እስራኤል በጋዛ "እርዳታን እንደ ጦር መሳሪያ" መጠቀም እንድታቆም የሰብዓዊ እርዳታ ቡድኖች ጠየቁ

ከ100 በላይ ድርጅቶች በጋዛ ያለው ረሃብ "እየተባባሰ በሄደበት ወቅት" እስራኤል "እርዳታን እንደ ጦር መሳሪያ" መጠቀም እንድታቆም የሚጠይቅ ደብዳቤ ተፈራረሙ።

ኦክስፋም እና ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድንን ጨምሮ የሰብዓዊ እርዳታ ቡድኖች ጥብቅ የእስራኤል ሕግጋትን እስካላከበሩ ድረስ እርዳታ ለማከፋፈል "ፈቃድ እንደሌላቸው" በተደጋጋሚ እየተነገራቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ቡድኖች የእስራኤልን መንግሥት "የሚቃወሙ" ከሆነ ወይም ፍልስጤማውያን ሠራተኞቻቸውን ዝርዝር መረጃ ካልሰጡ ሊታገዱ እንደሚችሉ እንደተነገራቸው ደብዳቤው ያትታል።

እስራኤል በእርዳታ ላይ ገደቦች ተጥለዋል የሚለውን ውንጀላ በመቃወም በመጋቢት ወር የወጣው ሕግ የእርዳታ ስራ ከእስራኤል "ብሔራዊ ጥቅም" ጋር በተጣጣመ መልኩ መከናወኑን ያረጋግጣል ብላለች።

ቡድኖቹ የተፈራረሙት ደብዳቤ ከመጋቢት 2 ጀምሮ አብዛኞቹ ዋና ዋና ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አንድ የጭነት መኪና ሕይወት አድን እርዳታዎችን ማድረስ እንዳልቻሉ ይገልጻል።

አዲሱን ሕግ በመጥቀስም የእስራኤል ባለስልጣናት "በርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሕይወት አድን እርዳታዎችን ለማስገባት ያቀረቡትን ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል" ሲሉ ተናግረዋል።

በሐምሌ ወር ብቻ ከ60 በላይ ጥያቄዎች ውድቅ ተደርገዋል።

የእርዳታ ቡድኖች እርዳታ ማድረስ ባለመቻላቸው "ሆስፒታሎች ያለ መሠረታዊ አቅርቦቶች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ እና አዛውንቶች በረሃብ እና መከላከል በሚቻል በሽታ እንዲሞቱ ሆነዋል" ሲል መግለጫው ገልጿል።

አኔራ በመባል የሚታወቀው የአሜሪካ እርዳታ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ሼን ካሮል "አኔራ ወደ ጋዛ ለመግባት ዝግጁ የሆኑ ከ7 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመቱ የሕይወት አድን ቁሳቁሶች አሉት። ይህም 744 ቶን ሩዝ የሚያካትት ሲሆን ስድስት ሚሊዮን ሰዎችን ለመመገብ በቂ ነው። ነገር ግን በአሽዶድ በኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ታግዷል" ብለዋል።

በመጋቢት ወር የወጣው አዲሱ መመሪያ የእርዳታ ቡድኖች እስራኤል በምትቆጣጠራቸው አካባቢዎች ለመንቀሳቀስ እንዴት መመዝገብ እንዳለባቸው፣ ማመልከቻዎቻቸው እንዴት ውድቅ እንደሚሆኑ ወይም እንደሚሰረዙ የሚገልፁ ድንጋጌዎችን ይዟል።

የእስራኤል ባለስልጣናት አንድ ቡድን እስራኤል ዲሞክራሲያዊ መሆኗን የሚክድ ወይም በአገሪቱ ላይ "ሕጋዊ እውቅናን የሚነፍጉ ዘመቻዎችን የሚያበረታታ" እንደሆነ ካሰቡ ምዝገባቸው ውድቅ ሊደረግ ይችላል።

የእስራኤል የዲያስፖራ ሚኒስትር አሚቻይ ቺክሊ ለፈረንሳይ የዜና ወኪል "እንደ አለመታደል ሆኖ፣ ብዙ የእርዳታ ድርጅቶች ለጠላት እና አንዳንዴም ለአመጽ ተግባራት ሽፋን ሆነው ያገለግላሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

ቺክሊ አክለውም "ከጠላት ወይም ከአመጽ እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት የሌላቸው እና ግንኙነትን ከማቀብ እንቅስቃሴ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ድርጅቶች እንዲሰሩ ፈቃድ ይሰጣቸዋል።"

ቡሽራ ካሊዲ የኦክስፋም ፖሊሲ ኃላፊ እስራኤል ከ2.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዳይገባ ውድቅ አድርጋለች ብለዋል።

አክለውም "ይህ የምዝገባ ሂደት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የመስራት እና የመናገር ነጻነታቸውን ዋጋ ሊያስከፍላቸው እንደሚችል ያሳያል።"

ማስጠንቀቂያው የመጣው እስራኤል የጋዛ ከተማን ለመቆጣጣር ላስቀመጠችው ዕቅድ የቦምብ ድብደባዋን አጠናክራ በቀጠለችበት ወቅት ነው።

እስራኤል "ከጦርነት ቀጣና ውጪ" ለሚገኙ ሰላማዊ ሕዝቦች ሰብዓዊ እርዳታ እንደምትሰጥ ገልጻ፣ ነገር ግን እርዳታው በእስራኤል እና በዩናይትድ ስቴትስ በሚደገፈው የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን (GHF) በኩል እንደሚደርስ አስታውቃለች።

እስራኤል ሐማስ የሚሰርቀውን እርዳታን ለማስቆም ይህ አዲስ አሰራር አስፈላጊ ነው ስትል ሐማስ በበኩሉ ውንጀላውን ውድቅ አድርጎታል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከግንቦት ወር ጀምሮ 859 ፍልስጤማውያን ፋውንዴሽኑ የእርዳታ ማከፋፈያ ጣቢያዎች አቅራቢያ እንደተገደሉ ገልጿል።

በጋራ መግለጫው በጋዛ የኤምኤስኤፍ የድንገተኛ አደጋ አስተባባሪ የሆኑት አይቶር ዛባልጎግኤዞካ እንዳሉት "ወታደራዊ የምግብ ማከፋፈያ ስርዓት ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሟል" ብለዋል።

የኤምኤስኤፍ ዋና ፀሃፊ ክሪስ ሎክየር ለቢቢሲ እንደተናገሩት ፋውንዴሽኑ "የሞት ወጥመድ" ነው ሲሉ በጋዛ ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ "በቀጭን ክር ላይ የተንጠለጠለ ነው" ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ግጭቱ ከጀመረ ወዲህ በጋዛ ያለው ረሃብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስጠንቅቋል።

በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በእስራኤል ጥቃት እስካሁን 61,722 ፍልስጤማውያንን ተገድለዋል።

አክሎም 106 ሕጻናትን ጨምሮ 235 ሰዎች በረሃብ እና በተመጣጠነ ምግብ እጥረት መሞታቸውንም አስታውቋል።