ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከወራት በፊት ለፈጸመው ጥቃት የሁለት ጨዋታ ቅጣት ተጣለበት

የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ ተጫዋች የነበረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከአንድ የኤቨርተን ደጋፊ እጅ ላይ ሞባይል ስልክ መትቶ በማስጣሉ ከሁለት የአገር ውስጥ ጨዋታዎች እገዳ ተጥሎበታል።

የ37 ዓመቱ ሮናልዶ ይህንን ድርጊት የፈጸመው ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ላይ በጉዲሰን ፓርክ ስታዲየም ሽንፈት ከገጠማቸው በኋላ በስታዲየሙ መተላላፊ በኩል ሲወርድ መሆኑ ተገልጿል።

ከቡድኑ ማንችስተር ዩናይትድ እና ከአሰልጣኑ ኤሪክ ቴን ሃግ ጋር በተፈጠረው የግንኙነት መሻከር ምክንያት፣ ባለፈው ማክሰኞ ሮናልዶ እና ቡድኑ በጋራ በደረሱት ስምምነት ተጫዋቹ ተሰናብቷል።

ሮናልዶ ከወራት በፊት በአንድ ተመልካች ላይ ፈጽሞታል ከተባለው ጥቃት ጋር ተያይዞ ከሁለት ጨዋታ ከመታገዱ በተጨማሪም፣ የእግር ኳስ ማኅበሩ የ50,000 ፓወንድ ቅጣትም ጥሎበታል።

ይህ የጨዋታ ዕገዳ ግን ዛሬ ከአፍሪካዋ ተወካይ ጋር በዓለም ዋንጫ የመጀመሪያዋን ግጥሚያ ለምታደርገው ለአገሩ ፖርቱጋል ከመሰለፍ አያግደውም ተብሏል።

በኳታሩ የዓለም ዋንጫ በምድብ 'ሸ' ከጋና፣ ከደቡብ ኮሪያ እና ከኡራጓይ ጋር የተደለደለችውን የፖርቱጋልን ብሔራዊ ቡድን በአምበልነት የሚመራው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ትልቅ ኃላፊነት ይጠብቀዋል።

ከማንችስተር ዩናይትድ ከተሰናበተ በኋላ በአሁኑ ወቅት የሚጫወትበት ቡድን የሌለው ሮናልዶ፣ የተጣለበት የክለብ ጨዋታ ዕገዳ በአንግሊዝም ሆነ በሌላ አገር በቀጣይ በሚቀላቀው ቡድን ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል።

ነገር ግን ይህ ቅጣት ቡድኑ በሚያደርገው የአገር ውስጥ የሊግ ጨዋታ ላይ እንጂ ሻምፒዮን ሊግን በመሳሰሉ አህጉራዊ የክለቡ ተሳትፎዎች ላይ ተፈጻሚ አይደረግም ተብሏል።

ሮናልዶን ለሁለት ጨዋታ ዕገዳ የዳረገውን ድርጊት በተመለከተ በእንግሊዝ የእግር ኳስ ማኅበር በኩል ገለልተኛ ማጣራት ከተካሄደ በኋላ ነው ተገቢ ያልሆነ እና ጎጂ ጥፋት ፈጽሟል ተብሎ ጥፋተኛ የተባለው።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ሮናልዶ ከፖሊስ ማስጠንቀቂያ የደረሰው ሲሆን፣ ጥቃት አድርሶበታል የተባለው ወጣት የእግር ኳስ ተመልካችን ከክስተቱ በኋላ ይቅርታ መጠየቁም ተነግሯል።

የእንግሊዝ እግር ኳስ ማኅበር ክርስቲያኖ ሮናልዶ ተገቢ ያልሆነ ባህሪይ ማሳየቱን እንዳመነ፣ ነገር ግን ጎጂ ፀባይ የተባለውን እንዳልተቀበለው ገልጸወል።

ክርስቲያኖ ሮናልዶ ወደ ቀድሞ ክለቡ ማንችስተር ዩናይትድ ከተመለሰ በኋላ የነበረው ቆይታውን እንዲያበቃ ያደረገው አወዛጋቢ ቃለ ምልልስ ከሰጠ በኋላ ነበር።

በቃለ ምልልሱ ሮናልዶ ቡድኑን ክፉኛ ያብጠለጠለ ሲሆን፣ ለአሰልጣኙ ኤሪክ ቴን ሃግም “አክብሮት እንደሌለው” ከገለጸ በኋላ መነጋገሪያ ሆኖ ትችትና ድጋፍ ከተለያዩ ወገኖች ደርሶታል።

ይህ ሁኔታ የፈጠረው መቃቃርም ተጫዋቹ በቡድኑ ውስጥ የመቀጠሉን ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ አስገብቶ ከቆየ ከሳምንት በኋላ በስምምነት ከኦልትራፎርድ ተሰናብቷል።

ነገር ግን ሮናልዶ በቀጣይ ወደ የትኛው አገር እና ቡድን ሊያመራ እንደሚችል አስካሁን የታወቀ ነገር የለም።