ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ጉባኤ እየተካሄደ ነው
በትግራይ ክልል ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ እንዲሁም ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ ባለፉት ወራት የተለያዩ ችግሮች የተከሰቱበት የአማራ ክልልን እየመራ የሚገኘው የክልሉ ገዢ ብልጽግና ፓርቲ የሕዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።
በተለይ ባለፉት ወራት የተለያዩ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች፣ ውጥረት፣ ግጭቶች እና የከፍተኛ አመራር ግድያ ያጋጠመው የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ አንድ ክንፍ የሆነው የአማራ ብልጽግና፣ የከፍተኛ እና የመካከለኛ አመራሮች ጉባኤውን በክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር ውስጥ ጀምሯል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ፣ እንደተናገሩት በክልሉ ያጋጠሙት ቀውሶች የበለጠ ችግሮችን የፈጠሩ መሆናቸውን ጠቅሰው ሕዝቡ እነዚህን ሁኔታዎች “መመርመር አለበት” ብለዋል።
ባለፉት ወራት ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ውጪ ያሉ ታጣቂዎችን በተመለከተ፣ የክልሉን ልዩ ኃይል መልሶ ለማዋቀር በፌደራል መንግሥቱ ከወጣው ዕቅድ ጋር እና የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ከሆኑት አቶ ግርማ የሺጥላ ግድያ ጋር በተያያዘ የሰው ሕይወት የጠፋባቸው ቀውሶች ማጋጠማቸው ይታወሳል።
የክልሉ ገዢ ፓርቲ ብልጽግና፣ የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ እና ጥቅሞቹን ለማስከበር በሚጥርበት ወቅት ርዕሰ መስተዳደሩ “ባለቤታቸው ያልታወቁ” ያሏቸው አድማ እና አመጾች አመራሩ ለጥያቄዎቹ አስፈላጊውን ግብ እና ስልት አስቀምጦ እንዳይሰራ አድርገውታል ብለዋል።
“የገጠመን ችግር ውስብስብ ነው” ያሉት ዶ/ር ይልቃል ይህም “በፓርቲው እና በመንግሥት መፍትሔ ከሚያስፈልገው ወቅት ላይ ደርሰናል” በማለት፣ አመራሮቹ ከሐሙስ ግንቦት 10/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በሚያካሂዱት ጉባኤ ላይ ትኩረት ይደረግባቸዋል ብለዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መሰተዳደር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ በአሁኑ ወቅት የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄዎች ምን እንደሆኑ እንደገና መፈተሽ እንደሚያስፈልግ አመልክተው፣ በክልሉ “ያደሩ፣ የነበሩ እና ትግል እየተካሄደባቸው ያሉ ጥያቄዎች አሉ” ብለዋል።
ዶ/ር ይልቃል የአማራ ክልል ሕዝብ አሁንም ምላሽ እንዲያገኙ የሚፈልጋቸው ጥያቄዎች በማለት “የማንነት እና የወሰን፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ፣ የተዛባ ትርክት እና የብሔሩ ተወላጆች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል መብታቸው ተጠብቆ የመኖር መብት” ሲሉ ዘርዝረዋቸዋል።
ለዚህም ፓርቲው ተገቢውን ግብ እና ስልት አስቀምጦ ባለመስራቱ በሕዝቡ ዘንድ ቅሬታ ተፈጥሯል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ገዥው ፓርቲ የሕዝቡን ጥያቄ በመመለስ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው አሁንም “ጥያቄዎቹን መርምሮ ወጥ አቋም በመያዝ ትክክለኛ የትግል ስልት ቀይሶ ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ” ከፓርቲው አመራር የሚጠበቅ መሆኑን አመልክተዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ ጨምረውም እነዚህ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በተናጠል በክልሉ ሕዝብ እና አመራር ጥረት ብቻ የሚመለሱ አለመሆናቸውን አንስተው፤ የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ተሳትፎን የሚጠይቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል በተለይ በስተሰሜን ከሚዋሰነው ከትግራይ ክልል ጋር ለዘመናት የቆየ የማንነት እና የይዞታ ይገባኝል ጥያቄዎች ያሉበት ሲሆን አስካሁንም እልባት አላገኘም።
እንዲሁም ባለፉት ዓመታት ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ የብሔሩ አባላት በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጸምባቸው ጥቃቶች የተነሳ ጉዳት የደረሰባቸው ከመሆኑ ባሻገር በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል ተመልሰው በችግር ላይ መሆናቸው ተዘግቧል።
የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የሆነው ብልጽግና አንድ አካል የሆነው የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አባላት ያሉት ሲሆን፣ አሁን በአጠቃላይ የክልሉ እና የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሚመክሩት የፓርቲው መካከለኛ እና ከፍተኛ አመራሮች መሆናቸው ተነግሯል።
“ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ያለው የአማራ ብልጽግና ፓርቲ የከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ጉባኤ፣ የሚካሄደው ከሳምንታት በፊት የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ እና የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በታጣቂዎች ከተገደሉ በኋላ ነው።
የከፍተኛ ባለሥልጣኑ ግድያ በክልሉ ውስጥ ተጨማሪ ቀውስን ያስከተለ ሲሆን፣ በአመራሮቹ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ርዕሰ መስተዳደሩ ግድያውን አንስተው ጥቃቱን አውግዘዋል።
ዶ/ር ይልቃል ከፋለ በአማራ ክልል ውስጥ አመራርን መግደል መደጋገሙን አመልክተው “ክልሉን መሪ በማሳጣት እና የሕዝቡን ሰላም በመናድ የሚመጣ ውጤት አይኖርም” በማለት አመራር በመግደል የአማራ ክልልን ችግር መፍታት አይቻልም ሲሉ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቀደም ሲል ከ25 ዓመታት በላይ አገሪቱን ያስተዳደረው የኢህአዴግ አባል የነበረ እና ብልጽግናን ከመሰረቱ ዋነኛ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው።