ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በመቶ ሺዎች ያስገጠሙት ማይክሮቺፕ በሰውነትዎ ውስጥ እንዲቀበር ይፈቅዳሉ?
ከስምንት ዓመት በፊት በገጠመው አደጋ ምክንያት ከትከሻው በታች ፓራላይዝድ ሆኗል።
ከወራት በፊት በተለቀቀ ቪድዮ ላይ ኖላንድ ከአእምሮው በሚተላለፍ ትዕዛዝ እየተመራ በበይረ መረብ ቼዝ ሲጫወት ይታያል።
እጁንም ሆነ እግሩን ማዘዝ አይችልም።
ሆኖም ግን የቼዝ መጫወቻዎቹን ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላው ያንቀሳቅሳል።
ከየትኛው ሥፍራ ወደየትኛው ሥፍራ ማንቀሳቀስ እንደሚፈልግ ሲያስብ፣ ጭንቅላቱ ውስጥ የተቀበረው ቺፕ መልዕክቱን ያነባል።
መልዕክቱ ወደ ኮምፒውተሩ ተልኮ ኖላንድ ያሰበውን ድርጊት ይፈጽማል።
በኒውሮቴክኖሎጂ ላይ የሚሠራው የኤለን መስክ ተቋም 'ኒውራሊንክ' በሰው ልጅ ጭንቅላት ውስጥ ቺፕ ሲቀብር ኖላንድ የመጀመሪያው ነው።
ኖላንድ የተገጠመለት ቺፕ ሳንቲም የሚያህል ነው። በአንጎሉ ውስጥ ያለውን የኒውሮን እንቅስቃሴ አንብቦ መልዕክቱን በራድዮ ሞገድ ያስተላልፋል።
ስለዚህ፣ ሰዎች መራመድ ሲያስቡ እንዲራመዱ ወይም ሌላም ያሰቡትን እንዲከውኑ ያስችላቸዋል።
ጭንቅላታችን ውስጥ ወደ 86 ቢሊዮን የሚጠጉ ኒውሮኖች አሉ። እነዚህ ነርቮች ሲናፕሲስ በተባለ ሕዋስ እርስ በእርሳቸው ይተሳሰራሉ።
ማሰብ ወይም መራመድ ስንፈልግ አንደኛው ኒውሮን ከሌላኛው ኒውሮን ጋር በከፍተኛ ፍጥረት መረጃ ይለዋወጣል።
ይህንን የመረጃ ልውውጥ በሰው ሠራሽ ቺፕ አማካኝነት ለማከናወን ጥናት እና ምርምሮች ቀጥለዋል።
ማይክሮቺፕ ወይም ቺፕ አነጋጋሪም አወዛጋቢም ከሆኑ የቴክኖሎጂ ዘርፎች አንዱ ነው።
በእጅ ቆዳ ሥር በሚቀበር ቺፕ ክፍያ መፈጸም እየተለመደ መጥቷል። ገበያ ሲወጡ ስልክ ወይም ካርድ ይዞ መውጣት የማያስፈልግበት ጊዜ እየመጣ ይመስላል።
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ቺፕ በሰው ሰውነት ውስጥ የተቀበረው በአውሮፓውያኑ 1998 ነበር።
በዩናይትድ ኪንግደም እና በአውሮፓ የሚኖሩ 4 ሺህ ሰዎችን በማነጋገር ከሦስት ዓመት በፊት የተሠራ ጥናት እንደሚጠቁመው፣ 51 በመቶው ቺፕ በሰውነታቸው ውስጥ እንዲቀበር ይፈቅዳሉ።
በሕክምና እና በክፍያ ሥርዓት ቺፕን በመምረጥ ረገድ በቻይና፣ በጃፓን እና በደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ ፍላጎት ተስተውሏል።
ከሰዎች ባሻገር የቤት እንሰሳትም ሲጠፉ ለማግኘት ቺፕ እየተገጠመላቸው ነው።
እንደ ስዊድን እና ኔዘርላንድስ ባሉ አገራት ባቡር ለመሳፈር፣ ምግብ ለመግዛት እና ወደ ቢሮ ለመግባት ቺፕ መጠቀም የተለመደ ሆኗል።
አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ቺፕ ያላስቀበሩ ሰዎችን አንቀጥርም ማለታቸውን ተከትሎ፣ ቺፕን አስገዳጅ ማድረግን በሕግ ያገዱ የአሜሪካ ግዛቶች አሉ።
ከጤና እንዲሁም ከግል መረጃ ጥበቃ አንጻር ማይክሮቺፕን የተመለከቱ ጥያቄዎች ይነሳሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ቺፕን የተመለከቱ የሴራ ትንታኔዎች ተበራክተዋል።
ማይክሮቺፕ ምንድን ነው? ለምን አገልግሎት ይውላል? ለሰው ልጆች ስጋት ነው? ዓለምንስ እንዴት ይለውጣል? ለሚሉት ጥያቄዎች ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጠን የማይንድ ፕሌክስ ሥራ አስኪያጅ እና የአይኮግ ላብስ መሥራች ኅሩይ ፀጋዬን ጠይቀናል።
ማይክሮቺፕ ምንድን ነው?
