እስራኤል የምትመካበት የሚሳኤል እና የሮኬቶች ማምከኛ ‘አይረን ዶም’ ምንድን ነው?

በቅርብ ወራት እስራኤል ሐማስ ከጋዛ፣ ሄዝቦላ ከሊባኖስ እንዲሁም ከየመን የሁቲ አማፂያን የሚተኮሱባትን ሚሳኤሎች ዒላማቸውን ከመምታታቸው በፊት ታመክናለች።

እስራኤል ከየትኛውም ወገን የሚሰነዘሩባትን የሚሳኤል እና የሮኬት ጥቃቶችን ለመከላከል “አይረን ዶም” የተባለውን የአየር ላይ ጥቃት ማምከኛ ሥርዓትን ነው የምትጠቀመው።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ፍልስጥኤማዊው ታጣቂ ቡድን ሐማስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶን ወደ እስራኤል ሲያስወነጭፍ ይህ የጥቃት መከላከያ ሥርዓት በርካቶቹን በማክሸፍ አገሪቱ ረድቷታል ተብሎ ይነገራል።

ነገር ግን አንዳንዶቹ የሐማስ ሮኬቶች ሳይከሽፉ ቀርተው በመኖሪያ አካባቢዎች ላይ ወድቀዋል።

ማክሰኞ ዕለትም ኢራን ወደ እስራኤል ያስወነጨፈቻቸውን ሚሳዔሎች አይረን ዶምን በመጠቀም ማምከኗን እየተናገረች ነው።

አይረን ዶም ምንድን ነው? እንዴት ነው የሚሰራው?

አይረን ዶም ከአጭር ርቀት የሚወነጨፉ የጦር መሳሪያዎችን እንዲያከሽፍ ተደርጎ የተሰራ የአየር መከላከያ ሥርዓት ሲሆን፣ በየትኛውም የአየር ሁኔታ ውስጥ ተግባሩን የሚያከናውን ነው።

የተተኮሱ ተወንጫፊ መሳሪያዎችን ለመለየት ራዳር የሚጠቀም ሲሆን፣ ተወንጫፊዎቹ በመኖሪያ አካባቢዎች ወይም በባዶ ሜዳ ላይ የሚወድቁ መሆናቸውን ቀድሞ የመለየት አቅም አለው።

ይህ የአየር እና የከባድ መሳሪያ ጥቃቶችን በመለየት ለማክሸፍ የሚያገለግለው ሚሳኤል፣ በእስራኤል ውስጥ በአስር የተለያዩ ቦታዎች ላይ ተጠምዶ ይገኛል።

እነዚህ ፀረ ሚሳኤሎች እያንዳንዳቸው ሦስት ወይም አራት ፀረ ሚሳኤል መተኮሻ መሳሪያዎች ያሏቸው ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው አስከ 20 የሚደርሱ ሚሳኤሎችን ይይዛሉ።

አይረን ዶም የጥቃት መከላከያ የእስራኤልን የአየር ክልል በመጣስ አደጋን ያስከትላል በተባለ በእያንዳንዱ ሮኬት ላይ ሁለት ‘ታሚር’ የተባሉት ሁለት አክሻፊ ሚሳኤሎች ይተኮሱበታል።

እያንዳንዳቸው አስሩ የአየር መከላከያ የሚሳኤል ቡድኖችን ለመሥራት አስከ 100 ሚሊዮን ዶላር ወጪን እንደሚጠይቅ የዓለም አቀፍ የስትራተጂክ ጥናት ማዕከል ግምቱን አስቀምጧል።

የተወንጫፊ የጦር መሳሪያዎች ማክሸፊያው ‘አይረን ዶም’ ሥርዓት፣ ምንም እንኳን ወጪው ከፍተኛ ቢሆንም ስጋት የሚሆኑ ጥቃቶችን ለማክሸፍ የሚተኮሰው ሕዝብ በሚበዛባቸው ስፍራ ላይ በመውደቅ ጉዳት ያደርሳሉ ተብለው የተለዩትን ነው።

አይረን ዶምን ማነው የሠራው? መቼ ሥራ ላይ ዋለ?

