ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትራምፕ ምክትል በመሆን በዕጩነት የቀረበው አነጋጋሪው ጄዲ ቫንስ ማን ነው?
ጄዲ ቫንስ ምናልባትም የወደፊቱ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ሊሆን ይችላል። ከሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ በቀሩት የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ትኩረት ከሳቡ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ ነው።
ስለእርሱ የሚታወቁ ጥቂት ነጥቦችን እነሆ፦
ትራምፕን በንቀት የሚመለከት ሰው ነበር
አሁን ቫንስ ስለ ትራምፕ አውርቶ አይጠግብም።
የትራምፕ ጥብቅ ወዳጅ፣ ተከታይ እና የፕሬዝዳንታዊ ውድድሩ ምክትል ዕጩ ከመሆኑ በፊት ጄዲ ቫንስ ለትራምፕ ከፍተኛ ንቀት ነበረው።
“ትራምፕ ከባድ ድድብና ያለበት ሰው ነው - እጸየፈዋለሁ” ብሎ ነበር በአንድ ወቅት።
ይህን ያለው በአውሮፓውያኑ 2016 ነበር።
በዚያው ዓመት አብሮት ለሚማረው የቀድሞ የዩኒቨርስቲ ጓደኛው ጆሽ ማክላውሪን እንዲህ ብሎ ማስታወሻ ጽፎለት ነበር።
“ስለ ትራምፕ አዘውትሬ በሐሳብ እዋልላለሁ። ትራምፕ የሚባል ሰው ብሽቅ ሰው ነው ወይስ አሜሪካዊ ሒትለር እያልኩ።”
አሁን እንዲህ ብሎ የጻፈለት ጓደኛው ጆሽ በጂርጂያ የምክር ቤት እንደራሴ ነው።
ቫንስ ያኔ እንዲህ ያበሻቀጣቸውን ትራምፕ አሁን ስለእርሳቸው ታላቅነት እያወራ መሽቶ ይነጋበታል። የቫንስ አነጋጋሪነቱ የሚጀምረው ከዚሁ ነው።
ገና 40 ዓመቱ ነው
ጄዲ ቫንስ ገና 40 ዓመቱ ነው። ይህ አሁን ለደረሰበት ደረጃ “ወጣቱ” የሚያስብለው ነው።
በዚህ ወቅት የኦሃዮ ግዛት እንደራሴ ሆኖ ያገለግላል። ዕድሜው ገና ከመሆኑም በተጨማሪ ከአሜሪካ “ሚድዌስት” ከሚባለው ክፍል መገኘቱ ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል።
በተለይ ሚድዌስት የአሜሪካ ገጠራማው ክፍል ነው። ነጭ የሠራተኛ መደብ በብዛት የሚገኝበት አካባቢ ነው።
ኤሊኖይ፣ ኢንዲያና፣ አዮዋ፣ ካንሳስ፣ ኔብራስካ፣ ዊስኮንሰን፣ ሚቺጋን፣ ሜኔሶታን. . . ወዘተ ያካልላል።
ሚድዌስት የሚባለው አካባቢ በስፋት ለትራምፕ ድምጹን እንዲሰጥ፣ በተለይ ወጣቶች ትራምፕን እንዲመርጡ ለማበረታታት ከዚያው አካባቢ ተወላጅ የሆነውን ቫንስን ምክትል ማድረግ መልካም መስሎ ታይቷቸዋል - ሪፐብሊካኖች።
“ስደተኞች ውሻ እና ድመት እየበሉ ነው”
አንዱ የቫንስ መለያ ባህሪ እና መነጋገሪያነቱ የሚመነጨው በየሚዲያው ቀርቦ ከሚሰጣቸው ሐሳቦች ነው።
በአንድ ወቅት እንዲህ ሲል ተናገረ። “የሔይቲ ስደተኞች በኦሃዮ ግዛት፣ ስፕሪንግፊልድ ከተማ ውሻ እና ድመት እየበሉ እንደሆነ ሰምተናል።”
ቫንስ ይህን ካለ በኋላ ትራምፕም ከካማላ ሃሪስ ጋር በነበራቸው የክርክር መድረክ ላይ ደግመውት መሳቀለቂያ ሆነዋል።
ወደዚህ የትራምፕ ምክትልነት ከመምጣቱ በፊትም ቫንስ በተመሳሳይ አወዛጋቢ ንግግሮቹ ይታወቃል።
በአንድ ወቅት ዩናይትድ ኪንግደምን ‘እስላማዊ አገር’ ብሎ ጠርቷታል።
በመላው አሜሪካ ጽንስን ማቋረጥ ከነአካቴው በሕግ እንዲታገድ ጥሪ አቅርቦም ነበር።
ከእነዚህ ሁሉ ንግግሮቹ አወዛጋቢ የሆነው ትዳር ሳይመሰርቱ የሚቆዩ ሴቶችን የጠራበት መንገድ ነው።
“ልጅ አልባ መሃናዊያን፤ ከድመታቸው ጋር የተወዳጁ” ሲል መስመር ያለፈ ነገር መናገሩ ቫንስን ችግር ውስጥ ከቶት ነበር።