እስካሁን ድረስ በዓለም ላይ "ወደ 200 ሺህ ሰዎች" ሰውነታቸው ውስጥ ማይክሮቺፕ እንዳስገቡ ኅሩይ ይናገራል።
የቺፕ ሁለት ዓይነቶችን እንዲህ ያስረዳል።
የመጀመሪያው ዓይነት በእንግሊዘኛው radio-frequency identification chips (RFID) የሚባለው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በእንግሊዘኛው near field communication chips (NFC) ናቸው።
አንደኛው፣ ገመድ አልባ እና በራድዮ ሞገድ መልዕክት የሚያስተላልፍ ቺፕ ነው። መጠኑ የሩዝ ፍሬ ያህላል። ለእያንዳንዱ ሰው መለያ ቁጥር ይሰጣል።
ይሄ ቺፕ የጤና መረጃ ይመዘግባል። የልብ ምት፣ የሰውነት ሙቀት አልያም የሆርሞን መጠን ተመዝግቦ መረጃው በራድዮ ሞገድ ይተላለፋል።
ቺፑ ከሰውነት ውስጥ ወጥቶ የያዘው መረጃ ወደ ኮምፒውተር ሊገለበጥም ይችላል።
"ይሄ በሕክምናው ውስጥ የቆየ ነገር ነው" ይላል ባለሙያው።
ሁለተኛው ዓይነት ቺፕ በተለይም ከጭንቅላት ኒውሮኖች ጫፍ ጋር ይገናኛል። መጠኑም ሳንቲም የሚያክል ነው። በአቅራቢያው ካለ ኮምፒውተር ጋር መረጃ ሊለዋወጥ ይችላል።
ኅሩይ እንደሚለው፣ ማይክሮቺፕ ባለፉት ዓመታት ከሕክምናው ዘርፍ ወጥቶ ኑሮን ቀላል ለማድረግ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።
ጣት ጫፍ ላይ በተቀበረ ቺፕ ክፍያ መፈጸምን እንደ ምሳሌ ይጠቅሳል።
"ስልክ በጣት አሻራ እንደሚከፈተው በጣት ቆዳ ሥር በተቀበረ ቺፕ ክፍያ መፈጸም ይቻላል። በር፣ ካዝና ወይም መኪና ለመክፈትም ይውላል። ጀርመን ውስጥ ብቻ 5 ሺህ ሰዎች ለክፍያ ማይክሮቺፕ አስቀብረዋል" ይላል።
ማይክሮቺፕ የጤና ሁኔታን መዝግቦ ወደ መረጃ ቋት ካሻገረ፣ የክፍያ ሥርዓት ውስጥ ከገባ፣ ለምን የሰዎችን ሰውነት ለማዘዝ አይውልም? በሚል አዳዲስ ጥናቶች እየተደረጉ ነው።
ጭንቅላት ውስጥ በሚቀበሩ ማይክሮቺፖች እግርን እና እጅን ማዘዝ የዚህ ምርምር አካል ነው።
ማይክሮቺፕ እና የሴራ ትንታኔዎች
የትኛውም አዲስ ቴክኖሎጂ ሲመጣ እንደሚሆነው ስለ ማይክሮቺፕም ብዙ የሴራ ትንታኔዎች ተሰምተዋል።
በጉልህ የሚታወሰው ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን የተመለከተው ነው።
ወረርሽኙ 'የተለቀቀው' በክትባት ሰበብ በሰዎች ሰውነት ውስጥ ቺፕ ለመቅበር እና በቺፑ አማካኝነት ክትትል ለማድረግ ነው የሚል ሐሰተኛ መረጃ መሠራጨቱ አይዘነጋም።
