አሜሪካዊው ታዋቂ የጊታር ተጫዋች ካርሎስ ሳንታና ራሱን ስቶ መድረክ ላይ ወደቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታዋቂው አሜሪካዊ ጊታር ተጫዋች ካርሎስ ሳንታና በዲትሮይት ሚቺጋን አቅራቢያ በነበረ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ መድረክ ላይ ራሱን ስቶ ወደቀ።
የህክምና ባለሙያዎች የ74 ዓመቱን ሙዚቀኛ በስፍራው ተገኝተው ያከሙት ሲሆን በአካባቢው ወደሚገኝ ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ተወስዷል።
ሜክሲኮ የተወለደው ካርሎስ ሳንታና ትንሽ ሻል ካለው በኋላ ፌስቡክ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው “ ምግብ መብላትና መጣጣት ረስቼ ነበር” እናም “ሰውነቴ ዝሎ ራሴን ስቼ ወደቅኩ” ብሏል።
የካርሎስ ሳንታና ስራ አስኪያጅ ሚካኤል ቭሪዮኑስ ሙዚቀኛው ሻል ባለ ሁኔታ ላይ ነው ያለው ብሏል።
ሆኖም ዛሬ ረቡዕ በበርጌትስታውን ፔንስልቬንያ ሊካሄድ የታሰበው የሙዚቃ ኮንሰርት ለሌላ ጊዜ እንደሚዘገይ አክሏል።
ካርሎስ ሳንታና በክላርክሰን ፓይን ኖብ የሙዚቃ ትያትር ቤት ከመድረክ ላይ ታግዞ ሲወሰድ የሚያሳይ ቪዲዮም ወጥቷል። ቪዲዮው ላይ ሙዚቀኛው በቃሬዛ ሲወሰድ ወደ ታዳሚው እጁን እያውለበለበ ነበር።
ስመ ጥር የሆነውን የግራሚ ሽልማት አስር ጊዜ ያሸነፈው ሳንታና ተወካዮች በሙቀት ድካም እና በድርቀት እየተሰቃየም ነበር ብለዋል።
ጊታር ተጫዋቹ ከባንዱ ጋር ለየት ያለ የሙዚቃ ዝግጅታቸውን በሰሜን አሜሪካ እየተዘዋወሩ ኮንሰርት እያቀረቡ ይገኛሉ።
በ1960ዎቹና 70ዎቹ ሮክ ኤንድ ሮልና የላቲን አሜሪካን ጃዝ ለየት ባለ መልኩ በማጣመር ፈር ቀዳጅ የሆኑት ካርሎስ ሳንታናና ባንዱ ዝነኛም ለመሆን በቅተዋል።
የባንዱ ታዋቂ ሙዚቃዎች መካከል ‘ብላጅ ማጂክ ውማን’፣ ‘ዘ ጌም ኦፍ ላቭ’ እና ኦዬ ኮሞ ቫ ይገኙበታል።
በአሁኑ ወቅት ካርሎስ ሳንታና አለማችን ካተረፏቸው የጊታር ተጫዋቾች አንዱ ነው ተብሎ ይታሰባል። ለዚህም ለየት ያለ የሙዚቃ ዘይቤ ይዞ መምጣቱና የላቲን ምቶች ይጠቀሳሉ። በአውሮፓውያኑ 2015 የሮሊንግ ስቶን መጽሔት በ100 ታላላቅ ጊታሪስቶች ዝርዝር ውስጥ 20ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጦታል።












