ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የተራቡ ሕጻናትን ሊያይ ሄዶ በእስራኤል ጥቃት የቆሰለው የቢቢሲ ዘጋቢ
እስራኤል በጋዛ የምታካሄደው ጦርነት አስከፊ ገጽታ በየስፍራው ይታያል። የሞቱ ሰዎች አካላት፣ ለመሞት የሚያጣጥሩ፣ በረሃብ የተጎዱ ሁሉ በጋዛ ይታያሉ።
ይህ ቁጥር በየዕለቱ እየጨመረ የሚሄድ መሆኑን የቢቢሲ ጋዜጠኛ ይናገራል።
ማንም ቢሆን በጋዛ የሚገጥመውን ለረዥም ደቂቃ ለማየት አይደፍርም። የቢቢሲ ካሜራ ባለሙያ ግን ለዚህ ስሜት የሚረብሽ ትዕይንት አልተሸነፈም። ማክሰኞ ዕለት በጋዛ በምግብ እጥረት የተጎዱ ሕጻናትን ታሪክ እየሰነደ የነበረው የቢቢሲ የካሜራ ባለሙያ ጥቃት ደርሶበታል።
ለደኅነነቱ ሲባል ይህ የካሜራ ባለሙያ ስም ከመግለጽ ተቆጥበናል።
የቢቢሲ ካሜራ ባለሙያ የዕድል ጉዳይ ሆኖ በጥቃቱ ከባድ ጉዳት አልደረሰበትም።
የእስራኤል ቦምብ የወደቀው ኻሃን ዩኒስ በሚገኘው የአውሮፓውያን ሆስፒታል የመኪና ማቆሚያ ላይ ነበር።
በጥቃቱም ከ20 በላይ ሰዎች መሞታቸው ታውቋል።
የእስራኤል ጦር የሐማስ መሪ በሆስፒታሉ ስር ተደብቆ ትዕዛዝ እየሰጠ ነው ብሏል።
መከላከያው "ዒላማውን የጠበቀ" ጥቃት መፈጸሙን ተናግሮ ሐማስን "ለማመን በሚያስቸግር እና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በሆስፒታል አካባቢ የሚገኙ ሰላማዊ ዜጎች መካከል ይሸሸጋል" ሲል ወንጅሎታል።
ሐማስ የሚቀርቡበትን ውንጀላዎች አስተባብሏል።
ጥቃቱ በደረሰበት ወቅት ልጆቻቸው የታመሙባቸው እና አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ የተነገራቸው ወላጆች በስፍራው ተሰባስበው ነበር።
ሌሎች ደግሞ ከውጭ ሕክምና ተከታትለው የሚመለሱ ልጆቻቸውን ለመቀበል እየተጠባበቁ ነበር። ከቢቢሲ የካሜራ ባለሙያ ጋር አንድ አባት የነበረ ሲሆን፣ እርሱም በቦምብ ጥቃቱ ጉዳት ደርሶበታል።
የቢቢሲ ባልደረባ ሕክምና ተከታትሎ ከሆስፒታል ወጥቷል።
ጋዜጠኛው በጥቃቱ የተሸበረን ልጅ ለማጽናናት ሲታገል የሚያሳይ ምሥል ይታያል።
ማስጠንቀቅያ፡ ይህ ዘገባ የሚረብሽ ምስል ይዟል
በጋዛ ዙሪያ ዘገባ የሚሠሩ አብዛኞቹ ባልደረቦቼ ትኩረታቸው በምግብ እጥረት የተጎዱት ሕጻናት ናቸው።
ፍንዳታው ከመድረሱ ጥቂት ደቂቃ ቀደም ብሎ የሲዋር አሾርን ታሪክ በሚገባ በመቅረፁ የጽሑፍ መልዕክት ልኬለት ነበር።
የእርሱ ምላሽ "የሲዋር ታሪክ በሁላችንም ውስጥ የሆነ ነገር ፈንቅሏል። እናም ይህ ታሪክ ከሠራኋቸው ሁሉ ስሜቴን የረበሸው ነው። ነገር ግን ፊቷን አውቀዋለሁ፤ ስሟን አውቀዋለሁ፤ ታሪኳን አወቀዋለሁ እናም ታሪኳ መታየት፤ መደመጥ አለበት።"
የአምስት ዓመቷ ሲዋር ትልቅ እና ጎላ ጎላ ያሉ ቡናማ ዓይኖቿ በከባድ የምግብ እጥረት ምክንያት ቅዝዝ ብለዋል።
ቢቢሲ የእናቷን የናጅዋን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ እየተከታተለ ሰንዷል።
