ፎክስ ኒውስ ስም በማጥፋት በቀረበበት ክስ 787.5 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማማ

ፎክስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፎክስ ኒውስ፣ ዶሚኒዮን የተባለው ድምጽ መቁጠሪያ ስርዓት የሚያስተዳደር ኩባንያ ባቀረበበት የስም ማጥፋት ክስ 787.5 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማማ።

እአአ በ2020 ከተካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ፣ ዶሚኒዮንን በተመለከተ ፎክስ ኒውስ የሠራው ዘገባ ላይ ስም የማጥፋት ክስ ተከፍቶ ነበር።

ዶሚኒዮን ክሱን ሲመሠርት ካሳ እንዲከፈለው የጠየቀው 1.6 ቢሊዮን ዶላር ነበር።

በምርጫው ወቅት ለቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተሰጡ ድምጾች ተጭበርብረዋል በሚል ፎክስ ሐሰተኛ ዘገባ በማሰራጨቱ፣ ዶሚኒዮን ንግዱ ጉዳት እንደደረሰበት ገልጿል።

የፎክስ ኒውስ ኃላፊ ሩፔት መርዶክን ጨምሮ ሌሎችም የሚድያው አመራሮች ቃላቸውን በፍርድ ቤት ሰጥተዋል።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ ፎክስ ኒውስ ላይ ከተከፈቱ የስም ማጥፋት ክሶች ትልቁ በመሆኑ ትኩረት ስቦ ቆይቷል።

ፎክስ ገንዘብ ለመክፈል ከተስማማ በኋላ “ከፍ ላለ የጋዜጠኝነት ሥራ እንተጋለን” ሲል መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫው ዝርዝር መረጃ ባይሰጥም ፎክስ በፍርድ ቤት ዶሚኒዮንን በተመለከተ ሐሰተኛ መረጃ ናቸው ተብለው ከቀረቡት በተወሰኑት እንደሚስማማ ገልጿል።

የዶሚኒዮን ኃላፊ ጆን ፖሎስ እንዳሉት ስምምነቱ ከገንዘብ ክፍያ በተጨማሪ ፎክስ “ውሸት መናገሩን እና ተቋሙ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን እንዲያምን” ያስገድዳል።

“ውሸት አሉታዊ ውጤት ያስከትላል። ከሁለት ዓመት በፊት ስለ ዶሚኒዮን የተሰራጩ ውሸቶች መላው አሜሪካን አጥለቅልቀዋል። ይህም ለሴራ ትንተና መነሻ ሆኗል። ድርጅታችንንም ጎድቷል” ብለዋል።

ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሊታይ ቀነ ቀጠሮ ተይዞ ሳለ ነው ሁለቱ ድርጅቶች ስምምነት ላይ መድረሳቸው የተሰማው።

የፎክስ ጠበቆች መጀመሪያ ላይ የተጠየቀውን የ1.6 ቢሊዮን ዶላር ካሳ የተጋነነ ነው ሲሉ ተቃውመዋል።

ፎክስ በበኩሉ “ትልቁ ጉዳት” ብሎ የሚወስደው የንግግር ነጻነት ላይ የደረሰው ገደብ እንደሆነ ገልጿል።

ለትራምፕ የተሰጡ ድምጾች ተጭበርብረዋል የሚለው የወግ አጥባቂው ፎክስ ዘገባ ሐሰተኛ መሆኑን ዶሚኒዮን ሲነቅፍ ቆይቷል።

የሕግ ቡድኖች ባደረጉት ምርመራ መሠረት የፎክስ አመራሮች እና ጋዜጠኞች የ2020ው ምርጫው ተጭበርብሯል ብለው ባያምኑም ዘገባዎቻቸው ይህንን የሚያንጸባርቁ ነበሩ።

የፎክስ ኃላፊ መርዶክ ስለ ዶሚኒዮን በፎክስ የተላለፉ ዘገባዎችን “በጣም ጤናማ ያልሆኑ” ሲሉ ቢገልጿቸውም ምንም እርምጃ አልወሰዱም።

የፎክስ ኃላፊ ሩፔት መርዶክ እና ልጃቸው ላቻላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የፎክስ ኃላፊ ሩፔት መርዶክ እና ልጃቸው ላቻላን

የፎክስ ጋዜጠኛ ሾን ሄነቲም ዘገባዎቹን “አንዳችም አላምናቸውም” ሲል በግሉ ቢናገርም ዘገባዎቹን ከማስተላለፍ አልታቀበም።

ሆኖም ግን ፎክስ ዘገባዎቹ ከዐውድ ውጭ እንደተወሰዱበት ተከራክሯል።

የገንዘብ ክፍያ ስምምነት ላይ ከመድረሳቸው በፊት ጉዳዮን የያዙት ዳኛ ስለ ዶሚኒዮን የተላለፉት ዘገባዎች ሐሰተኛ ይዘት እንዳላቸው ማረጋገጫ ተገኝቷል።

አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች የገንዘብ ስምምነቱ በጎ ውጤት እንደሆነ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በሲራከስ ዮኒቨርስቲ መምህርና የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ላይ ባለሙያ ሮይ ጉተርማን “ስድስት ሳምንታት የሚወስድ ሂደት ሁሉንም ወገን ያታክት ነበር። ፎክስን የሚያዋርድ ሂደትም ነበር የሚሆነው። ሆኖም ግን ፎክስ በፍርድ ቤት ቢፈረድበት ከፍተኛ ገንዘብ ነበር የሚቀጣው” ብለዋል።

ዶሚኒዮን ከፎክስ ውጭ ኦኤኤን እና ኒውስማክስ የተባሉ ወግ አጥባቂ ሚዲያዎች ላይም ክስ መሥርቷል።

ሌላ የድምጽ መስጫ ማሽን የሠራ ድርጅትም ፎክስ ስሜን አጥፍቷል ብሎ የ2.7 ቢሊዮን ዶላር ክስ መሥርቷል። በተጨማሪም የትራምፕ ደጋፊዎች ሩዲ ጁልያኒ፣ ሲድኒ ፖዌል እና ማይክ ሊንደልን ከሷል።