በሊቢያ የባሕር ዳርቻ የ61 ስደተኞች አስከሬን ተገኘ

የሊቢያ ባለሥልጣናት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ በአገሪቱ ምዕራባዊ ባሕር ዳርቻ የ61 ስደተኞችን አስከሬን መገኘቱን አስታወቁ።

በሊቢያ ጤና ሚኒስቴር ስር የሚተዳደረው የድንገተኛ ሕክምና እና ድጋፍ ማዕከል አስከሬኖቹ የተገኙት በቱኒዚያ ድንበር አቅራቢያ ከዙዋራ እስከ ራስ ልጃር ባሉት አካባቢዎች ነው ብሏል።

ማዕከሉ ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ ላይ "ሁሉም አስከሬኖች የሕገወጥ ስደተኞች ሲሆኑ የሦስት ሰዎች አስከሬን የተገኘው በሜሊታህ፣ የ12ቱ ደግሞ በዙዋራ ነው" ብሏል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ተጨማሪ የ34 ስደተኞች አስከሬን በዙዋራ፣ አቡ ካማሽ እና ሜሊታህ መገኘቱን ማዕከሉን ጠቅሶ ዘግቧል።

እስካሁን ድረስ የ12 ስደተኞች አስከሬን ሲቀበር የቀሪዎቹ ደግሞ ለምርመራ እና ማን መሆናቸውን ለመለየት ወደ አስከሬን ማቆያ ክፍል መላኩን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

በማዕከሉ በተረጋገጠ የፌስቡክ ገፁ ላይ ያጋራቸው ምስሎች የሕክምና ቡድን አባላት ከባሕር ዳርቻዎች አስከሬኖቹን እየሰበሰቡ በነጭ ፕላስቲክ ውስጥ ሲያስቀምጡ ያሳያል።

ይህ አሳዛኝ ዜና የተሰማው ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት መስከረም አጋማሽ ላይ 75 ሱዳናውያን ስደተኞችን ያሳፈረች መርከብ፤ ከሊቢያ የባሕር ዳርቻ ከተነሳች በኋላ በእሳት በመያያዟ የተነሳ ቢያንስ 50 ሰዎች መሞታቸውን ካስታወቀ በኋላ ነው።

ሊቢያ ከአፍሪካ እና ከመካከለኛው ምሥራቅ መጥተው ወደ አውሮፓ በባሕር ለማቋረጥ ለሚፈልጉ ሕገወጥ ስደተኞች ቁልፍ መሸጋገሪያ አገር ናት።

የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በአሁኑ ወቅት በሊቢያ ከ45 አገራት የመጡ 900,000 ስደተኞች እንደሚኖሩ ይገምታል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2011 ሙአመር ጋዳፊ ከሥልጣን ከተወገዱ አንስቶ አገሪቱ ወደ ለየለት አለመረጋጋት ውስጥ ገብታ ቆይታለች።

የባሕር ዳርቻዎቿም የበርካታ ስደተኞችን ሕይወት እየቀጠፈ የሕገወጥ መተላላፊያ ዋና መስመር ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።