ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስን “የእኛ ናት” የሚሉት የሕንዷ መንደር ነዋሪዎች
በደቡባዊቷ ሕንድ ከተማ ቼናይ ግዛት 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው አነስተኛዋ መንደር ቴላሴንድድራፑራም ነዋሪዎች የአሜሪካዋን ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ የእኛ ናት እያሉ ነው።
ከዋሽንግተን ዲሲ በ14 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ይህች አነስተኛ መንደር፣ የካማላ ሃሪስ በእናታቸው በኩል ያሉ አያቶቻቸው የትውልድ ስፍራ ናት።
በመንደሯ ማዕከል የ59 ዓመቷ ካማላ ሃሪስ ትልቅ ባነርም ተሰቅሎ ይታያል።
የዲሞክራቶች ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ የሆኑት ካማላ እንዲሳካላቸውም የመንደሪቷ ነዋሪዎች ለአማልክቱ ጸሎት እያደረሱ ነው።
የካማላ እንዲሁም የአያቷ ስምም በመንደሯ ባለችው ቤተ መቅደስ ድጋፍ ባደረጉ ዝርዝር ውስጥ ተካቷል። የላኳቸውም ጣፋጮች ለነዋሪዎች እየተከፋፈለ ነው።
በዕድሜ መግፋት ምክንያት ከምርጫው ራሳቸውን እንዲያገሉ ከፍተኛ ጫና የበዛባቸው ጆ ባይደን ከፉክክሩ መውጣታቻቸውን እንዲሁም ካማላ ቀጣይዋ ዕጩ መሆናቸውን ተከትሎ ነው ነዋሪዎች የአሜሪካን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በቅርበት እየተከታተሉ የሚገኙት።
“በዓለም ላይ እጅግ ኃያል በሆነች አገር ላይ እንዲህ የላቀ ስፍራ ላይ መቀመጥ ቀላል ነገር አይደለም” ሲሉም ጡረተኛው የባንክ ሥራ አስኪያጅ ክሪሽና ሙርቲ ያስረዳሉ።
አክለውም “በእውነቱ በእሷ ኮርተናል። በአንድ ወቅት ሕንዶች በባዕድ አገራት ይገዙ ነበር። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሕንዶች ኃያላን አገራትን እየመሩ ነው” ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ካማላ ሃሪስ በተለይም ለሕንዳውያን ሴቶች ኩራት ሆነዋል። ምክትል ፕሬዚዳንቷን እንደ ራሳቸው ማኅበረሰብ አካል አድርገው የሚመለከቷቸው ሲሆን፣ በየትኛውም ቦታ ሴቶች መድረስ የሚችሉበትን ስፍራ ተምሳሌት ሆነዋል።
“ሁሉም ሰው ያውቃታል፣ ልጆች ጭምር። ‘እህቴ፣ እናቴ’ እያሉ ነው የሚጠሯት” ሲሉ የመንደሯ አስተዳደር ተወካይ የሆኑት አሩልሞዝሂ ሱድሃካር ገልጸዋል።
“መሠረቷን ስላልዘነጋች ደስ ብሎናል። ደስታችንንም እየገለጽን ነው” ብለዋል።
ካማላ ሃሪስ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዋ ሴት፣ ጥቁር እና የእስያ ዝርያ ያላቸው ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው በአውሮፓውያኑ 2020 ነበር ወደ ሥልጣነ የመጡት።
ካማላ ሃሪስ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው በተሾሙበት ወቅት የመንደሪቷ ነዋሪዎች ርችቶችን፣ ፖስተሮችን ይዘው የወጡ ሲሆን፣ ያ ደስታ እና ትዕይንትም አሁንም እየተደገመ ይገኛል።
በስፍራውም በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የታደሙበት ድግስ የተዘጋጀ ሲሆን፣ የቀረቡት የደቡባዊ ሕንድ ባህላዊ ምግቦች የሆኑት ሳምባር እና ኢድሊ ከካማላ ተወዳጅ ምግቦች መካከል እንደሆኑ ከዘመዶቻቸው አንዷ ተናግረዋል።