ከዚህ ጀርባ ያለው ደግሞ የማይክሮሶፍት አጋር መሥራቹ ቢልየነር ቢል ጌትስ ነው ተብሎ በስፋት ይወራ ነበር።
የማይክሮቺፕ ባለቤቶች ማይክሮቺፕ ያስቀበሩ ሰዎችን ይቆጣጠራሉ፣ በማይክሮቺፕ አማካኝነት መንግሥት ይከታተለናል፣ በማይክሮቺፕ አማካይነት 'ከሌላ ዓለም የመጡ ፍጡራን' ከሰው ጋር ተዳቅለው ዓለምን ለመውረስ መረጃ እየሰበሰቡ ነው፣ ማይክሮቺፕ 'የዲያቢሎስ' ሥራ ነው የሚሉ እና ሌሎችም ብዙ የሴራ ትንታኔዎች ይሰማሉ።
እነዚህ ግን ሳይንሳዊ መሠረት እንደሌላቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ኅሩይ፣ ቺፖች "ካንሰር ወይም ኢንፌክሽን ሊያመጡ ይችላሉ" የሚለውን መላ ምት ይጠቅሳል።
በሌላ በኩል ቺፖች ድንገት በመረጃ መዝባሪዎች እጅ ቢገቡ ግላዊ መረጃዎች ሊሰረቁ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው። የቴክኖሎጂ ደኅንነት ባለሙያዎች ስጋተቸውን ሲገልጹም ይደመጣል።
"ከጤና ጋር በተያያዘ የሚነሳው ጥያቄ ሚዛን ይደፋል። ቺፖችን በተሻለ ሲልከን ሸፍኖ ለመሥራት ጥናቶች እየተደረጉም ነው" ይላል።
ስለ ማይክሮቺፕ ከሚነገሩ ልቦለዳዊ የሚመስሉ ዕሳቤዎች አንዱ "የሰዎችን ዲጂታል ማንነት ማስቀረት ያስችላል" የሚለው አንዱ እንደሆነ ባለሙያው ይናገራል።
ማይክሮቺፕ ጭንቅላት ውስጥ ከተቀበረ የሰዎችን ስሜት እና ትውስታ ወደ ኮምፒውተር ማስተላለፍ ይቻላል።
"የሚመዘገበው መረጃ 24 ሰዓት ስለሚቀመጥ ግለሰቡ ሲሞት ዲጂታል ማንነቱን ማስቀረት ይቻላል። ከግለሰቡ የተመዘገበ መረጃ ተነስቶ የዚያን ሰው ዲጂታል ማንነት መገንባትም ይቻላል" ሲል ባለሙያው ያስረዳል።
ከዚህ ጋር የሚያያዘው ሌላው ዕሳቤ ደግሞ፣ አእምሮ የሚሠራበትን ምሥጢር ማወቅ ተችሎ ስለ ንቃተ ሕሊና ያለውን ግንዛቤ ሲጨምር "የሰዎችን ጭንቅላት ወስዶ ሮቦት ላይ መጫን ይቻላል" የሚለው ነው።
በዚህ መንገድ "የሰዎችን አካል በማስመሰል (cloning) የሚሠሩ ግዑዝ አካላት ላይ ከሰዎች ጭንቅላት የተገኘ መረጃን መጫን ይቻላል። ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያለን ማንነት እና መረጃን መጫን ማለት ነው" ሲል ኅሩይ ያብራራል።
የሰው ልጅን ተፈጥሯዊ አቅም በቴክኖሎጂ በመታገዝ የላቀ ማድረግ (transhumanism) ከማይክሮቺፕ ጋር ተያይዞ ይነሳል።
በማይክሮቺፕ ታግዞ በማሰብ ብቻ እንቅስቃሴን መከወን ከተቻለ፣ ለምን የሰዎች ሰውነት ከተፈጥሯዊ አቅሙ የላቀ ድርጊት እንዲፈጽም ማድረግ አይቻልም?