ይህ ‘ስድቡ’ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስንም የሚጨምር ነበር።በዚህ ንግግሩ የተበሳጩ በርካታ ሴቶች ድምጻቸውን ለሃሪስ እንደሚሰጡ ዝተዋል። አሱም ይቅርታ አላለም።
በአሜሪካ የምክትል ዕጩ ፕሬዝዳንቶች ታሪክ ዝቅተኛ ተወዳጅነት ያለው ሰው ነው፣ ቫንስ።
ትራምፕ ይህን መወደድ ያልሆነለትን ሰው ለምን በሌላ አይቀይሩትም የሚለው አሁንም በምርጫ ዋዜማ ያነጋግራል።
ተንታኞች ግን የቫንስ አወዛጋቢነት እና በየሚዲያው አነጋጋሪ መሆን ከኢኮኖሚ ጥያቄ ፋታ እንዲያገኙ ስለሚያደርጋቸው ነው ይላሉ።
በከፍተኛ ቁጥር የተሸጠ መጽሐፉ
ቫንስ የተወለደው በኦሃዮ ግዛት ሚድልታውን ነው። እናቱ በከፍተኛ አደገኛ ዕጽ ሱስ ትሰቃይ ነበር። ቫንስን ገና ልጅ እያለ ነው ጥላው የጠፋችው።
እሱ ያደገው እንደ እናት እና አባት ከሚጠራቸው አያቶቹ ነው።
ቫንስ ተወዳጅ የሆነለትን ግለታሪክ መጽሐፍ ጽፏል። ይህም በ2016 የታተመ ሲሆን “ሂልቢሊ ኢሌጂ” የሚል ርዕስ አለው።
በኔትፍሊክ ወደ ፊልምነት ተቀይሯል።
በዚህ መጽሐፉ እንደሚተርከው በእናቱ የአደገኛ ሱስ መጠመድ የእርሱ ሕይወት ፈተና ውስጥ ገብቶ ነበር። ከበድ ያለ ልጅነት እንደነበረው ያትታል።
ይህ መጽሐፉ በስፋት ስለ ገጠራማው የኦሃዮ አካባቢዎች ሕይወት ይዳስሳል።
መጽሐፉ ከተወደደለት ወዲህ በስፋት የሚዲያ ሰው ሆነ። በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እየተጋበዘ ትራምፕን ማንጓጠጥ ዋና ሥራው ነበር - ያኔ። የዛሬን አያድርገውና።
ያን ጊዜ ይሰጣቸው የነበሩ ቃለ ምልልሶችን ለሰማ ሰው አሁን የትራምፕ ቀንደኛ ወዳጅ ይሆናል ብሎ አይልም።
የዝነኛው የዬል ዩኒቨርስቲ የሕግ ምሩቅ ነው
ቫንስ በትምህርቱ የላቀ ውጤት ነው የሚያስመዘግበው። የተመረቀውም ከዝነኛው ዬል ዩኒቨርስቲ ነው።
በዩኒቨርስቲ ቆይታው ከተዋወቃት የአሁኑ ሚስቱ ኡሻ ሦስት ልጆችን ወልዷል። ኢዋን፣ ቪቬክ እና ሚራብል ይባላሉ።ስድስት፣ አራት እና ሁለት ዓመት ዕድሜ አላቸው።
ባለቤቱ ኦሻ ቫንስ በሳንዲያጎ ካሊፎርኒያ ነው ያደገችው።
ወላጆቿ የሕንድ ስደተኞች ሆነው ስኬታማ የሚባሉ ናቸው። እሷም በትምህርቷ ድንቅ የምትባል ሴት ናት። ከዬል ዩኒቨርስቲ በሕግ ዲግሪ እንዲሁም ከኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ደግሞ ማስተርስ አግኝታለች።
በጽንስ ማወቋረጥ ላይ ጠንካራ አቋም አለው
ቫንስ በአውሮፓውያኑ 2019 ካቶሊክ ሆኖ ተጠምቋል። ከዚህ ቀደም በነበረው አመለካከቱ ማንኛውም ጽንስ የማቋረጥ ተግባር መታገድ አለበት የሚል አስተያየት ነበረው።
ሆኖም ትራምፕ ነገሩ ላይ ለዘብ ያለ አቋም መውሰድ ከጀመሩ ወዲህ ቫንስም ተመሳሳይ ስሜት ማንጸባረቅ ግድ ሆኖበታል።
ትራምፕ በዚህ የጽንስ ማቋረጥ ጉዳይ ላይ አሁን ያላቸው አቋም “ግዛቶች ራሳቸው ይወስኑበት” የሚል ነው።
ሆኖም እርሳቸውም ሆኑ ደጋፊዎቻቸው ጽንስ ማቋረጥ ላይ ክልከላ እንዲጣል ውስጥ ውስጡን ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው።
በቅርቡ ቫንስ አምልጦት እንዲህ አለ፦ “ኮንግረስ አገር አቀፍ የጽንስ ማቋረጥ ጉዳይ ላይ ተጻራሪ አቋም ከወሰደ ትራምፕ ድምጽን በድምጽ በመሻር መብት ይሽሩታል።”
ትራምፕ በዚህ ጉዳይ ላይ ምክትላቸውን ተቆጥተውታል።
“እውነት ለመናገር በዚህ ጉዳይ ላይ አላወራንም። እሱም አልነገረኝም። የራሱ አመለካከት ቢኖረው ግን ችግር የለብኝም” ብለዋል።
ትራምፕ በምርጫው ቀንቷቸው የፕሬዝዳንትነት መንበሩን የሚይዙ ከሆነ ጄዲ ቫንስ በአሜሪካ ታሪክ ከማይወደዱ ምክትል ፕሬዝዳንቶች አንዱ ሆኖ ወደ ሥልጣን ይመጣል።