ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግሥት የሚያዋቅረውን ኮሚቴ እንደማይቀበሉት ሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች አስታወቁ
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግሥት የሚመሰረትበት ሰነድ በቀጣይ ሳምንት ይፋ እንደሚሆን መገለጹን ተከትሎ በትግራይ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሂደቱ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታወቁ።
ሳልሳይ ወያነ፣ ባይቶና እና የትግራይ ነጻነት ፓርቲ በኮሚቴው ላይ የገለልተኝነት እና የአሳታፊነትም ጥያቄ በማንሳት ከኮሚቴው ጋር ግንኙነት እንደሌላቸውም ሐሙስ የካቲት 09/2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ኮሚቴው በምን ሕግ፣ ደንብ እና አሰራር እንደተቋቋመ ግልጽ መልስ እንዳልተሰጣቸው የብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ (ባይቶና) ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ፀጋ ዘአብ ካህሱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኮሚቴውን ህወሓት አቋቁሟል ብለዋል እንደሚያምኑ የተናገሩት ሊቀመንበሩ ይህም በፕሪቶሪያ ከተደረገው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት መሠረት ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
“በዋናነት ሂደቱ ነው አሳታፊ መሆን ያለበት እንጂ ውጤቱ አይደለም። የህወሓት ኮሚቴ ውስጥ ገብተን አስተዋጽኦ የምናደርገው ነገር የለም” በማለት ከሂደቱ ራሳቸውን ማግለላቸውን ገልጸዋል።
ምሥረታውን ለማካሄድ የተቋቋመው አስተባባሪ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሌ/ጄኔራል ታደሰ ወረደ የካቲት 08/2015 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጊዜያዊ መንግሥቱ የሚተዳደርበትን ሰነድ የማዘጋጀቱ ሥራ እየተገባደደ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሊቀመንበሩ ይህንን የኮሚቴዎቹን መግለጫ በመጥቀስ “ሂደቱ እንዳለቀ እና በቅርብ ቀናት ውስጥ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚመሠረት ነው። ባለቀ ጉዳይ ላይ መግባት ብዙም አስተዋጽኦ እናደርጋለን ብለን ስላላመንን ራሳችንን ከኮሚቴው አርቀናል” ብለዋል።
ኮሚቴው የትግራይ ኃይሎች አዛዥ ሌ/ጄኔራል ታደረሰ ወረደ እና አቶ ሙሉ ወርቅ ኪዳነማርያምን ጨምሮ ዘጠኝ አባላት ያሉት ሲሆን፣ ሦስት ከትግራይ ኃይሎች፣ ሦስት ከህወሓት እና ሦስት ከሲቪክ ማኅበራት የተውጣጡ መሆናቸው በወቅቱ ተገልጿል።
ጊዜያዊ መንግሥቱን ለመመሥረት የሚከናወነው የሥራ ሂደት ሁሉንም አሳታፊ እንደሆነ እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበራት፣ ሕዝብን ያሳተፈ እና ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ በሆነ ሁኔታ ለማካሄድ እንደተሞከረም ጄኔራሉ አውስተዋል።
ሊቀመንበሩ በበኩላቸው በዚህ አይስማሙም ከኮሚቴው ዘጠኝ አባላት ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲ፣ የነጻ ማኅበር፣ የምሁራን እና የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮችም ሆኑ የትግራይ ባለ ድርሻ አካላት የሉም ይላሉ።
“ዘጠኙ በአንድ ጽህፈት ቤት የተመረጡ አብዛኛዎቹም የህወሓት የሥራ አስፈጻሚ አባላት እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ናቸው። ሌሎቹም በተግባር የህወሓት አባላት ናቸው። አባላቱ የተመረጡት በህወሓት በውስጠ ፓርቲ ስብሰባ ላይ ነው” ብለዋል ዶክተር ፀጋ ዘአብ።
በኮሚቴው ምርጫ እንዳልተሳተፉ የሚናገሩት ዶክተር ፀጋ ዘአብ፣ የኮሚቴው አባላት መግለጫ ሲሰጡ በነበረበት ወቅት በነበረውም መድረክም እንዳልታደሙ አስረድተዋል።
ኮሚቴው ጥያቄ የተነሳበት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን በትግራይ ካሉ ሲቪል ማኅበረሰብ አባላትም እንደሆነ የፓርቲው ሊቀመንበሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከሲቪል ማኅበረሰቡ አባላት ኮሚቴ መራጩም፣ ሰብሳቢውም ተመራጩ የህወሓት አባል መሆኑ አይጎዳም ወይ የሚሉ ጥያቄዎች መቅረባቸውንም ገልጸዋል።
የባይቶና ፓርቲ ሊቀመንበሩ የፌደራል መንግሥቱም ይህንን በትኩረት ሊከታተለው እና ኃላፊነቱን ሊወጣም እንደሚገባ አጽንኦት አሳስበዋል።
ሂደቱን ላይ ተቃወሞ ያሰሙት ፓርቲዎች ሁኔታውን ዝም ብለው እንደማይመለከቱትና በቀጣይም አማራጭ የሚሉትን ጊዜያዊ መንግሥት ምስረታም እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል በአጭር ጊዜ ውስጥ ይመሠረታል በተባለው ጊዜያዊ መንግሥት ላይ በክልሉ ባሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል የተሰማውን ቅሬታን በተመለከተ ከህወሓት በኩልአስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ይህ ሂደት ለትግራይ ሕዝብ ወሳኝ የታሪክ ሂደት ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የፌደራሉ መንግሥት እና የትግራይ ተደራዳሪ ቡድን አባላት ውይይት ላይ የበጀት ጉዳይ በተነሳበት ወቅት በቀዳሚነት የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት ከተቋቋመ በኋላ እንደሚለቀቅ ተገልጾ ነበር።
ከበጀትም ጋር በተያያዘ የጊዜያዊ መንግሥት ምሥረታ እንደ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡንም የትግራይ ተደራዳሪ አቶ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ አስታውቀው ነበር።