ይህ "ተፈጥሯዊ የሰውነት ገደብን መሻገር ማለት ነው። ለምሳሌ በጣም ፈጣን አትሌት መፍጠር ይቻላል። ሰውነት ውስጥ የሚገባውን እና የሚወጣውን የትንፋሽ መጠን ከተፈጥሯዊው መጠን በላይ በመጨመር ሰዎች ሳይተነፍሱ የሚቆዩበትን ጊዜ መጨመር ወይም ዓይን የሚያይበትን ርቅተ መጨመር ሊሆን ይችላል" ሲል ኅሩይ በምሳሌ ያስረዳል።
በእርግጥ የሰዎችን ተፈጥሯዊ አሠራር 'ማሻሻል' የሚለውን ሐሳብ ከሃይማኖት፣ ከሥነ ምግባር እና ከሞራል አንጻር የሚነቅፉት አሉ።
እንደ ማይክሮቺፕ ያሉ ቴክኖሎጂዎች ተደራሽነታቸው ለጥቂት ሃብታሞች ሆኖ አሁን ዓለም ላይ ያለውን የእኩልነት እጦት ያሰፋዋል የሚለውን ፍርሃት ኅሩይ ሳይጠቅስ አያልፍም።
"90 በመቶ የዓለም ሃብት በ10 በመቶ ሃብታሞች ተይዞ ባለበት ሁኔታ እንዲሁም ዴሞክራሲ እና ምክንያታዊ ዕሳቤ ባልጎለበበት ሁኔታ ውስጥ ቴክኖሎጂው በቅርብ ዓመታት ውስጥ ለገበያ ሲቀርብ ተጠቃሚዎቹ ሃብታሞች ይሆናሉ።"
ማይክሮቺፕ ሰዎችን ይጎዳል?
ኅሩይ እንደሚለው፣ ከማይክሮቺፕ ጋር በተያያዘ ከሚነሱ ጥያቄዎች አንዱ ድንገት ኢንተርኔት ቢቋረጥ ሰዎች ምን ሊገጥማቸው ይችላል? የሚለው ነው።
በሌላ በኩል ለከፍተኛ ኤሌክትሮማግኔቲክ ፐልስ የመጋለጥን ስጋት ይጠቀሳል። በማይክሮቺፕ ላይ ብዙ ጥናቶች የሚደረጉትም ለዚህ ነው።
ስለዚህ በአንድ ጊዜ ማይክሮቺፕ በሰውነት ውስጥ ከመቅበር ቀስ በቀስ ጥናት ቢደረግበት የሚል ምክር አላቸው።
ኅሩይ በበኩሉ ማይክሮቺፕ በአንድ ጊዜ በሰዎች ላይ የሚጫን ሳይሆን ቀስ በቀስ መደረግ ያለበት ነው ብሎ ያምናል።
"ለንግድ መሯሯጥ ሳይሆን ቀስ በቀስ መደግ ያለበት ነው። የሰው ልጅ በልኅቀት መድረስ የሚችለበት ድረስ ገና አልደረሰም። የሰው ልጅ አብሮ መኖርን አልተማረም። አሁንም ጦርነት አለ። ስለዚህም የሳይንስ ማኅበረሰብን ስጋት እጋራለሁ" ይላል።