ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል ወደ ጋዛ ሰብአዊ እርዳታ የማስገባት ሕጋዊ ግዴታ እንዳለባት ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ገለጸ
እስራኤል ወደ ጋዛ ሰርጥ ሰብአዊ እርዳታ እንዲገባ ማመቻቸት ግዴታዋ እንደሆነ ዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት አስታወቀ።
እስራኤል በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት በተባበሩት መንግሥታት ተቋማት በኩል ለፍልስጤማውያን ሰብአዊ እርዳታ እንዲገባ መንገድ መክፈት እንዳለባት ተገልጿል።
እስራኤል፤ የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤማውያን ተፈናቃዮች ተቋም (Unrwa) "ገለልተኛ አይደለም" በሚል ላነሳችው ክስ ማስረጃ እንዳላቀረበች ተመድ አክሏል።
ከተቋሙ አባላት አብዛኞቹ የሐማስ ወይም የሌላ ታጣቂ ቡድን አባላት ናቸው ብላ እስራኤል ብትከስም ማስረጃ አላቀረበችም።
የተባበሩት መንግሥታትን ውሳኔ እስራኤል ታከብራለች ብለው እንደሚያምኑ የተመድ ከፍተኛ ኃላፊ ተናግረዋል።
የዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት ውሳኔ "ፖለቲካዊ ነው" በማለት የምትተቸው እስራኤል፤ እንደማትቀበለው አስታውቃለች። ከተመድ የፍልስጤማውያን ተፈናቃዮች ተቋም ጋር በጋራ እንደማትሠራም ገልጻለች።
ዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ አሳሪ ባይሆንም ከዲፕሎማሲ እና ከሞራል አንጻር ከፍተኛ ዋጋ አለው።
ከዚህ ቀደም በተካሄደው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እስራኤል ግዛቶችን በግዳጅ ስለመያዟ እና እንደ ተመድ አባል አገር ስላሉባት ግዴታዎች ዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት አስተያየት እንዲሰጥ ተጠይቋል።
እስራኤል የተመድ ተቋማት በዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌም የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አስቁማለች።
ዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት በበኩሉ እስራኤል ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ ለፍልስጤማውያን እንዲደርስ መፍቀድ ግዴታዋ እንደሆነ ገልጿል።
እስራኤል ወደ ጋዛ የሚገባው ሰብአዊ እርዳታ ላይ ከፍተኛ ገደብ ጥላለች። ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰብአዊ እርዳታ ከነጭራሹ የማይገባባቸው ወቅቶችም ነበሩ።
በጋዛ ከሚኖሩ 2.1 ሚሊዮን ሰዎች መካከል ከ640,000 በላይ የሚሆኑት ለከፋ ረሃብ መጋለጣቸውን ተመድ አስታውቋል።
ተመድ ድጋፍ የሚሰጣቸው ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች "በጋዛ ሰው ሠራሽ ረሃብ ተከስቷል" ብለዋል።
እስራኤል በቂ ምግብ እያቀረበች እንደሆነ በመግለጽ ረሃብ መኖሩን አስተባብላለች።
የዓለም አቀፍ የፍትሕ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዩዊጂ አይዋሳዋ የተላለፈውን ውሳኔ አቅርበዋል።
11 ዓለም አቀፍ ዳኞች ያሉበት ቡድን ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት፤ እስራኤል ግዛቶችን በግዳጅ እንደመያዟ ለዓለም አቀፍ ሰብአዊ ሕግ መገዛት ግዴታዋ ነው።
ዳኛው "የመጀመሪያው ግዴታ በወረራ በተያዙ የፍልስጤም አካባቢዎች ለእለት ከእለት ሕይወት የሚሆን ምግብ፣ ውሃ፣ ልብስ፣ መጠለያ፣ ነዳጅ፣ ሕክምና እና ሌሎችም አገልግሎቶች ማቅረብ ነው" ብለዋል።
ሁለተኛው ግዴታ ደግሞ "በወረራ በተያዙ የፍልስጤም አካባቢዎች ለሚኖሩ ፍልስጤማውያን በቂ የሆነ ሰብአዊ እርዳታ ማቅረብ" ነው።
በወረራ በተያዙ የፍልስጤም አካባቢዎች የሰዎችን እንቅስቃሴ አለመገደብ እና ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያ አለመጠቀም የእስራኤል ግዴታዎች ናቸው።