የሕንድ መሠረት
የጡት ካንሰር ተመራማሪ የሆኑት የካማላ እናት ሻይማላ ጎፓላን ትውልዳቸው በደቡባዊቷ ሕንድ ግዛት ታሚል ናዱ ነው። የሻይማላ ወላጆች ደግሞ ትውልዳቸው አነስተኛዋ የሕንድ መንደር ቴላሴንድድራፑራ ናት። የካማላ እናት ወደ አሜሪካ የመጡት በአውሮፓውያኑ 1958 ነው።
“እናቴ ሻይማላ ከሕንድ ወደ አሜሪካ የመጣችው ብቻዋን በ19 ዓመቷ ነበር። ኃያል ሴት ናት። ሳይንቲስት፣ የሲቪል መብት ተሟጋች እንዲሁም ሁለት ሴት ልጆቿ በኩራት እንዲያድጉ ያደረገች እናት ናት” ሲሉ ካማላ ሃሪስ ባለፈው ዓመት ባጋሩት የማኅበራዊ ሚዲያ ጽሁፋቸው ጠቅሰዋል።
በኦክላንድ፣ ካሊፎርኒያ የተወለዱት ካማላ ወላጆቻቸው ስደተኞች ሲሆኑ፣ እናታቸው ሕንዳዊት፣ አባታቸው ደግሞ ጃማይካዊ ናቸው።
አባት እና እናታቸው የተፋቱት የአምስት ዓመት ሕጻን እያሉ ሲሆን፣ ያሳደጓቸውም እናቷ ሻይማላ ጎፓላን ሃሪስ ናቸው።
እናታቸው እሷን እና እህታቸውን ማያን በኦክላንድ በነበረው ጥቁር ማኅበረሰብ ውስጥ እንዲቀላቀሉ አድርገው እንዳሳደጓቸው ካማላ ያስረዳሉ።
“እናቴ ሁለት ጥቁር ልጆችን እንደምታሳድግ በደንብ ተረድታው ነበር” ሲሉም ካማላ ሃሪስ የሕይወት ታሪካቸውን በሚተርከው ‘ዘ ትሩዝስ ዊ ሆልድ’ የሚል ርዕስ በተሰጠው መጽሐፍ ላይ አስፍረዋል።
ካማላ ሃሪስ እና እህታቸው እናታቸው ከሞቱ በኋላ ወደ ሕንድ ቼናይ ግዛት አቅንተው በሂንዱ እምነት እና ወግ መሠረት አመዳቸውን በባህሩ ውስጥ እንደበተኑም 'ዘ ሂንዱ' የተሰኘው ጋዜጣ አስነብቧል።
ካማላ ሃሪስ በሕይወታቸው ከፍተኛ ስኬትን ከተጎናጸፉ ቤተሰብ የመጡ ናቸው። የእናቷ አጎት ጎፓላን ባላንቻንድራን ምሁር ናቸው። እንዲሁም አያቷ ፒቪ ጎፓላን የስደተኞች መልሶ ማቋቋሚያ ባለሙያ እንዲሁም ታዋቂ ቢሮክራት ናቸው። በአውሮፓውያኑ 1960ዎቹም የዛምቢያ የመጀመሪያ ፕሬዝዳንት አማካሪ በመሆን አገልግለዋል።
“ካማላ ስመ ጥሩ ከሆነች የተወሰነ ጊዜ ሆኖታል። በጣም የሚያስደንቅ ነገር አይደለም። ለዓመታት ሲጠበቅ የነበረ ነገር ነው” ሲሉ በደልሂ ጃዋሃርላል ኔህሩ ዩኒቨርስቲ የፊዚክስ ፕሮፌሰር እና የካማላ እናት የክፍል ጓደኛ የሆኑት አር ራጅራማን ያስረዳሉ።
ፕሮፌሰሩ ከካማላ እናት ጋር የነበራቸው ግንኙነት ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም በ1970ዎቹ አጋማሽ አሜሪካ ሄደው በበርክሌይ ዩኒቨርስቲ እንዳገኟቸው ገልጸዋል።
“ሻይማላ ጋር በተገናኘንበት ወቅት ሻይ አቀረበችልኝ። ሁለቱ ልጆቿ ካማላ እና ማያ በስፍራው ነበሩ። እንደ ልጆች ምንም ትኩረት አልሰጡኝም” ሲሉም ፕሮፌሰሩ አስታውሰዋል።
ወደ አነስተኛዋ መንደር ስንመለስ ነዋሪዎች የካማላ ሃሪስን የፕሬዝዳንትነት ዕጩ መሆን መታወጅ በጉጉት እየጠበቁ ነበር።
“የካማላ አክስት ሳራላ ይህችን ቤተ መቅደስ አዘውትራ ትጎበኛለች። በ2014 በካማላ ሃሪስ ስም ስልሳ ዶላር (5 ሺህ ሩፒ) ለግሳለች” ሲሉ የቤተ መቅደሷ ካህን ናታራጃን ይናገራሉ።
ካህኑ የመንደሩ ነዋሪዎች እያከናወኑት ያለው ጸሎት ካማላ ሃሪስ በምርጫው እንዲያሸንፉ እንደሚረዳቸው እርግጠኛ ናቸው።
የመንደሪቷ ነዋሪዎች ከአሜሪካ በሺዎች በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ቢሆኑም፤ ነገር ግን ከካማላ የፖለቲካ ጉዞ ጋር ቁርኝት እንዳላቸው እንደሚሰማቸው ይናገራሉ።
ካማላ አንድ ቀን እንደምትጎበኛቸው ወይም መንደሪቷን በንግግራቸው ውስጥ ልታነሳ እንደሚትችል ተስፋን ሰንቀዋል።