የሥነ ዜጋ እና ሥነ ምግባር ትምህርት ከ12ተኛ ክፍል ፈተናዎች መካከል እንዲወጣ ተደረገ

ያለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ ፈተናውን ሲወስዱ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Education/FB

የምስሉ መግለጫ, ያለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ ፈተናውን ሲወስዱ

ትምህርት ሚኒስቴር የ12ተኛ ክፍል ፈተና ላይ ከሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ውስጥ የሥነ ዜጋ እና ሥነ ምግባር ትምህርትን ሲያስወጣ፣ በአንጻሩ የኢኮኖሚክስ ትምህርት በማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ፈተና ውስጥ ተካተተ።

በዚህ ዓመት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ላይ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት መተግበር የጀመረው ትምህርት ሚኒስቴር፤ የ12ተኛ ክፍል የፈተና ዝርዝር ላይ ለውጥ ማድረጉን ያሳወቀው ሐሙስ ጥር 9/2016 በጻፈው ደብዳቤ ነው።

ለሁሉም የአገሪቱ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ትምህርት ቢሮዎች ሚኒስቴሩ የተጻፈው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ ፈተና በሚሰጥባቸው የትምህርት አይነቶች ላይ ለውጥ ለማድረግ የተወሰነው አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ወደ ትግበራ በመግባቱ ነው።

በዚህ ዓመት መተግበር የጀመረው ይህ ሥርዓተ ትምህርት 11ኛ እና 12ኛ ክፍሎች ላይ በሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ላይ ለውጥ አምጥቷል። በዚህም መሠረት የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች እንደ ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ እንዲሁም የጤና ሳይንስ ተማሪዎች የሥራ እና የቴክኒክ ትምህርቶችን እንዲወስዱ ተደርጓል።

የማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት ተማሪዎች ደግሞ በውስጡ ጋዜጠኝነትን ያካተተውን ቋንቋ እና ማኅበራዊ ሳይንስ እና ማርኬቲንግን የሚያካትተውን ቢዝነስ እንዲሁም ቲያትር እና ፊልምን ያካተተውን የሥነ ጥበባት ትምህርቶችን ይወስዳሉ።

በ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ላይ ከተካተቱት በአንጻሩ የተቀነሱ ትምህርቶችም አሉ። ከእነዚህም መካከል እስከ 10ኛ ክፍል ብቻ እንዲሰጡ የተደረጉት የሥነ ዜጋ እና ሥነ ምግባር እንዲሁም የጤና እና ሰውነት ማጎልመሻ ትምህርቶች ይገኙበታል።

በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ምክንያት 12ተኛ ክፍል ፈተና ላይ የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ተማሪዎቹ እንዲይዙት የሚፈለገውን “እውቀት፣ ክህሎት እና ባህሪያት” መቅሰማቸው የሚፈተኑበት እንደሚሆኑ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እሸቱ ከበደ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ሰባት የትምህርት ዓይነቶችን ተፈትነው ውጤታቸው ከ700 ይያዝ ነበር። ስድስት ፈተናዎችን የሚወስዱት የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ደግሞ ውጤታቸው የሚያዘው ከ600 ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአዲሱ የ12ተኛ ክፍል ፈተና የትምህርት ዓይነቶች ዝርዝር መሠረት ግን የማኅበራዊም ሆነ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች የሚፈተኑባቸው የትምህርት ዓይነቶች ስድስት እንዲሆን ተደርጓል። በዚህም ምክንያት የሥነ ዜጋ እና የሥነ ምግባር ትምህርት ከሁለቱም የትምህርት ዘርፎች ፈተናዎች ውስጥ ወጥቷል።

ከዚህ ቀደም የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች የ12ተኛ ክፍል ፈተና ላይ የማይሰጥ የነበረው ኢኮኖሚክስ ትምህርት ደግሞ እንዲካተት ተደርጓል።

እንደ ዶ/ር እሸቱ ገለጻ፣ የሥነ ዜጋ እና ሥነ ምግባር ትምህርት በ12ተኛ ክፍል ፈተና ላይ እንዳይሰጥ የተደረገው በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ምክንያት ትምህርቱ ከ10ኛ ክፍል በኋላ ስለማይሰጥ ነው።

ዶ/ር እሸቱ ኢኮኖሚክስ ትምህርት የተካተተበትን ምክንያት ሲያስረዱ ደግሞ “ኢኮኖሚክስ ከዚህ ቀደምም ይሰጥ ነበር። መሃል ላይ የሆኑ የጥናት ሃሳቦች ተነስተው ከፈተና እንደወጣ እናውቃለን፤ አሁን ግን ወደ ሥርዓተ ትምህርቱ ተመልሷል፤ መጽሐፍ ታትሞለታል። እንዲማሩ እየተደረገ ካለው ጥረት አንጻር ወደ ፈተና ቢገባ የሚሉ ሀሳቦች ተነስተዋል” ብለዋል።

የ12ተኛ ክፍል ፈተና ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ የሚሰጠውን ትምህርት የሚያካትት ሲሆን፣ ዘንድሮ ግን የኢኮኖሚክስ ትምህርት ፈተና የሚወጣው ከ12ተኛ ክፍል ብቻ እንደሆነ ትምህርት ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ ላይ ጠቅሷል።

ኩረጃን እና የፈተና ስርቆትን ለመከላከል በጥብቅ ቁጥጥር ውስጥ ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ መሰጠት የተጀመረው የ12ተኛ ክፍል ፈተና፤ ባለፉት ዓመታት እጅጉን ዝቅተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች የሚያልፉበት ሆኗል።

የዘንድሮው የ12ተኛ ክፍል ፈተና መቼ ሊሰጥ እንደታሰበ ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እሸቱ፤ “አሁን ከክልሎች ጋር ምክክር እያደረግን ነው። በቅርቡ እናሳውቃለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።