አይረን ዶም የተሠራው ደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው እስላማዊው ቡድን ሄዝቦላህ እና እስራኤል እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2006 ላይ ግጭት ውስጥ ከገቡ በኋላ ነው።

በወቅቱ ሄዝቦላህ በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል በማስወንጨፍ በርካታ ዜጎቿን የገደለ ከባድ ውድመትን አድርሷል።

ከዚህ ጥቃት ከዓመት በኋላም ራፋኤል የተባለው ዘመናዊ ወታደራዊ ቁሶች አምራች የሆነው የእስራኤል መንግሥት የመከላከያ ተቋም አዲስ የሚሳኤል ጥቃት መከላከያ ሥርዓት እንደሚገነባ እቅዱ ይፋ ተደርጎ ነበር።

አይረን ዶም ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ ላይ የዋለው በአውሮፓውያኑ 2011 ነው። በወቅቱ አሁን ድረስ ሐማስ ከሚቆጣጠረው ጋዛ ሰርጥ በደቡባዊ እስራኤል ክፍል ወደምትገኘው ቢርሼባ ከተማ ሚሳኤሎችን በተኮሰበት ወቅት ማክሰሸፍ በቻለበት ጊዜ ነው።

በ2019 (እአአ) የእስራኤል ጥብቅ ወዳጅ የሆነችው አሜሪካ እራሷ ያላትን ፓትሪዮት የተባለውን ፀረ ሚሳኤል ሥርዓትን ለማጠናከር፣ አይረን ዶምን ከእስራኤል በመግዛት እንደምትሞክረው አሳውቃለች።

የአሜሪካው ፓትሪዮት ፀረ ሚሳኤል የሚሠራው ከአይረን ዶም ጋር በተመሳሳይ መንገድ ነው። ነገር ግን የአሜካው ፓትሪዮት የሚያከሽፈው ከረጅም ርቀት የሚነሱ የአውሮፕላን እና ሌሎች የሚሳኤል ጥቃቶችን ነው።

አይረን ዶም ግን የአጭር ርቀት ተወንጫፊዎችን ጭምር በመምታት የሚያከሽፍ በመሆኑ ይህንን ሚሳኤል ከራሷ ጋር በማቀናጀት ለመጠቀም አሜሪካ ፍላጎቷን ገልጻለች።

አይረን ዶም ምን ያህል ውጤታማ ነው?

እስራኤል በአውሮፓውያኑ 2012 በሐማስ አማካይነት ከጋዛ ከተተኮሱባት ሮኬቶች መካከል የአይረን ዶም የመከላከያ ሥርዓት 84 በመቶውን አክሽፏል ብላለች።

በወቅቱ ፀረ ሚሳኤል መከላከያው 573 ፀረ ሚሳኤሎችን ተኩሶ ከእነዚህ መካከል 421 የሚሆኑትን የሐማስ ሮኬቶችን አየር ላይ በመምታት ማክሸፍ ችሏል በማለት ብቃቱን ትገልጸዋልች።

ነገር ግን በዩናይትድ ኪንግደም የማንችስተር የቴክኖሎጂ ኢኒስቲቲዩት የመከላከያ ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ቴዎዶር ፖስቶል፣ አይረን ዶም ከተተኮሱት ሮኬቶች ማክሸፍ የቻለው ምናልባት 10 በመቶውን ካልሆነም ምንም ማክሸፍ አልቻለም ብለዋል።

በ2021 (እአአ) ሐማስ ከጋዛ ሰርጥ ሦስት ሺህ ሚሳኤሎችን መተኮሱን እና ከእነዚህም ውስጥ አይረን ዶም 90 በመቶውን በማክሸፍ በከፍተኛ ሁኔታ ስኬታማ ነው በማለት የእስራኤል ጦር ሠራዊት ምስክርነት ሰጥቷል።

አሁን ተባብሶ በቀጠለው የሐማስ እና የእስራኤል ግጭት ጅማሬ ላይ ሐማስ ወደ እስራኤል 5,000 ሮኬቶችን ማስወንጨፉን ቢገልጽም፣ እስራኤል ግን ቁጥሩ በግማሽ ያነሰ ነው ትላለች።

እስራኤል ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ሐማስ ተኩሶብኛል ከምትላቸው 2,500 ሮኬቶች መካከል አይረን ዶም የአየር የመከላከያ ሥርዓት 153ቱን ያከሸፈ መሆኑን እና ሌሎቹ ግን በሜዳ ላይ ወይም እዚያው ጋዛ ሰርጥ ውስጥ የወደቁ ናቸው ሲል የአገሪቱ ጦር ኃይል አስታውቋል።

ነገር ግን ሐማስ በቅርቡ በፈጸማቸው የሮኬት ጥቃቶች በደቡባዊ እስራኤል እና በቴል አቪቭ ከተማ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን እና መቁሰላቸውን የእስራኤል የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።