ሉዊስ ኤንሪኬ እና ፒኤስጂ ታሪክ የሠሩበት አስደናቂው የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ

የፓሪ ሳን ዠርማ አሰልጣን ሉዊስ ኤንሪኬ በደስታ እንባ ተጠምቀው በታዩበት ምሽት የፈረንሳዩ ክለብ የጣሊያኑን ኢንተር በመርታት የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ባለቤት ሆኗል።

በጀርመኗ ሚዩኒክ በተካሄደው ፍልሚያ ፒኤስጂ ኢንተር ሚላንን በአስደናቂ ሁኔታ 5 ለምንም በመርታት ነው ባለድል የሆነው።

ታዳጊው ዴዚሬ ዱዌ በፍፃሜው ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር በአውሮፓ መድረክ ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች መሆኑን አስመስክሯል።

ሉዊስ ኤንሪኬ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ከሁለት ቡድኖች ጋር በማንሳት በታሪክ ስድስተኛው አሰልጣኝ ሆነዋል። አሰልጣኙ ከ10 ዓመት በፊት ከባርሴሎና ጋር የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ እንደነበሩ አይዘነጋም።

ፒኤስጂ ጨዋታውን ሙሉ በሙለ በሚባል ደረጃ ተቆጣጥሮ ባመሸበት ጨዋታ የጣሊያኑ ኢንተር ሚላን ላይ 5 ጎሎች አስቆጥሯል።

የፓሪሱ ክለብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ባለድል ሲሆን በ2019 በአጥንት ካንሰር ምክንያት የ9 ዓመት ሴት ልጃቸውን ያጡት ሉዊስ ኤንሪኬ ስሜታቸውን በደስታ እና በእንባ ሲገልፁ አምሽተዋል።

አሰልጣኙ ከባርሴሎና ጋር የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ባነሱበት ወቅት ልጃቸው ዛና በካምፕ ኑ ሜዳ የባርሳን ባንዲራ እንድትተክል አድርገው ነበር። ኤንሪኬ ለልጃቸው መታሰቢያ እንዲሆን በፒኤስጂ ሜዳ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንደሚፈልጉ ተናግረው ያውቃሉ።

ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ ከልጃቸው ጋር የፒኤስጂን ማሊያ ሲተክሉ የሚያሳይ ፎቶ ያለበት ካናቴራ አድርገው ደስታቸውን ሲገልፁ ታይተዋል። የክለቡ ደጋፊዎችም ተመሳሳይ ፎቶ ያለበት ግዙፍ 'ባነር' ለክብራቸው ሰቅለዋል።

"በጣም ደስተኛ ነኝ። ደጋፊዎቹ ለኔና ለቤተሰቦቼ ያደረጉት ነገር ልብ የሚነካ ነው። ስለልጄ ሁሌም አስባለሁ" ብለዋል ኤንሪኬ።

"ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ ከባድ የሚባሉ ዋንጫዎችን ማሸነፍ እፈልጋለሁ ብዬ ነበር። ፒኤስጂ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ በልቶ አያውቅም። ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ይህን ያደረግነው። ተጫዋቾችና ደጋፊዎች ደስ ማሰኘት ትልቅ ነገር ነው።"

በባየር ሙኒክ ስታድየም የተደረገው ፍፃሜ የ19 ዓመቱ ዴዚሬ ዱዌ በአውሮፓ መድረክ ስሙን የተከለበት ሆኖ አምሽቷል።

ባለፈው ጥቅምት በሊጉ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ከአርሰናል ጋር በነበረው ጨዋታ 64 ደቂቃዎችን ብቻ ነበር የተጫወተው። በወቅቱ አርሰናል ፒኤስጂን 2-0 መርታት ችሏል።

ዱዌ በ12ኛው ደቂቃ የመጀመሪያዋን ጎሎ ለአሽራፍ ሐኪሚ አመቻችቶ ከማቀበል ባለፈ ከ8 ደቂቃዎች በኋላ ለቡድኑ ሁለተኛውን ጎሎ አስቆጥሯል። በ63ኛው ደቂቃ ደግሞ ለፒኤስጂ ሶስተኛ ጎል ከመረብ በማገናኘት የምሽቱ ኮከብ መሆን ችሏል።

ተጫዋቹ ወደፊት በአውሮፓ መድረክ ትልቅ ስም ከሚይዙ ተጫዋቾች መካከል እንደሚሆን ተንታኞች ሲተንብዩ ተሰምተዋል።

በቅዳሜ ምሽቱ ጨዋታ ወቅት ዕድሜ 19 ዓመት ከ362 ቀናት የነበረው ዱዌ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ሁለት ጎሎች ያስቆጠረ በዕድሜ ትንሹ ተጫዋች ሆኗል።

ምንም እንኳ ፒኤስጂ በጥቅምት ወር በአርሰናል ቢረታም ማንቸስተር ሰቲን፤ ሊቨርፑል በጥሎ ማለፍ በማሸነፍ፤ አስተን ቪላን በሩብ ፍፃሜ እንዲሁም አርሰናልን በግማሽ ፍፃሜው በመርታት ነው ለፍፃሜው የደረሰው።

"አማፂያኑ" የፒኤስጂ ደጋፈዎች በሙኒክ ስታድየም ከጨዋታ ጅማሬ እስከ ፍፃሜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በጭፈራ እና በጭስ ታጅበው ቡድናቸውን ሲደግፉ አምሽተዋል።

የጣሊያኑ ክለብ ኢንተር ሚላን ኳስ መቆጣጠር እና ያሰበውን ዕቅድ መተግበር ተስኖት ታይቷል። በወጣቶች የተሞላው የፒኤስጂ አማካይ መስመር ኢንተርን አላፈናፍን ብሎ አምሽቷል።

ዱዌ ተቀይሮ ከወጣ በኋላ ክቪቻ ክቫርትስኬሊያ እና ተቀይሮ የገባው የ19 ዓመቱ ሴኒ ማዩላ ሁለት ጎሎችን በማከል ለፒኤስጂ ፍፁም ድል አቆናፅፈዋል።