ዚምባብዌ የመገበያያ ገንዘቧ መዳከምን ለመቋቋም የወርቅ ሳንቲሞችን ልታስተዋውቅ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዚምባብዌ የመገበያያ ገንዘቧ ከውጭ ምንዛሬ አንፃር ማሽቆልቆልንና በአገሪቱ የተከሰተውን የዋጋ ግሽበት ለመግታት የወርቅ ሳንቲሞችን ለመገበያያነት እንዲውል ልታደርግ ነው።
በተጨማሪም የሀገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ የአሜሪካ ዶላርን ለሚቀጥሉት አምስት አመታት ህጋዊ መገበያያ ለማድረግም ማቀዱን አስታውቋል።
አመታዊው የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት 190 በመቶ በላይ ከፍ ማለቱን ተከትሎ የማዕከላዊ ባንክ ዋና የወለድ ምጣኔ በዚህ ወር ከእጥፍ በላይ ወደ 200 በመቶ አድጓል።
የዚምባብዌ የመገበያያ ገንዘብ ዶላር በዚህ አመት ከሌሎች ከውጭ አገር መገበያያ ገንዘቦች አንፃር በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆል አሳይቷል።
አንድ ትሮይ አውንስ ብዛት ያላቸው 22 ካራት ወርቅ የሆኑ የወርቅ ሳንቲሞች በያዝነው ወር መጨረሻ በገበያ ላይ እንደሚውሉ የዚምባብዌ ሪዘርቭ ባንክ ገዥ የሆኑት ጆን ፒ ማንጉዲያ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ትሮይ አውንስ የከበረ ማዕድናትን እንደ ወርቅ፣ ብር እና ፕላቲኒየም የመሳሰሉትን ለመመዘን የሚያገለግል የመለኪያ አሃድ ነው። መለኪያው ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ የነበረ ሲሆን አንድ ትሮይ አውንስ ከ31.10 ግራም ጋር እኩል ነው።
“የወርቅ ሳንቲሞቹ በአለም አቀፍ የወርቅ ዋጋ እና በተመረተበት ዋጋም በበመስረት ለህዝቡ በአገር ውስጥ ምንዛሬ፣ በዶላር እና በሌሎች አገራት የውጭ ምንዛሬዎች ለሽያጭ ይቀርባሉ" ብለዋል ማንጉዲያ
መግለጫው በተጨማሪም ለእያንዳንዱ የወርቅ ሳንቲም መለያ ቁጥር የሚሰጣቸው ሲሆንም ሳንቲሞቹንም በቀላሉ ወደ ጥሬ ገንዘብ በአገር ውስጥ እና በአለም አቀፍ ደረጃ እንደሚለወጥም ገልጿል።
በዚምባብዌ እና ዛምቢያ አዋሳኝ ላይ የሚገኘውን የቪክቶሪያ ፏፏቴንም ስያሜ በመውሰድ "ሞሲ-ኦአ-ቱኒያ” የወርቅ ሳንቲም" የሚል ስም ተሰጥቶታል።
የወርቅ ሳንቲሞቹ ወደ ገበያ መምጣት የዚምባብዌ መንግስት የሀገሪቱን የመገበያያ ገንዘብ ቀውስ ለመቅረፍ የወሰደው እርምጃ አካል ነው።












