ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በትግራይ መፈንቅለ መንግሥት እና ሥርዓት አልበኝነት የተባሉት ክስተቶች ምንድን ናቸው?
በትግራይ የተካሄደውን ጦርነት ያበቃውን የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተከትሎ በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመሄድ እርስ በርስ ሲካሰሱ ቆይተዋል።
በተለይ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እውቅናን ያላገኘው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ከተካሄደ በኋላ በድርጅቱ ሊቀመንበር እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት መካከል ያለው ውዝግብ እየተባባሰ ቀጥሎ ነበር።
ይህንንም ለማርገብ በክልሉ ያሉ ሲቪል ማኅበራት፣ የአገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ጥረት ሲያደርጉ ቆይተው ፍሬ ሳያፈራ ቢቆይም ከአንድ ሳምንት በፊት የሃይማኖት መሪዎች ዶክተር ደብረ ጽዮንን እና አቶ ጌታቸውን በማቀራረብ እንዲነጋገሩ እና አለመግባባቱን እንዲፈቱ መንገድ ከፍተው ነበር።
ሁለቱ የህወሓት ዋነኛ ሰዎች እየተካረረ እና ጋብ እያለ የቆየውን አለመግባባታቸውን ለመፍታት የሚያስችሉ ውይይቶችን ያደርጋሉ ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በአቶ ጌታቸው የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር ተቀናቃኙ የህወሓት ቡድን “በይፋ መፈንቅለ መንግሥትን ወደ መፈጸም ተሸጋግሯል” ሲል ከሷል።
በክልሉ የተካሄደውን ጦርነት ያስቆመውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ተከትሎ የተቋቋመው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት እና የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ እና የድርጅቱ ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረ ጽዮን ወልደሚካኤል መካከል ያለው አለመግብባት ለወራት የዘለቀ ነው።
ህወሓት ባለፈው ዓመት ተከታታይ ስብሰባዎችን በማድረግ በድርጅቱ ውስጥ ያለውን ችግር ለመፍታት ቢጥርም ሳይሳካለት ቀርቶ ውዝግቡ አደባባይ ወጥቶ ሁለቱም ወገኖች እርስ በርስ ሲካሰሱ ቆይተዋል።
በተለይ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው አለመግባባት ሊቀመንበሩ የሚመሩት ወገን ከሕግ ውጪ ነው የተባለውን ጠቅላላ ጉባኤ ነሐሴ 7/ 2016 ዓ.ም. መቀለ ውስጥ በማድረግ አቶ ጌታቸውን እና ከእሳቸው ጋር ያሉትን አመራሮች ከህወሓት ኃላፊነት እና አባልነት ማገዱ የተፈጠረውን ችግር የበለጠ አባብሶታል።
ከዚያም በኋላ አንዳቸው እንዳቸውን በሕገወጥነት በመክሰስ ሲወቃቀሱ የቆዩ ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዜያትም መግለጫዎችን ሲያወጡ እና ጊዜያዊ አስተዳደሩም ሕግ ለማስከበር እርምጃ እንደሚወስድ ሲዝት ቆይቷል።
የቀጠለው መካሰስ
ባለፈው እሁድ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት በኩል የወጣው መግለጫ በዶ/ር ደብረ ጽዮን የሚመራው ቡድን መፈንቅለ መፈንቅለ መንግሥት ወደ መፈጸም መድረሱን በመግለጽ የከሰሰ ሲሆን፣ በሌላኛው ወገን ያለው አካልም አስካሁን ያለው ነገር የለም።
መስተዳደሩ ጨምሮም ቡድኑ “የመንግሥት ሥራዎችን ከማደናቀፍ አልፎ ይፋዊ መፈንቅለ መንግሥትን ወደ መፈጸም እና በከክልሉ ሥርዓት አልበኝት እንዲሰፍን ወደ ማድረግ ተሸጋግሯል” በማለት ለዚህም የተቀናጀ ተግበራትን እያከናወነ ነው ሲል ከሶታል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በህወሓት ሊቀመንበር የሚመራው ቡድንን በመፈንቅለ መንግሥት በመፈጸም እና ሥርዓት አልበኝነትን ለማስፋፋት በተደራጀ ሁኔታ እየሠራ ነው ሲል አንዳንድ ክስተቶችን በደፈናው ጠቅሷል።
ከዚህ አንጻርም በመቀለ ከተማ፣ በሰሜን ምዕራብ እና በማዕከላዊ ዞኖች እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች ማሳያ ናቸው ከማለት ውጪ በዝርዝር ኣለው ነገር የለም።
እንዲሁም ባለፉት ሳምንታት “ከትግራይ ሠራዊት አመራሮች ጋር” መግባባት ላይ መድረሱን እና ሁሉንም የክልሉን የመንግሥት መዋቅሮች ለመቆጣጠር መቃረቡን በስፋት እየገለጸ መሆኑንም አመልክቷል።
በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ውስጥ በአብዛኛው የትግራይ ፀጥታ ኃይል የሚባለው ሠራዊት እና አመራሩ ባለፉት ወራት ከሁለቱም ወገን ገለልተኛ ሆኖ ቆይቷል።
‘የመዝገብ ቤት ኃላፊዋ መታፈን’
