ፈረንሳይ የፍልስጥኤም የድጋፍ ሰልፎችን ከለከለች

ፈረንሳይ ፍልስጥኤምን ለመደገፍ የሚደረጉ ማንኛውንም የአደባባይ ሰልፎች ከለከለች።

የድጋፍ ሰልፎችን ሙሉ በሙሉ የከለለከችው ፈረንሳይ ይህንን ህግ ተላልፈው ለሰልፍ የሚወጡ የውጭ ሃገር ዜጎች ከአገሪቱ መባበረርን የመሰለ ጠበቅ ያለ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጄራልድ ዳርሚን አስጠንቅቀዋል።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው ህዝቡ በአንድነት እንዲቆም ጠይቀዋል።

በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ ጸረ ሴማዊነት እያንሰራራ ይመጣል የሚል ፍራቻ በአውሮፓውያኑ ዘንድ የነገሰ ሲሆን ይህም እርምጃ ያንን ተከትሎ ነው ተብሏል።

ፈረንሳይ ክልከላ ብታደርግም በሺዎች የሚቆጠሩ የፍልስጥኤም ደጋፊዎች ሐሙስ ዕለት በፓሪስ አደባባዮች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ሰልፈኞቹ የፍልስጥኤምን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ “እስራኤል ነፍሰገዳይ”፤ “ፍልስጥኤም ታሸንፋለች” እያሉ ዴ ላ ሪፐብሊክ በተሰኘው ስፍራ ሲያሰሙም ነበር።

ከ3 ሺህ በላይ የነበሩ ሰልፈኞችን ፖሊስ በውሃ ለመበተን የሞከረ ሲሆን አስር ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉም ተገልጿል።

እገዳውን ያዘዙት ሚኒስትሩ በበኩላቸው ህጉን የሚቃወሙ ማናቸውም መታሰር አለባቸው “ምክንያቱም የህዝብን ጸጥታ እያደፈረሱ ስለሆነ” ብለዋል።

የፍልስጥኤም ደጋፊ ቡድኖች በበኩላቸው እገዳው ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ጋር የሚጻረር ነው ሲሉ ድጋፋቸውን ለመቀጠልም ቃል ገብተዋል።

በሰልፉ ላይ የነበሩት ሻርሎት ቫውቲየር “ እኛ የምንኖረው ህግ ባለበት እንዲሁም አቋም የመውሰድ እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት በተከበረባት ሃገር ውስጥ ነው። ለአንድ ወገን መከልከል እና ለሌላው መፍቀድ ኢ-ፍትሃዊ ነው” ሲሉም ለሮይተርስ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ መልኩ የጀርመን ፖሊስ የጸረ ሴማዊነት መገለጫ እና ሁከትን ማወደስ ነው በሚል በመዲናዋ በርሊን ሊደረጉ የነበሩ የፍልስጥኤም የድጋፍ ሰልፎችን አግዷል።

ፖሊስ እንዳለው 60 የሚሆኑ ሰልፈኞች ፖስትዳመር ፕላትዝ ከተሰኘው ስፍራ ለቀው እንዲወጡ ሐሙስ እለት ትዕዛዝ መስጠቱን ነው።

የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ማክሮን ህዝቡ በአንድነት እንዲቆም አሳስበው ሐማስን “የእስራኤልን ህዝብ ሞት የሚፈልግ አሸባሪ ድርጅት” ሲሉም ገልጸውታል።