ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር አብዛኛዎቹን የቪኦኤ ሠራተኞች ማባረር ጀመረ
የፕሬዝዳንት ዶናልድ አስተዳደር በአሜሪካ ፌዴራል መንግሥት የሚደገፈውን መገናኛ ብዙሃን የአሜሪካ ድምጽ (ቪኦኤ) 500 ገደማ ሠራተኞችን አባረረ።
ይህ ውሳኔ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "አክራሪ" በማለት የሚገልጹትን ቪኦኤን፤ ለመዝጋት እየወሰዷቸው ካሉ ተከታታይ እርምጃዎች አንዱ ነው።
የቪኦኤ እናት ኩባንያው ጊዜያዊ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ካሪ ሌክ፤ ውሳኔው "የፌዴራል ቢሮክራሲን ለመቀነስ፣ የኤጀንሲውን አገልግሎትን ለማሻሻል እና የአሜሪካ ህዝብ በድካሙ ያገኘውን ገንዘብ በይበልጥ ለማዳን ይረዳል" ብለዋል።
የመገናኛ ብዙሃኑን ሠራተኞችን የሚወክል አንድ ህብረት ለአሜሪካው ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በሰጠው መግለጫ እርምጃውን "ህገ ወጥ" ሲል ጠርቶታል።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የናዚ ፕሮፓጋንዳን ለመቋቋም በሚል የተመሰረተው ቪኦኤ፤ ትልቅ ዓለም አቀፍ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን አሰራጭ ድርጅት ሆኗል።.
የቪኦኤ እናት ኩባንያ የሆነው 'ኤጀንሲ ፎር ግሎባል ሚዲያ' በአጠቃላይ 532 የስራ መደቦች እንደሚዘጉ አስታውቋል።
በዚህ የተነሳ ከሚባረሩት ውስጥ አብዛኛዎቹ የቪኦኤ ሰራተኞች እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከሰራተኛ ቅነሳው በኋላ መገናኛ ብዙሃኑ 108 ሠራተኞች ብቻ እንደሚኖሩት ለፍርድ ቤት በቀረበ የክስ መዝገብ ላይ ተጠቅሷል።
ጊዜያዊ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ሌክ የ639 ሠራተኞች የስራ ውል እንደሚቋረጥ ሰኔ ላይ አስታውቀው ነበር። ኋላ ላይ ግን ውሳኔውን ለማስፈጸም በሚከናወኑ ወረቀት ነክ ስራዎች ላይ በተፈጠረ ስህተት ምክንያት ይህ ማስጠንቀቂያ ተሰርዞ ነበር።
ከስራ የተባረሩ አንዳንድ ሠራተኞች የስራ ውሏቸው እንዲቋረጥ የተላለፈውን ውሳኔ ለማሳገድ በፍርድ ቤት ክስ መስርተዋል።
የአሁኑ ሰራተኞችን የመቀነስ ውሳኔ አርብ ማታ ይፋ የተደረገው የትራምፕ አስተዳደር የቪኦኤን ዳይሬክተር ማይክል አብራሞዊትዝን ከሥራ ለማባረር ያደረገው ሙከራ ተገቢውን አሠራር ያልተከተለ እንደሆነ በፍርድ ቤት ብይን ከተሰጠ አንድ ቀን በኋላ ነው።
ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ፤ የጊዜያዊ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ከጠበቃዎች የሚቀርቡ ጥያቄዎችን እንዲመልሱ በሚደረግበት የቅድመ ክስ ሂደት ምስክርነት ላይ እንዲሳተፉ አዝዘዋል።
ይህ ውሳኔ የተላለፈበት ክስ የተመሰረተው፤ ቪኦኤን ለመዝጋት የሚደረገውን ጥረት ለማስቆም እየጣሩ ባሉ የኤጀንሲው ሰራተኞች ነው።
ሠራተኞቹ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ በላኩት መግለጫ፤ "የሌክ በኤጀንሲያችን ላይ እየፈጸመቻቸው ያሉ ተከታታይ ጥቃቶች አስጸያፊ ሆነው አግኝተናቸዋል" ብለዋል።
"ቪኦኤን ለማፍረስ ያቀረበችው እቅድ ኮንግረሱ በሚጠይቀው ጥብቅ የግምገማ ሂደት ያለፈ መሆን አለመሆኑን ለመስማት የምስክር ቃሏን በጉጉት እንጠብቃለን። እስካሁን ድረስ ይህንን የሚያመለክት ምንም ማስረጃ አላየንም፤ ስለሆነም በህጉ መሰረት መብታችን ነው ብለን ስለምናምንበት ነገር መታገላችንን እንቀጥላለን" ሲሉም አቋማቸውን ገልጸዋል።
አብዛኞቹ የቪኦኤ ጋዜጠኞች ከመጋቢት ወር ጀምሮ በግዳጅ ፈቃድ ላይ እንዲቆዩ የተደረጉ ሲሆን አንዳንድ የፋርስ ቋንቋ ተናጋሪ ሠራተኞች ግን ሰኔ ላይ በእስራኤል እና በኢራን መካከል ጦርነት በፈነዳበት ጊዜ ተመልሰው ተጠርተው ነበር።
ሰራተኞችን የማባረር ውሳኔው ከማያሚ በስፓኒሽ ቋንቋ ዜና የሚያስተላልፈው የኩባ ብሮድካስቲንግ ክፍል ውስጥ የሚሰሩ ጋዜጠኞችን አይመለከትም።
ትራምፕ የአሜሪካ ድምፅን ለመዝጋት ያደረጉት ያለው ጥረት የፕሬስ ነጻነት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው በማለት የሚቃወሙ ተቺዎች፤ እርምጃው አሜሪካ በውጭ አገራት ላይ ለስላሳ ኃይል የመጠቀም አቅሟን የሚጎዳ መሆኑን ይናገራሉ።
የፕሬዝዳንቱ አስተዳደር በበኩሉ መገናኛ ብዙሃኑ "ፀረ-ትራምፕ" እና "አክራሪ" ነው በማለት ይከስሳል።
የቲቪ እና ራዲዮ ስርጭቶች እንዲሁም የዲጂታል አማራጮች ያሉት ቪኦኤ፤ በተለያዩ ሀገራት በ50 ገደማ ቋንቋዎች ይዘቶቹን ያቀርባል።