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በተቀናቃኙ የህወሓት ቡድን እየተወሰዱ ናቸው ከሚላቸው ሕገወጥ እርምጃዎች መካከል በቅርቡ በታሪካዊቷ አክሱም ከተማ የተከሰተው የሚጠቀስ ነው።
በጊዜያዊ አስተዳደሩ የተሾሙት የማዕከላዊ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሰለሞን ማዓሾ ስለዚሁ ጉዳይ ለቢቢሲ ትግርኛ አንደተናገሩት “ሕገ ወጥ” ያሏቸው የሚሊሻ፣ የፖሊስ እና የፀጥታ አባለት በከተማዋ ወደሚገኝ የማዕከላዊ ዞን ጽሕፈት ቤት መዝገብ ቤት በመሄድ የጽህፈት ቤቱ ማህተም [ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚጠቀምበት] አገልግሎት ላይ እንዳይውል ከልክለዋል።
አስተዳዳሪው እንደሚሉት ይህ ከተፈጸመ ከአራት ቀን በኋላ ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም. ተመሳሳይ ድርጊት ተጠናክሮ ቀጠለ። አምስቱ ሰዎች በዕለቱ ማህተም ለመንጠቅ መሞከራቸውን በመግለጽ ይህም ለሚመለከተው አካል [ጊዜያዊ አስተዳደሩ] ደብዳቤ እንዲጽፍ እንዳስገደደው ተናግረዋል።
በወቅቱ የመዝገብ ቤት ሠራተኛዋ ማኅተሙን ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኗ በማግስቱ ከሰዓት በኋላ ከቢሮ ወጥታ ወደ ቤቷ ስትሄድ “በመንገድ ላይ ጠልፈው” ከአክሱም ወደ አድዋ ከተማ ወሰደዋታል ሲሉ አቶ ሰለሞን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
በጉዳዩ ላይ ፖሊስ የጀመረው ምርመራው ከተጠናቀቀ በኋላ በመንግሥት አካል ዝርዝር መረጃ እንደሚሰጥ ገልጸው፣ ይህ ድርጊት ግን ሆን ተብሎ የመንግሥት መዋቅርን እና ሥራ ለማደናቀፍ የተደረገ ነው ሲሉ ከሰዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራ ቡድን በአክሱም እና በአድዋ ከተሞች ከነዋሪዎች ጋር ለማካሄድ አቅዶት በነበረው ስብሰባ ላይ እንቅፋት እንዳጋጠመው የሚታወስ ነው።
በተለይም በሽሬ ከተማ ተጠርቶ በነበረው ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ከእናቶች በተሰማ ጩኸት እና ረብሻ ምክንያት አቶ ጌታቸው ስብሰባውን እንዲያቋርጡ ተገደዋል።
የማዕከላዊ ዞን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሰለሞን ማዓሾ በአክሱም የተፈጸመው ድርጊት በሽሬ የተከሰተው ቀጣይ ተግባር ነው ብለው ያምናሉ።
“ክስተቱ ‘ስልጣንን ከስር ጀምረን ወደ ላይ መቆጣጠር አለብን’ ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው። በእርግጥ የአክሱሙን ድርጊት የፈጸሙት ሰዎች ‘ማን ነው የላካቸው? ከፀጥታ አካላት ጋር ምን ግንኙነት አላቸው? ከመጋረጃው በስተጀርባ ያለው ማን ነው? የሚሉት ምርመራ እየተካሄደ ነው” ብለዋል።
ሁለቱም የህወሓት አመራር ቡድኖች አንዱ ለሌላው ዕውቅና የነፈጉ ሲሆን በዶ/ር ደብረፂዮን የሚመራው ክንፍ በጊዜያዊ አስተዳደር የተሾሙትን የዞን አስተዳዳሪዎች ውድቅ በማድረግ የራሱ አዳዲስ አስተዳዳሪዎችን እየሾመ ይገኛል።
ከጥቂት ወራት በፊት የሰሜን ምዕራብ ዞንን እንዲያስተዳድር በጊዚያዊ አስተዳደሩ የተሾሙት አቶ ተክላይ ፍቃዱ “ነባሩ አስተዳደር ኃላፊነት ለአዲሱ አመራር ለማስረከብ ፍቃደኛ አይደለም። ይህ ተግባር ደግሞ ውንብድና ነው” ሲል ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
አቶ ተክላይ ፍቃዱ እስካሁን ስራውን እንዳልጀመረ ምንጮቻችን ገልጸዋል።
በዚህም ከትግራይ ዞኖች መካከል አንዱ የሆነው አካባቢው ከጊዜያዊ አስተዳደር ቁጥጥር ውጪ መሆኑን የውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ።
የከንቲባው ጉዳይ
እንዲህ ዓይነቶቹ ክስተቶች ከጊዜያዊ አስተዳደሩ መቀመጫ ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ብቻ የተገደቡ ሳይሆኑ፣ የክልሉ ዋና ከተማ አስተዳደርም ከጊዜያዊ መንግሥቱ ቁጥጥር ውጪ ይገኛል።
በቅርቡ ነባሩ የከተማዋ ከንቲባ ተነስተው በዶ/ር ረዳኢ በርኸ በተባሉ አዲስ ከንቲባ ተተክተዋል።
ይህን ተከትሎ ጊዚያዊ አስተዳደሩ በዶ/ር ደብረጽዮን ቡድን የተወከለው ከንቲባ የሚተላለፍ ‘ምንም ዓይነት ትዕዛዝም ሆነ ውሳኔ’ ተፈጻሚነት እንደሌለው በከተማው ወደሚገኙ ጽሕፈት ቤቶች ባሰራጨው ደብዳቤ አስታውቆ ነበር።
ይሁን እንጂ ይህ በአቶ ጌታቸው በሚመራው አስተዳደር የተሰራጨው ደብዳቤ ከመቀለ ምክር ቤት ተቃውሞ ገጥሞታል። ደብዳቤውም ተግባራዊ አለመደረጉ ቢቢሲ አረጋግጧል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለጊዜያዊ ፕሬዝዳንቱ እውቅና እንደማይሰጥ እና እሳቸውን ለመተካት እንደሚሠራ ይፋ ያደረገው በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው ቡድን ከፌደራል መንግሥት እና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አስታውቆ ነበር።