግቶ ተጎድቷል” ብሏል።
በጥቃቱ ወቅት ከሩሽዲ ጋር መድረኩ ላይ ነበረ የተባለው ግለሰብ ሔንሪ ሪስም በጭንቅላቱ ላይ ጉዳት ደርሶበት ወደ ሆስፒታል ተወስዷል። ሔንሪ በጥቃት ውስጥ ሆነው ለተሰደዱ ፀሐፊያንን መጠለያና ድጋፍ የሚሰጥ በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራች ነው።
ጥቃቱ በተፈጸመበት ጊዜ በሥፍራው የነበሩ ሠራተኞችና ንግግሩን ለማዳመጥ የተሰበሰቡ ታዳሚዎች ወደ መድረኩ በመውጣት ጥቃት ፈጻሚውን ተረባርበው እንደያዙት ፖሊስ አመልክቷል።
የ‘ዘ ሳታኒክ ቨርስስ’ መዘዝ
ትውልዱ ሕንድ የሆነው የልብ ወለድ ፀሐፊ ሳልማን ሩሽዲ በሥራው እውቅናን ማግኘት የጀመረው ከ40 ዓመታት በፊት የጻፈውና በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ብቻ ከአንድ ሚሊዮን ቅጂዎች በላይ በተሸጠለት ‘ሚድናይትስ ችልድረን’ በተሰኘው መጽሐፉ ነው።
ነገር ግን በ1988 (እአአ) ያሳተመው ‘ዘ ሳታኒክ ቨርስስ’ የተሰኘው መጽሐፉ ይዘት በአንዳንድ ሙስሊሞች ዘንድ እስልምናን የሚያንቋሽሽ ነው ተብሎ ተወግዟል።
በተጨማሪም አንዳንድ አገራት ይህንን መጽሐፉ እስከማገድ ደርሰዋል። በዚህም ሳቢያ ለአስር ዓመታት ተደብቆ ለመኖር ተገዶ ነበር።
ይህንን መጽሐፍ ተከትሎ ሕንድ ውስጥ በተቀሰቀሱ ፀረ- ሩሽዲ የተቃውሞ አመጾች ምክንያት በርካታ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ኢራን ውስጥ የሚገኘው የብሪታኒያ ኤምባሲም በተቃዋሚዎች በድንጋይ ተደብድቦ ነበር።
በአውሮፓውያኑ 1991 የሩሽዲን መጽሐፍ የተረጎመው ጃፓናዊ በስለት ተወግቶ ተገድሏል።
በተጨማሪም መጽሐፉን ወደ ጣሊያንኛ የተረጎመው ግለሰብም እንዲሁ የስለት ጥቃት የተፈጸመበት ሲሆን፣ የኖርዌይ ዜጋ የሆነው የመጽሐፉ አሳታሚ ደግሞ በጥይት ተመትቶ ተርፏል።
‘ዘ ሳታኒክ ቨርስስ’ የተሰኘው ይህ መጽሐፍ ለንባብ ከበቃ ከዓመት በኋላ የኢራኑ ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ ኾሚኒ ደራሲው ሳልማን ሩሽዲ በተገኘበት እንዲገደል ጥሪ አቀረቡ።
በዚህ ፋትዋ [እስልምና ሃይማኖት መሪ የሚተላለፍ ትዕዛዝ] መሠረት ደራሲውን ለሚገድል ግለሰብ የ3 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት እንደሚሰጠውም ኾሚኒ አስታውቀው ነበር።
የኢራን መንግሥት አያቶላህ ኾሚኒ ካስተላለፉት የሳልማን ሩሽዲ የግድያ ጥሪ እና ከሚሰጠው የገንዘብ ሽልማት እራሱን ያራቀ ቢሆንም እስካሁን የግድያ ጥሪው አልተነሳም።
እንዲያውም ከፊል መንግሥታዊ የሆነ አንድ የኢራን ሃይማኖታዊ ተቋም ከአስር ዓመት በፊት ከቀረበው ሽልማት ላይ 500,000 ዶላር መጨመሩን አሳውቆ ነበር።
አርብ ዕለት አሜሪካ ውስጥ በተፈጸመበት የስለት ጥቃት በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘው ሳልማን ሩሽዲ፣ እምነቱን ተግባራዊ ከማያደርጉ ሕንዳዊ ሙስሊም ቤተሰቦች የተወለደ ሲሆን እሱ ደግሞ ኢ አማኝ ነው።
ሩሽዲ የአሜሪካ እና የብሪታኒያ ጥምር ዜግነት ያለው ሲሆን፣ የመናገር ነጻነት መብት እንዲከበር በመቀስቀስ ይታወቃል።