"እስራኤል በበጎ ፈቃደኛነት የፍልስጤማውያን ተፈናቃዮች ተቋምን ጨምሮ ከሌሎችም የተመድ አጋሮች ጋር የመተባበር እና የተመድን ድንጋጌዎች ማክበር ግዴታዋ ነው" ሲሉ የዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዩዊጂ አይዋሳዋ ተናግረዋል።
በተመድ መርሕ መሠረት የድርጅቱን አመራሮችን ያለመከሰስ መብት ማክበርም የእስራኤል ግዴታ ነው ብለዋል።
"የተመድ ቢሮዎችን ጥሶ ያለመግባት፣ የተመድ መገልገያዎችን ደኅንነት የመጠበቅ እንዲሁም የድርጅቱን እንቅስቃሴ አለማስተጓጎል" እስራኤል ከተጣሉባት ግዴታዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
በጄኔቫ የተላለፈውን ውሳኔ በተመለከተ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ "በጣም ጠቃሚ ውሳኔ ነው። እስራኤል ውሳኔውን ትተገብራለች ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል።
ተመድ ወደ ጋዛ የሚገባው ሰብአዊ እርዳታ እንዲጨምር እየሠራ ባለበት በዚህ ወቅት ውሳኔው መተላለፉ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አክለዋል።
የተመድ የፍልስጤማውያን ተፈናቃዮች ተቋም ዋና ኃላፊ ፊሊፔ ላዛሪኒ ውሳኔው "አሻሚ አይደለም" ብለዋል።
"በግብፅ እና በዮርዳኖስ ከፍተኛ መጠን ያለው እርዳታ ተከማችቷል። ተቋማችን እርዳታውን በጋዛ ለማከፋፈል የሰው ኃይልም ብቃትም አለው። እርዳታው በረሃብ እየተቀጣ ያለውን ሕዝብ ሕይወት ይታደጋል" ሲሉም በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።
ተመድ ወደ ጋዛ እርዳታ በማስገባት "አስከፊውን ሁኔታ ለመለወጥ" እየሞከረ ባለበት ወቅት ዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት ውሳኔ ማሳለፉ ያለውን ሚናም ገልጸዋል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "በዓለም አቀፍ ሕግ ስም እስራኤል ላይ ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደር እየተሞከረ ነው" ሲል መግለጫ አውጥቷል።
እስራኤል ግዴታዋን እየተወጣች እንደሆነ፤ "በአሸባሪዎች ከተሞላ ድርጅት ሠራተኞች ጋር ለማበር" ግን እንደማትፈቅድ መግለጫው ያትታል።
ሐማስ ከሁለት ዓመት በፊት ባደረሰው ጥቃት የተመድ የፍልስጤማውያን ተፈናቃዮች ተቋም ሠራተኞች ተሳትፈዋል ብላ እስራኤል ትከሳለች።
ተመድ አምና ባደረገው ምርመራ በጥቃቱ ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩ ዘጠኝ የጋዛ ሠራተኞቹን አባርሯል።
የዓለም አቀፍ የፍትሕ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዩዊጂ አይዋሳዋ ግን "ተቋሙ ገለልተኛ አይደለም ለሚለው ክስ ማስረጃ አላገኘንም" ብለዋል።
ተቋሙ በእስራኤል ክልከላ ከተጣለበት በኋላ ፍልስጤማውያን የተቋሙ አባላት በትምህርት፣ በጤና እና በሌሎችም ዘርፎች በጋዛ፣ በዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌም የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን ይደግፋሉ።
ሆኖም ግን ተቋሙ ወደ ጋዛ ሰብአዊ እርዳታ እንዳያስገባ ታግዷል። እስራኤል ለተቋሙ ሠራተኞች ቪዛ መስጠትም አቁማለች።
ተቋሙ እንዳለው ቢያንስ 309 ሠራተኞቹ እና 72 ድጋፍ የሚሰጡት ባለሙያዎች በጦርነቱ ተገድለዋል።
እስራኤል በጋዛ በከፈተችው ጥቃት ቢያንስ 68,229 ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተዘግቧል።
ዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ በተመለከተ የፍልስጤም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "እስራኤል ሕገ ወጥ ድርጊቷን ማቆም እንዳለባት እና አገራትም እስራኤል ግዴታዎችን እንድትወጣ ማድረግ እንዳለባቸው በግልጽ የሚያሳይ ነው" ብሏል።
"እስራኤል በተመድ የፍልስጤማውያን ተፈናቃዮች ተቋም ላይ የጣለችውን ሕገ ወጥ ክልከላ ማንሳት አለባት። ለዚህ ተቋም እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ፍልስጤም ጥሪ አቅርባለች። ሰብአዊ እርዳታ በነጻነት እና ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲሰጡ እስራኤል መፍቀድም አለባት" ሲልም አክሏል።