በታይላንድ የጠፋው ጀርመናዊ ነጋዴ አስከሬን በማቀዝቀዣ ውስጥ ተገኘ

በታይላንድ የጠፋው ጀርመናዊ ነጋዴ አስከሬን ተቆራርጦ በማቀዝቀዣ ውስጥ መገኘቱን ባለስልጣናቱ ተናገሩ።

መጥፋቱ የተገለጸው የ62 ዓመቱ ሃንስ ፒተር ማክ በደቡባዊ ታይላንድ ኖንግ ፕሩ ግዛት ውስጥ በሚገኝ የኪራይ ቤት የተቆራረጠው የአስከሬኑ አካልም በቆሻሻ መጣያ ከረጢት ተጠቅልሎ በማቀዝቀዣ በያዝነው ሳምንት ሰኞ ምሽት መገኘቱን ፖሊስ አስታውቋል።

በግለሰቡ ግድያም የተጠረጠሩ ሁለት ጀርመናውያን በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በምስራቃዊቷ ፓታያ ከተማ ከታይላንዳዊቱ ባለቤቱ ጋር ነዋሪነቱን አድርጎ የነበረው የሪል እስቴት ቢዝነስ ባለቤት ፒተር መጥፋቱ የተሰማው ከስምንት ቀናት በፊት ነበር።

ፖሊስ እንደተናገረው ሁለት ተጠርጣሪዎች ማክን ለመግደል በማሴር፣ ከገደሉት በኋላ አስከሬኑን አጓጉዘው መደበቃቸውን ነው።

ፒተር ማክ ለመጨረሻ ጊዜ የታየው በፓታያ ከተማ ውስጥ መርሴዲስ ሴዳን መሆኑን ቤተሰቦቹ መጥፋቱን ለማመልከት ያወጡት ማስታወቂያ አትቷል።

በዚሁ ማስታወቂያም ላይ ፒተር ማክ ያለበትን ቦታ ላመላከተ ግለሰብ 3 ሚሊዮን የታይላንድ ገንዘብ ወይም 86 ሺህ ዶላር ሽልማት አቅርበው ነበር።

መኪናው እሁድ እለት ኖንግ ፕሩ ግዛት ውስጥ በሚገኝ የጋራ መኖሪያ ቤት የመኪና ማቆሚያ ቦታ ላይ መገኘቱን ዘገባዎች አመልክተዋል።

መርማሪዎች በቤቱ ውስጥ ከአስከሬኑ በተጨማሪ መጋዝ፣ ጥቅል ፕላስቲክና ማያያዣ ሽቦዎች ማግኘታቸውን በታይላንድ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የወጡ ዘገባዎች ያስረዳሉ።

በተጨማሪም በመኪናው መቀመጫዎች፣ መሪና ዳሽቦርድ እንዲሁም ሌሎች ክፍሎች ላይ ለጽዳት የሚጠቀሙበትን ፈሳሽ የሚያሳዩ ምልክቶች መገኘቱም ተገልጿል።

የፖሊስ ኃላፊው ሜጀር ጀነራል ቴራቻይ ቻምናንሞር ግኝቶቹ “ማስረጃዎችን የመደበቅና የማጥፋት ፍላጎት እንደነበር የሚጠቁሙ ናቸው” ሲሉ ለባንኮክ ፖስት ተናግረዋል።

ከማክ የባንክ ሂሳብ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንደጠፋ ባለስልጣናቱ እንደደረሱበት የኖንግ ፕሩ ፖሊስ አዛዥ ታዌ ኩድታሌንግ አስረድተዋል።

አክለውም የማክስ አስከሬን በአካባቢው የተቀረጸ የሲሲቲቪ ቪዲዮን ክትትል በማድረግ መገኘቱን ቢገልጹም ተጨማሪ ማብራሪያ አልሰጡም።

የማክ ባለቤት በጠፋበት ዕለት ምሳ አብረው ለመብላት ቀጠሮ ይዘው የነበረ ሲሆን በቦታው ባለመገኘቱ ስልክ መደወሏን አንድ የአገር ውስጥ ሚዲያ ዘግቧል።

መልሶ እንደሚደውል የጽሁፍ መልዕክት እንደረሳትና ምሽት አራት ሰዓት ላይ እንዲሁ ከደንበኛ ጋር እንደሆነ የሚገልጽ ሌላ የጽሁፍ መልዕክት ደርሷታል።

ነገር ግን የማክ ባለቤት ለታይላንድ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገረችው በአምስት ዓመታት ግንኙነታቸው ውስጥ ምንም ዓይነት የጽሁፍ መልዕክት ልኮ እንደማያውቅ ነው።