ማክሰኞ ዕለት ናጅዋ በደቡብ ጋዛ ከሚገኘው የናስር ሆስፒታል ከሚገኘው ቤቷ ሆና የቪድዮ መልዕክት ላከችልን።
ዓለም ልጇን ምን ያህል እንደምትወዳት እንዲያውቅ ትፈልጋለች።
"የሚያስፍለጋትን ሕክምና ብታገኝ፤ ብትድን እና እንደ ከዚህ ቀደሙ ወደ ሙሉ ጤንነቷ ተመልሳ ከእኩዮቿ ጋር ብትጫወት ደስ ይለኛል። ዳግም አድጋ ክብደቷ ጨምሮ ባይ ደስታዬን አልችለውም። የመጀመሪያ ልጄ ናት እና እንደ እናት ለእርሷ ልቤ ክፉኛ ተሰብሯል።"
ባለፉት ጥቂት ቀናት ሲዋር የቆዳ ኢንፌክሽን አጋጥሟታል።
እጇ መላላጥ የጀመረ ሲሆን፣ ከአፏ ጀምሮ የምግብ መውረጃ ቱቦዋ ላይ ችግር ገጥሟታል።
የሕክምና ባለሙያዎች ትግል እያደረጉ ያሉት ውስጧ ምግብ እንዲረጋ ለማድረግ ነው።
የእስራኤል መንግሥት ምግብ እና መድኃኒት እንዳይገባ ማገዱን ተከትሎ በሽታ የመከላከል አቅሟ ተዳክሟል።
ማክሰኞ ዕለት መልካም ዜና ተሰማ።
በአቅራቢያው የሚገኙ የዮርዳኖስ የመስክ ሆስፒታል ባለሙያዎች የሚያስፈልጋትን የዱቄት ወተት አገኙላት።
ትንሽ ቢሆንም ለሲዋር ለመላክ ወሰኑ።
በሚቀጥሉት ቀናት የታመሙ ሕጻናትን ወደ ተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ እና ዮርዳኖስ ለመላቅ ዕቅድ ተይዞ ነበር።
እዚህ ልጆቻቸው የታመሙባቸው ወይንም በአካባቢያቸው በሚገኝ ሆስፒታል በተፈጸመ ጥቃት ጉዳት ያጋጠማቸው ልጆችቻቸው የሚታከሙ በርካታ ወላጆች ይገኛሉ።
የእስራኤል መንግሥት ለሕክምና የሚሄዱ ልጆችን እና አብረዋቸው የሚሄዱ ወላጆችን የጀርባ ታሪክ በቅድሚያ ያጣራል።
በጥር ወር አብደልራህማን አል ናሻሽ ከእናቱ አስማ ጋር ሕክምና ተከታትሎ ሲመለስ ቀረጻ አድርገናል።
አብደልራህማን በእስራኤል ጥቃት የተነሳ አግሩን አጥቷል።
ለአራት ወራት ያህል ደኅነንነቱ በተጠበቀ ስፍራ ምግብ እና መጠለያ እያገኙ ቆይተዋል።
ማክሰኞ ዕለት አስማን ስንጎበኝ ለልጆቿ እና ለአያታቸው ደውላላቸው ነበር።
አያታቸው ናጅዋ በአካባቢያቸው ስላለው ጦርነት ታወራለች።
"ሮኬት በሁሉም ቦታ ነው የሚተኮሰው። በአናታችን ላይ ሲወነጨፍ ነው የሚውለው። ሕይወት ከባድ ነው። ምግብ፤ ዱቄት የለም። ዋጋው ደግሞ ጣሪያ ነክቷል፤ አይቀመስም።"
ልጆቹ እጃቸውን እያውለበለቡ፤ ከንፈራቸውን አሞጥሙጠው እጃቸውን እየሳሙ ፍቅራቸውን መናፈቃቸውን እና ስስታቸውን ገለፁ።
ከዚያ በኋላ አስማ "ምን ማለት እንዳለብኝ አላውቅም። እናቴ ለእኔ ስለምታደርገው ሁሉ በጣም አመሰግናለሁ። ብድራቷን መመለስ ብችል እና ደኅነነቱ የተጠበቀ ቦታ ባስቀምጣት ጤንነቷን ብንከባከብ ደስ ይለኛል" ብላለች።
ከዚያ በኋላ በሐዘን ውስጥ ሆና ዝም አለች።
ልጆቿ መውጫ እና መላወሻ አጥተው በተቀመጡ እናት ዓይን ውስጥ ፍርሃት እና ከረዥም ርቀት ረሃብ ይነበባል።
ሰዎች ወደ ጋዛ መመለስ ለምን እንደሚፈልጉ ማየት ይቻላል።