ለታይዋን ከተደረገ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ጋር በተያያዘ ቻይና በአምስት የአሜሪካ ድርጅቶች ላይ ማዕቀብ ጣለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ ለታይዋን ካካሄደችው የጦር መሳሪያ ሽያጭ ጋር በተያያዘ በአምስት የምዕራባውያን የመከላከያ ድርጅቶች ላይ ማዕቀብ እንደምትጥል ቻይና አስታውቃለች።
መግለጫው የተሰጠው ታይዋን ከቀናት በኋላ ፕሬዝዳንታዊ እና የፓርላማ አባላት ምርጫን ለማድረግ በምትዘጋጅበት ወቅት ነው ።
የአሜሪካ ጦር መሳሪያ ለታይዋን መሸጥ በቤጂንግ እና በዋሽንግተን መካከል ተደጋጋሚ የውጥረት ምንጭ ነው።
ቻይና ታይዋንን እንደ አንድግዛቷ ትመለከታለች፤ የታይዋን መንግሥት ግን ይህንን ውድቅ ያደርገዋል።
ባለፈው ወር የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የታይዋንን የታክቲካል መረጃ ስርዓት ለመጠበቅ የሚረዳ የ300 ሚሊዮን ዶላር የመሣሪያ ሽያጭ አጽድቋል።
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እሑድ ዕለት በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው ማዕቀቡ “ዩናይትድ ስቴትስ ለወሰደቻቸው የተሳሳቱ እርምጃዎች ምላሽ እንዲሆን ነው።”
በቅርቡ የተካሄደው የጦር መሳሪያ ሽያጭ የቻይናን ሉዓላዊነት እና ደኅንነት በእጅጉ ከመጉዳት ባለፈ በአካባቢው ያለውን ሠላም እና መረጋጋት ይጎዳል ብሏል።
ማዕቀብ የተጣለባቸው ኩባንያዎች ቢኤኢ ሲስተም ላንድ ኤንድ አርማመንት፣ አሊያንት ቴክሲስተምስ ኦፕሬሽን፣ ኤሮቫይሮንመንት፣ ቪያሳት እና ዳታ ሊንክ ሶሉሽንስ የሚባሉ ናቸው።
ቻይና የኩባንያዎቹን ንብረት ከማገድ ባለፈ በቻይና ያሉ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ከእነሱ ጋር እንዳይገናኙ ታግዳለች ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ቢቢሲ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጠው በቤጂንግ የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲ ጠይቋል።
ደሴቲቱ ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት ሊቀይረው ከሚችለው ምርጫ በፊት ቤጂንግ፣ በታይዋን ላይ ጫናዋን አሳድጋለች።
ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በዓመታዊው የአዲስ ዓመት ዋዜማ ንግግራቸው ታይዋን ከቻይና ጋር "በእርግጠኝነት ዳግም ትዋሃዳለች" ሲሉ በድጋሚ ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት ካስተላለፉት ጠንከር ባለ መልኩም ታይዋን “የትልቁ ቤተሰብ” አካል መሆኗን ተናግረዋል።
23 ሚልዮን ህዝብ ያላት ደሴት ውሎ አድሮ በቤጂንግ ቁጥጥር ስር እንደምትሆን ቤጂንግ ታምናለች።
ታይዋን ራሷን ከቻይና የተለየች፣ የራሷ ህገ መንግስት እና በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ መሪዎች እንዳላት አገር ትቆጥራለች።












