ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዘለንስኪ ከትራምፕ ጋር ከመነጋገራቸው በፊት "ሩሲያ ሰላም አትፈልግም" አሉ
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ አራት ዓመት ገደማ የዘለቀውን ጦርነት ለመቋጨት ያለመ ንግግር ለማድረግ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር እሁድ ለመነጋገር ቀጠሮ ይዘዋል።
ሁለቱ መሪዎች ሞስኮው ድጋፏን ባልቻረችው እና በአሜሪካ በቀረበው የሰላም እቅድ ማሻሻያ ዙሪያ ከመምከር ባሻገር የተናጠል የአሜሪካ የደኅንነት ዋስትና ረቂቅ ላይ ይመክራሉ ተብሏል።
ፍሎሪዳ በሚገኘው በትራምፕ መኖሪያ ቤት ማራ ላጎ የሚደረገው ንግግር ሩሲያ በሳምንቱ መገባደጃ ኪዬቭ ላይ ከባድ የአየር ድብደባ ካደረገች በኋላ ሲሆን፤ ድብደባውንም ተከትሎ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ሞስኮው "ሰላም እንደማትፈልግ" ማስረጃ ነው ብለዋል።
ለ10 ሰዓታት በዋና ከተማዋ ኪዬቭ በዘለቀው የሚሳኤል እና የድሮን ዝናብ ሁለት ሰዎች ሲገደሉ 32 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ዘለንስኪ እሁድ ከትራምፕ ጋር በሚያደርጉት ንግግር ለዩክሬን የደኅንነት ዋስትና እና የግዛት ማረጋገጫ ማግኘትን እንደሚያነሱ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ሁለቱንም ጉዳዮች ሩሲያ ከዚህ ቀደም ለመቀበል አሻፈረኝ ብላለች።
መሪዎቹ ማሻሻያ የተደረገበት ባለ 20 ነጥብ የሰላም ስምምነት እቅድ ላይ የሚነጋገሩ ሲሆን፤ ስምምነቱ በትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ የተነደፈ እና ለሩሲያ ያደላ የሚል ስም ተሰጥቶታል።
የዩክሬን ምስራቃዊ ዶንባስ ክልል የንግግሩ ትልቁ ክፍል ሆኖ የዘለቀ ሲሆን፤ ዘለንስኪ አሁን ላይ አካባቢው "ነፃ የኢኮኖሚ ዞን" መሆን እንደሚችል እንደ አማራጭ አቅርበዋል።
ሞስኮው 75 በመቶ የሚሆነውን የዶኔትስክ ክልል እና 99 በመቶ የሚሆነውን የጎረቤት ክልል ሉሀንስክን ትቆጣጠራለች። ሁለቱ ክልሎች ዶንባስ በመባል የሚታወቁ ናቸው።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ሩሲያ ወታደሮቿን ካስወጣችበት ከምስራቃዊ የዶንባስ ክልል ወታደሮቻቸውን ለማስወጣት ባቀረቡት ሀሳብ ላይ ክሬምሌን እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።
ይሁን እንጂ እንደ ሩሲያ የዜና ኤጀንሲ (ታስ) ዘገባ ከሆነ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቅዳሜ እለት ዩክሬን "ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየተጣደፈች አይደለም" ብለዋል።
ፑቲን አክለውም ኪዬቭ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ካልፈለገች ሩሲያ ግቧን በወታደራዊ መንገድ እንደምታሳካ ተናግረዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት በአዲሱ የሰላም እቅድ ማሻሻያ ላይ ያላቸውን ተስፈኝነት "ጦርነቱን ለመቋጨት መሰረታዊ ሰነድ" ሲሉ አንፀባርቀዋል።
አርብ ዕለት ባለ 20 ነጥቡ እቅድ 90 በመቶ መጠናቀቁን ሲገልፁ "የእኛ ሥራ መቶ በመቶ ሁሉም ነገር ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ ነው" ብለዋል።
ትራምፕ ከፖለቲኮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አዲሱን ረቂቅ ለማየት እሁድ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ የሰላም ስምምነቱ በሁለቱም መሪዎች ጥሩ እንደሚሆን ጠቁመው ከፕሬዝዳናት ፑቲን ጋር በቅርቡ እንደሚነጋገሩ ገልፀዋል።
ዘለንስኪ ከትራምፕ ጋር ከመቀመጣቸው በፊት ከአውሮፓ መሪዎች ጋር የተነጋገሩ ሲሆን፤ ስምምነቱን ለመቀበል "ጠንካራ አቋም ያስፈልጋል" ብለዋል።
የጀርመኑ መራሂ መንግሥት ፍሬድሪክ መርዝ ኪዬቭ የአውሮፓ እና የኔቶ መሪዎች "ሙሉ ድጋፍ" አላት ብለዋል።