ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አንበሶች በሚኖሩበት ፓርክ ውስጥ ለአምስት ቀናት የቆየ የስምንት ዓመት ህጻን በህይወት ተገኘ
በሰሜናዊ ዚምባብዌ አንበሶች እና ዝሆኖች በሚኖሩበት ፓርክ ውስጥ ለአምስት ቀናት የቆየ አንድ የስምንት ዓመት ህጻን በህይወት መገኘቱን የአገሪቱ የፓርላማ አባል ገለጹ።
ቲኖቴንዳ ፑዱ የተሰኘው ህጻን ከቤቱ 23 ኪሜ ወደ ሚርቀው ማቱሳዶና ፓርክ የደረሰው ዝም ብሎ እየተዟዟረ በነበረበት ወቅት መሆኑን የማሾናላንድ ዌስት የፓርላማ አባሉ ሙትሳ ሙሮምቤዚ በኤክስ ላይ ገልጸዋል።
አምስቱን ቀናትን ለማሳለፍም "በሚያገሱ አንበሶች መካከል፣ ዝሆኖችን በአቅራቢያው ሲያልፉ በድንጋያማ ቦታ ተኝቶ፣ የዱር ፍራፍሬ እየበላ" ነበር ሲሉም ተናግረዋል።
የማቱሳዶና ፓርክ 40 የሚሆኑ አንበሶች አሉት። በአንድ ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን አንበሳዎች በመያዝ ከአፍሪካ ቀዳሚው እንደነበር አፍሪካን ፓርክስ ገልጿል።
የዚምባብዌ ፓርኮች እና የዱር አራዊት አስተዳደር ባለስልጣን ጉዳዩን ለቢቢሲ ቢያረጋግጥም ግን ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።
ልጁ ስለ ዱር እና በአስቸጋሪ ወቅቶችን የማሳለፍ ልምዱን ተጠቅሞ በህይወት ለመቆየት መቻሉን ሙሮምቤዲዚ ገልጸዋል።
ቲኖቴንዳ ከደረሰበት ችግር የተረፈው የዱር ፍራፍሬ በመብላት ነው። በተጨማሪም በወንዞች አቅራቢያ ያሉ ደረቅ መሬቶችን በመቆፈር ውሃ ማግኘቱን አስታውቀው ይህንንም ለድርቅ ተጋላጭ አካባቢ በመኖር የተማረው መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኒያሚንያሚ ማህበረሰብ አባላት ፍለጋ በመጀመር በየቀኑ ከበሮ እየደበደቡ ድምጹን በመስማት ወደ ቤቱ እንዲመለስ ምልክት ሊሰጡት ይሞክሩ እንደነበር ተነግሯል።
ልጁን ሊያገኙት የቻሉት ግን የፓርኩ ጠባቂዎች ነበሩ።
ቲኖቴንዳ በአምስተኛ ቀኑ የጠባቂዎቹን መኪና ድምጽ ሰምቶ ወደመኪናው መሮጡን የፓርላማዋ አባል ተናግሯል።
እንደ ዕድል ሆኖ ጠባቂዎቹ ሲመለሱ "አዲስ የሰው የእግር ዳና" በመመልከታቸው እስኪያገኙት ድረስ ፍለጋቸውን ቀጥለዋል።
"ምናልባት ይህ በበረሃ ከቆየ ከ5 ቀናት በኋላ የመገኘቱ የመጨረሻ ዕድሉ ሊሆን ይችላል" ብለዋል የፓርላማዋ አባል።
ፓርኩ ከአንድ ሺህ 470 ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ ስፋት ያለው ሲሆን የሜዳ አህያ፣ ዝሆኖች፣ ጉማሬዎች እና አንበሶች መኖሪያ ነው።
በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በርካቶች ልጁ ችግሩን ተቋቁሞ በህይወት በመቆየቱ አወድሰውታል
አንድ ሰው በኤክስ ላይ "ይህ ከሰው የመረዳት አቅም በላይ ነው" ሲል ጽፏል።
ሌላ ተጠቃሚ ደግሞ "ወደ ትምህርት ቤት ሲመለስ የሚናገረው አንድ ትልቅ ታሪክ ይኖረዋል" ሲል ጽፏል።