ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባሕር ዳር እና ጎንደር ከተሞችን ጨምሮ በአማራ ክልል ግጭቶች መቀጠላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ
በባሕር ዳር እና ጎንደር ከተሞች ጨምሮ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች በታጣቂዎች እና በመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች መካከል የሚደረገው ግጭት መጠናከሩን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
በመዲናዋ ባሕር ዳር ጨምሮ በታሪካዊቷ ጎንደር አንዳንድ አካባቢዎች ከባድ የተባለ ግጭት እንዳለ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በመንግሥት ፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት መባባሱ የተሰማው የፌደራሉ መንግሥት በአማራ ክልል የተፈጠረውን የፀጥታ መደፍረስ በአጭር ጊዜ እቆጣጠራለሁ ባለበት ወቅት ነው።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያስፈጽመው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ “በዘራፊ ወንበዴ ቡድን” የታወከውን ሰላም በሕግ ማስከበር እርምጃ ክልሉን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው በአጭር ጊዜ እመልሳለሁ ብሏል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ዋና ሰብሳቢ እና የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አግልግሎት ዳይሬክትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በአማራ ክልል የተከሰተውን ችግር ለመፍታት ክልሉን በአራት ኮማንድ ፖስቶች በማዋቀር ሕግን የማስከበር ሥራ እንደሚከናወን እሁድ ምሽት በሰጡት ማብራሪያ ላይ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለፋኖ ታጣቂዎች ቅርበት ያላቸው አንቂዎች እና መገናኛ ብዙኃን የፋኖ ታጣቂዎች የአማራ ክልል መዲና የሆነችውን ባሕር ዳር ከተማን በከፊል መቆጣጠራቸውን እና በከተማዋ በሚገኘው አየር ማረፊያ እንዲሁም በክልሉ መገናኛ ብዙኃን አቅራቢያ ከፍተኛ የመንግሥት ሠራዊት መስፈሩን ይገልጻሉ።
በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ተብላ ወደተመዘገበችው ላሊበላ ጨምሮ ወደ ጎንደር እና ባሕር ዳር ከተሞች የሚደረጉ በረራዎች እንደተቋረጡ ናቸው። የኢንተርኔት ግንኙነትም ተቋርጦ ይገኛል።
ባሕር ዳር
የክልሉ መዲና ባሕር ዳር ትናንት እሁድ ሐምሌ 30/2015 ዓ.ም. ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ሲደረግባት መቆየቷን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከባሕር ዳር ያነጋገርናቸው ነዋሪ እንደገለጹት፣ በከተማዋ በተለይ እሁድ ከሰዓት በኋላ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ ነበር።
ቀበሌ 14 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ምሽቱን የተኩስ ሩምታ ሲሰማ ማምሸቱን የተናገሩት ነዋሪው፣ አብዛኛው ሰው ቤት ውስጥ በመሆኑ የተኩስ ድምጽ ከመስማት ባለፈ ግጭቱ ከየት ወደ የት እያመራ እንደሆነ ማወቅ አለመቻላቸውን ገልጸዋል።
እሁድ ከተኩሱ መጀመር በፊት አካባቢውን ለመቃኘት ከቤታቸው ወጥተው እንደነበረ የሚጋሩት ነዋሪው፣ የከተማው መንገድ በድንጋይ እና በእንጨት መዘጋጋቱን እና የነዋሪዎችም ሆነ የታጠቁ ሰዎች እንቅስቃሴ እንደማይታይ ይናገራሉ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ይህ የባሕር ዳር ነዋሪ የመንግሥት ሠራተኛ ሲሆኑ፣ በፀጥታው ምክንያት ሁሉም እንቅስቃሴ ስለተገደበ ወደ ሥራ ቦታ መሄድም የሚታሰብ አይደለም ብለዋል።
ነዋሪው ዛሬ ጠዋትም አልፎ አልፎ በክልሉ መዲና ተኩስ እንደሚሰማም ነዋሪው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ጎንደር
ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ጀምሮ ውጥረት ውስጥ ያለቸው ጎንደር እሁድ ሐምሌ 30/2015 ዓ.ም. በከተማዋ ውስጥ ከባድ የሚባል ውጊያ መካሄዱን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
አንዳንድ የጎንደር ማዕከላዊ ቦታዎች በስፋት በፋኖ ቁጥጥር እንደሚገኙ እና በከተማዋ ዳርቻ ባሉ ቦታዎች ደግሞ የመንግሥት መከላከያ ሰፍሮ እንደሚገኝ ይገልጻሉ።
እሁድ በጎንደር ፒያሳ እና ብልኮ ተብለው በሚጠሩት የከተማዋ አካባቢዎች እየተካሄደ የነበረው የተኩስ ልውውጥ እያየለ መጥቶ እንደነበረ ተናግረዋል።
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲጠቅስ ያልፈለጉ ነዋሪዎች ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 1/2015 ዓ.ም. ላይም የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ ገልጸዋል።
ነዋሪው በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ባለው የፀጥታ ስጋት ምክንያት የሰዎች እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ ተገድቦ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ላሊበላ
ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ ግጭቶች የተካሄዱባት ታሪካዊቷ ላሊበላ ከተማ በአሁኑ ወቅት አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት ከከተማዋ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የሹምሽሃ አየር ማረፊያ በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር መግባቱን ተከትሎ በከተማዋ እና በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት ነግሶ እንደነበር ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪው እንዳሉት እሁድም ሆነ ዛሬ ሰኞ በላሊበላ ከተማ እና በዙሪያዋ የተኩስ ድምጽ አልተሰማም፣ የተለየ የፀጥታ ችግርም አልገጠመም።
ነገር ግን በስተሰሜን በኩል ከሰቆጣ አቅጣጫ እና በደቡብ ደግሞ ሐሙሲት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የከባድ መሳሪያ ድምጽ ከርቀት እንደሚሰማ ነዋሪው ተናግረዋል።
ደብረ ብርሃን
ቢቢሲ ያነገራቸው ከአዲስ አበባ 130 ኪሎ ሜትር ለይ የምትገኘው የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች እንደተናገሩት፣ እሁድ ዕለት በከተማዋ ዙርያ የጥይት ተኩስ ድምጽ ይሰማ የነበረ ሲሆን፣ ወጣቶችም ወደ ጎዳናዎች በመውጣት ተቃውሞ ሲያሰሙ ነበር ብለዋል።
ከደብረ ብርሃን ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው ዋና መንገድ ዝግ መሆኑን የተናገሩት ነዋሪዎች በከተማዋ ውስጥ ያለው እንቅስእቃሴ ውስን መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።
“በስጋት ውስጥ ነው ያለነው” የሚሉት ነዋሪዎቹ ዛሬ ማለዳም በከተማዋ ያለው ሁኔታው ከእሁድ የተለየ አለመሆኑን ገልጸዋል።
ወልዲያ
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው የወልዲያ ነዋሪዎች በከተማዋ የተኩስ ድምጽ ባይኖርም አገልግሎቶች ዝግ መሆናቸውን እና እንቅስቃሴዎች መገታታቸውን ገልጸዋል።
ከተማዋ ያለችበትን ሁኔታ ለቢቢሲ የገለጹት ነዋሪዎች ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 1/2015 ዓ.ም. ላይ በከተማው የመንግሥትም ሆኑ የግል ተቋማት ሙሉ በሙሉ ዝግ ናቸው ብለዋል።
በከተማዋ የመከላከያ ሠራዊት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን እና በአንድ ቦታ የሚሰበሰቡ ወጣቶችን በኃይል እየበተኑ መሆኑንም ተናግረዋል።