ፑቲን አገራቸውን ለመከላከል አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠነቀቁ

የሩሲያው ፕሬዝዳንት የአገራቸው የግዛት አንድነት አደጋ ላይ የሚወድቅ ከሆነ ማንኛውንም ዓይነት እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠነቀቁ።

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ይህንን ያሉት ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌቪዥን ቀርበው በሰጡት መግለጫ ነው።

ጦርነቱ ተባብሶ በሩሲያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር የነበሩ በርካታ ቦታዎችን የዩክሬን ኃይሎች መልሰው እየተቆጣጠሩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ነው ፑቲን መግለጫ የሰጡት።

በዚህም “የአባት አገርን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ለመከላከል እንዲሁም የሕዝቡን ደኅንነት ለመጠበቅ” አስፈላጊ ነው ያሉትን “ከፊል የክተት ጥሪ” ይፋ አድርገዋል።

ፑቲን “የአገራችን የግዛት አንድነት ስጋት ላይ የሚወድቅ ከሆነ፣ ሕዝባችንን ለመከላከል ያለንን ሁሉ አማራጭ እንጠቀማለን” ሲሉ ተናግረዋል።

ጨምረውም “እደግመዋለሁ! ባሉን አማራጮች ሁሉ የአገራችንን የግዛት አንድነት እና ነጻነታችንን እናስከብራለን” በማለት በአጽኖት ተናግረዋል።

ይህ የክተት ጥሪ “በሠራዊቱ ውስጥ ያገለገሉትን እና የተጠባባቂ ኃይል አባላት የሆኑትን ዜጎች ብቻ የሚመለከት ነው” ብለዋል ፑቲን።

በተያያዘም የሩሲያው የመከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሾይጉ እንዳረጋገጡት፣ 300,000 የሚሆኑ የአገሪቱ ተጠባባቂ ኃይል አባላት ሠራዊቱን እንዲቀላቀሉ እንደሚጠሩ ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ፑቲን ይፋ ያደረጉት ከፊል የክተት ጥሪም ወታደራዊ ልምድ ያለቸውን የአገሪቱን ዜጎች እንደሚያካትት መከላከያ ሚኒስተሩ አረጋግጠዋል።

ፑቲን፣ ሩሲያ ላይ ስጋት ለመፍጠር እየሞከሩ ናቸው ያሏቸው የኒውክሌር ጦር መሣሪያ የታጠቁ አገራት “የወቅቱ ነፋስ ወደ እነሱ አቅጣጫ ሊዞር እንደሚችል ሊያውቁ ይገባል” በማለት አስጠንቅቀዋል።

ወራት ባስቆጠረው ሩሲያ በዩክሬን ላይ በከፈተችው ከባድ ጦርነትን፣ ሩሲያ በርካታ የዩክሬን መሥራቃዊ ክፍሎችን ለመቆጣጠር ችላ ነበር።

ባለፉት ሳምንታት ግን የዩክሬን ኃይሎች የተወሰዱባቸውን ግዛቶች መልሰው እየተቆጣጠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ ከምዕራባውያን አገራት ውግዘት የገጠማት ሲሆን፣ በርካታ ማዕቀቦችንም ተጥለውባታል።

የዩክሬን ኃይሎች በሩሲያ ሠራዊት ላይ የበላይነትን አግኝተው አሸናፊ እንዲሆኑም ምዕራባውያኑ አገራት ቢሊዮን ዶላሮችን የሚያወጡ ወታደራዊ ድጋፎችን በይፋ እየሰጡ ነው።

ጦርነቱ በዕቅዳቸው መሠረት እንዳልሄደላቸው የሚነገረው ፕሬዝዳንት ፑቲን ሠራዊታቸውን ለማጠናከር አሁን የክተት ጥሪ ማወጃቸው የበለጠ ደም መፋሰስን ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።