ትራምፕ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪያቸውን ከሥልጣን አንስተው ለተባበሩት መንግሥታት አምባሳደርነት በእጩነት አቀረቡ

የዩናይትድ ስቱትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪያቸውን ከኃላፊነታው አንስተው የተባበሩት መንግሥታት አምባሳደር እንዲሆኑ ማጨታቸውን አስታወቁ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ በጊዜያዊነት የብሔራዊ ደህንንት አማካሪነት ቦታውን ደርበው እንደሚሰሩ ጨምረው ተናግረዋል።

ባለፈው መጋቢት ወር የ'ዘ አትላንቲክ' መጽሔት ዋና አዘጋጅ ጄፍሪ ጎልድበርግ በስህተት በሲግናል የውይይት ቡድን ውስጥ ከከፍተኛ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ኃላፊዎች ጋር መካተቱን ከተሰማ በኋላ በብሔራዊ ደህንነት አማካሪው ላይ ትችቶች በዝተው ነበር።

ሐሙስ ዕለት በትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪያቸው መነሳትን ያስታወቁት ፕሬዝዳንቱ፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርክ ሩቢዮ የብሔራዊ ደህንንት አማካሪነት ቦታውን ደርበው እንደሚሰሩ ተገልጿል።

ዶናልድ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ "ማይክ ዋልዝን ለተባባሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር አድርጌ በእጩነት ሳቀርብ ትልቅ ደስታ ይሰማኛል" ብለዋል።

"ማይክ ዋልዝ የአገራችንን ፍላጎት በማስቀደም ጠንክሮ ሲሰራ የነበረ ነው። አዲስ በሚመደብበትም ቦታ ይህንኑ እንደሚያደርግ አውቃለሁ" ሲሉ አክለዋል።

ትራምፕ "በጋራ በመሆን አሜሪካን ብሎም ዓለምን ዳግም ደህንነቷ የተጠበቀች እንድሆን ያለመታከት እንፋለማለን" ብለዋል።

የብሔራዊ ደህንንት አማካሪው ማይክ ዋልዝ እና ምክትላቸው አሌክስ ዋንግ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረገው በየመን የሚፈጸም ጥቃትን ለመነጋገር በተከፈተ የሲግናል ቡድን ውስጥ በስህተት ጋዜጠኛ መካተቱን ተከትሎ በተነሳ ተቃውሞ ነው።

በዚህ የሲግናል ቡድን ውስጥ ማይክ ዋልዝ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴዝ እንዲሁም የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ የነበሩ ሲሆን፣ በየመን ስለሚፈጸም የአየር ጥቃት ውይይት እያደርጉ ነበር ተብሏል።

ጎልድበርግ ቡድኑን እንዲቀላቀል ያደረጉት የደኅንነት አማካሪው ማይክ ዋልዝ መሆናቸውን የገለፀ ሲሆን፣ በኋላ ላይ ስህተት መሥራታቸውን አምነዋል።

የቀድሞው የፍሎሪዳ ኮንግረስ አባል በትራምፕ የሁለተኛ የስልጣን ዘመን ዋይት ሐውስን በመልቀቅ የመጀመርያው ከፍተኛ ኃላፊ ሆነዋል።

ዋልዝ በኤክስ ገጻቸው ላይ ፕሬዝዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ያጋሩትን በማያያዝ አጭር መልዕክት አስፍረዋል።

"ለፕሬዝዳነት ትራምፕ እንዲሁም ለታላቁ ሕዝባችን አገልግሎት መስጠቴን በመቀጠሌ ኩራት ይሰማኛል።"

በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ትራምፕ የደህንነት አማካሪያቸውን ለተባባሩት መንግሥታት አምባሳደርነት ያጩት ከኃላፊነት መነሳታቸው በተሰማ በሰዓታት ጊዜ ውስጥ ነው።

ዋልዝ ከኃላፊነታቸው የተነሱት ባለፈው መጋቢት ወር በስህተት በሲግናል የውይይት ቡድን ውስጥ ጋዜጠኛ በማካተታቸው መሆኑን በርካታ ምንጮች ለሲቢኤስ ኒውስ አረጋግጠዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የብሔራዊ ደህንንት ምክር ቤቱን ባልደረቦች በአግባቡ መምራት አልቻሉም የሚል ቅሬታ መቅረቡም ተገልጿል።

እነዚህ ምንጮች አክለውም ትራምፕ ማይክ ዋልዝን ስለሚያከብሯቸው የተሻለ ቦታ መመደብ መፈለጋቸውን ተናግረዋል።

ይኹን አንጂ ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ግለሰቦች የትረምፕ አስተዳደር ዋልዝ አምባሳደር ሆነው እንዲሾሙ ለሴኔት ማሳመን ሊከብደው ይችላል።

ባለፈው መጋቢት ወር የ'ዘ አትላንቲክ' መጽሔት ዋና አዘጋጅ ጄፍሪ ጎልድበርግ በስህተት በሲግናል የውይይት ቡድን ውስጥ መካተቱን ከገለፀ በኋላ ትራምፕ እንዲሁም የአሜሪካ ደኅንነት ኃላፊ ክስተቱ የደኅንነት አደጋ የለውም ሲሉ ጉዳዩን ያጣጣሉ ሲሆን፣ ምሥጢራዊ ሰነድም አለመጋራቱን ተናግረው ነበር።

ይኹን እንጂ የተወሰኑ የዲሞክራት እና ሪፐብሊካን አባላት በርካታ እና የሕግ ባለሙያዎች ጥሰት ተፈጽሟል ሲሉ የጠሩት ክስተት ላይ ምርመራ እንዲካሄድ ሲወተውቱ ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ ለተባበሩት መንግሥታት አምባሳደርነት መጀመርያ በእጩነት ያቀረቧትን ኤሊሴ ስቴፋኒክን ሪፐብሊካን ከተቃወሙ በኋላ ቦታ ክፍት ሆኖ ቆይቶ ነበር።

ትራምፕ የብሔራዊ ደህንንት አማካሪነት ቦታውን ለውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደርበው መስጠታቸው በርካታ የመስርያ ቤቱ ባልደረቦችን አስገርሟል።

ሩቢዮ ከሔነሪ ኪሲንገር ወዲህ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪነትን እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስተርነት ቦታውን ደርበው የያዙ የመጀመርያው ሰው ሆነዋል።

አንዳንድ ሰዎች የአሜሪካ ልዩ ልዑክ በመሆን እያገለገሉ ያሉት እና በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል የሚካሄደው ጦርነት እንዲቆም እየሰሩ የሚገኙት ስቲቭ ዊትኮፍ ስልጣኑን ይረከባሉ ብለው ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ሌሎች ደግሞ ለትራምፕ ልዩ ልዑክ ሆነው እያገለገሉ ያሉት ሪክ ግሬኔል ካላቸው ረዥም ልምድ አንጻር እጩ ይሆናሉ ሲሉ ይናገራሉ።

ትራምፕ በመጀመርያው የስልጣን ዘመናቸው አራት የብሔራዊ ደህንነት አማካሪዎችን ቀያይረዋል።

የመጀመርያው አማካሪያቸው የነበሩት ማይክል ፍሊን በኃላፊነቱ ላይ የቆዩት ለሦስት ሳምንት ብቻ ነበር።