በናይጄሪያዋ አቡጃ እስር ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከ400 በላይ እስረኞች አመለጡ

በናይጄሪያ ዋና ከተማ አቡጃ ጥቃቱ የተፈጸመበት እስር ቤት አንድ ክፍል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በናይጄሪያ ዋና ከተማ አቡጃ ጥቃቱ የተፈጸመበት እስር ቤት አንድ ክፍል

በናይጄሪያዋ ዋና ከተማ አቡጃ ውስጥ በሚገኝ አስር ቤት ላይ የተፈጸመን ጥቃት ተከትሎ ከ400 በላይ አስረኞች ማምለጣቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ማክሰኞ ሌሊት እስር ቤቱን ኢላማ ያደረገው ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በጥቃቱ አራት አስረኞች፣ አንድ የእስር ቤቱ ጠባቂ እና በርካታ ጥቃት ፈጻሚዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናቱ አሳውቀዋል።

አስላማዊ ታጣቂዎች ይህንን ጥቃት ሳይፈጽሙ እንዳልቀሩ የተጠረጠረ ሲሆን፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው የቡድኑ አባላት ከአስር ቤቱ ሳያመልጡ እንዳልቀሩ ይታመናል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በናይጄሪያ ከሚገኙ እስር ቤቶች ከ5 ሺህ በላይ ታሳሪዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ተከትሎ ማምለጣቸው ይነገራል።

ከዋና ከተማዋ ወጣ ብሎ በሚገኘው መካከለኛ ጥበቃ በሚደረግለት የኩጄ እስር ቤት ላይ ማክሰኞ ዕለት ጥቃቱ ሲፈጸም በአቅራቢያው ከባድ ፍንዳታና የተኩስ ድምፅ ተሰምቷል።

“በመጀመሪያ የተኩስ ድምፅ ስንሰማ ታጣቂዎች ዘረፋ ፈጽመው ሊሆን ይችላል ብለን ነበር” ሲል አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግሯል።

"ከተኩሱ በኋላ ፍንዳታ ተከተለ። ከዚያምበተደጋጋሚ ፍንዳታ ተሰምቷል።”

በጥቃቱ አራት እስረኞች የተገደሉ ሲሆን፣ ሌሎች 16 ደግሞ የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸው የናይጄሪያ የማረሚያ ቤቶች አገልግሎት አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት በርካታ ቁጥር ያላቸው ተጠርጣሪ ታጣቂዎች እና ፖለቲከኞችን ጨምሮ ከፍተኛ ወንጀል ፈጽመዋል የሚባሉ ግለሰቦች በእስር ቤቱ ውስጥ ነበሩ። ነገር ግን የማረሚያ ቤቶች ባለሥልጣናት እንዳሉት ከእነዚህ መካከል ያመለጡ እንደሌሉ ተናግረዋል።

ጥቃቱ ሲፈጸም በእስር ቤቱ ውስጥ 1 ሺህ የሚሆኑ እስረኞች እንደነበሩ ባለሥልጣናት አመልክተዋል። ጥቃቱን ተከትሎ ሁሉም በሚባል ደረጃ ከአስር ቤቱ አምልጠው የነበረ ቢሆንም 443ቱ መልሰው ተይዘዋል።

የናይጄሪያ የመከላከያ ሚኒስትር ባሺር ማጋሺ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ ጥቃቱ በታጣቂው ቦኮ ሃራም ቡድን ሳይፈጸም እንዳልቀረ አመልክተዋል። በዚህም በአስር ላይ የነበሩ 64 አስላማዊ ታጣቂዎች ማምለጣቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

“አንዳቸውም በእስር ቤቱ ውስጥ የሉም፣ አምልጠዋል” ብለዋል ሚኒስትሩ፥

አስላማዊ መንግሥት ወይንም አይኤስ የሚባለው ቡድን አካል ነኝ የሚለውና በምዕራብ የአፍሪካ ክፍል የሚንቀሳቀሰው የቦኮ ሃራም ቡድን አጋር፣ በእስር ቤቱ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ኃላፊነቱን በመውሰድ በርካታ አስረኞችን ማስለቀቁን ገልጿል።

የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሐማዱ ቡሃሪ የአገሪቱ የደኅንነት ተቋማት የመረጃ ሥርዓት ደካማነትን በማንሳት ለጥቃቱ መከሰት ምክንያት ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

ፐሬዝዳንቱ ጨምረውም ለእስር ቤቱ ይደረግ በነበረው ጥበቃ ላይ ጥያቄ አንስተው፣ ስለተፈጸመው ጥቃት “አጠቃላይ ሪፖርት” እንዲቀርብላቸው አዘዋል።

በአገሪቱ በትጥቅ የተደገፉ ጠላፊ ወንጀለኞችና ታታቂ ቡድኖች በሚፈጽሟቸው ጥቃቶች ሳቢያ የፕሬዝዳንት ቡሃሪ መንግሥት እየተስፋፋ ያለውን የደኅንነት ስጋት ሊቆጣጠር አልቻልም በሚል እየተጠናከረ የመጣ ትችት ይቀርብበታል።