ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኬንያው ተቃውሞ "የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ" እንደሆነ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናገሩ
የኬንያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ረቡዕ ፣ሰኔ 18/ 2017 ዓ.ም በመላ አገሪቱ የተካሄደውን ተቃውሞ "ሰላማዊ መስሎ የታየ የሽብር ተግባር" እና "የመንግሥት ለውጥ ለማድረግ የተደረገ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ሙከራ" ነው አሉ።
ሚኒስትሩ ቢያንስ 10 ሰዎች በተገደሉበት ተቃውሞ ፖሊስ ከፍተኛ ኃይል ተጠቅሟል መባሉንም አስተባብለዋል።
ኪፕቹምባ ሙርኮሜን የጸጥታ ተቋማት ከፍተኛ የሆነ "ትንኮሳ ቢገጥማቸውም ላሳዩት አስደናቂ ትዕግስት" እና የተካሄደውን "የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በማክሸፍ" ላደረጉት እገዛ አመስግነዋል።
ረቡዕ ዕለት በተካሄደው ተቃውሞ ከተገደሉት 10 ሰዎች በተጨማሪ 300 የፖሊስ አባላትን ጨምሮ ከ400 በላይ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
" በሰላማዊ ተቃውሞ ስም የተካሄደውን ጥቃቶች ፣ ዘረፋዎች፣ ወሲባዊ ጥቃቶች እንዲሁም ውድመት የተፈፀመበትን ጭካኔ የተሞላበት ወንጀል እናወግዛለን" ብለዋል ሚኒስትሩ።
ቁልፍ የመንግሥት ተቋማት እና ቢሮዎችም በተቃውሞው ኢላማ መደረጋቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ዘጠኝ ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት መፈፀሙንና ከእነዚህ ውስጥ አምስቱን ሰብሮ በመግባት አምስት የጦር መሣሪያዎች ተሰርቀዋል ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ንብረትነታቸው የፖሊስ፣ የመንግሥት እና የሰላማዊ ሰዎች የሆኑ በርካታ ተሽከርካሪዎች መውደማቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ሙርኮሜ አክለው በተቃውሞው በትክክል የደረሰውን ጉዳት እና የጥቃቱን ሁኔታ ለማወቅ ምርመራ እየተካሄደ ነው ብለዋል።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በታቃውሞው የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 16 መሆናቸውን የገለጸ ሲሆን ሁሉም የተገደሉት በጥይት ተመትተው ነው ብሏል።
ከተገደሉት መካከል በሙኩሩ ነዋሪ የነበረው የ19 ዓመቱ ዴቪድ ምዋንጊ ይገኝበታል።
የወጣቱ እናት ለቢቢሲ እንደገለጸችው ዴቪድ የተገደለው በተቃውሞው ተሳትፎ ሳይሆን ታናሽ ወንድሙን ከትምህርት ቤት ለማምጣት በሄደበት ነው።
ሪቻል ኒያምቡራ ምዋንጊ ልጇ ጭንቅላቱን በጥይት ተመትቶ መሞቱን በእንባ ተሞልታ ገልጻለች። " ስቃይ ውስጥ ነው ያለሁት" ብላለች።
" ዴቪድ መካኒክ ለመሆን ወደ ኮሌጅ ለመግባት ተስፋ አድርጎ ነበር። የመጀመሪያ ልጄ ነው፤ ረዳቴም ነበር። ውሃ መቅዳት አሊያም የሆነ ነገር ስፈልግ የምልከው እሱን ነበር። ስኳር ድንች እየሸጥኩ ነው የምተዳደረው። የያዝኩት ሲያልቅብኝ የምልከው እሱን ነበር"
ሌላኛው የ17 ዓመቱ ታዳጊ ተማሪ ዴኒስ ኒጁጉናም ከመዲናዋ ናይሮቢ ሰሜን ምዕራብ 170 ኪሎ ሜትር በምትርቀው ሞሎ ውስጥ ተተኩሶበት ተገድሏል።
የታዳጊው እናት ጀሲንታ ጋቶኒ " በተቃውሞው ውስጥ ሆኖ ይሁን ተባራሪ ጥይት መትቶት አላውቅም።ነገር ግን በጥይት መመታቱን፣ መውደቁንና እዚያው መሞቱን ሰምቻለሁ" ብላለች።
ልጄ ገና ሕጻን ነበር። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ነበር። ሕልሞች ነበሩት። እኔም በእርሱ ላይ ተስፋ ነበረኝ። ሆስፒታል ሄጄ አስክሬኑን ለማየት አቅም የለኝም"
ተቃውሞው የተካሄደው ባለፈው ዓመት የተካሄደውን ፀረ መንግሥት ተቃውሞ አንደኛ ዓመት ለማሰብ ነበር።
ለዚህም ረቡዕ ዕለት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ መንግሥት ላይ ያላቸውን ቁጣ ለመግለጽ እና የፖሊስ ጭካኔ እንዲያከትም ለመጠየቅ አደባባይ ወጥተዋል።
በርካታ ተቃዋሚዎችም " ሩቶ ሥልጣኑን ሊለቅ ይገባል" ሲሉ ድምጻቸውን ያሰሙ ሲሆን የሰላማዊ ተቃውሞ ምልክት የሆነ የዛፍ ዝንጣፊ በመያዝ በአገዛዙ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ አሳይተዋል።
መንግሥት ተቃውሞው በቴሌቪዥን እና በሬዲዮ በቀጥታ እንዳይሰራጭ አግዶ የነበረ ሲሆን የናይሮቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔውን በመቀልበሱ እገዳው ተነስቷል።
የመብት ተቆርቋሪ ቡድኖችም ፖሊስ እና መንግሥት የወሰዱትን እርምጃ አውግዘዋል።
የኬንያ የሕግ ማኅበረሰብ "የጸጥታ ኃይሎች ያሳዩት አላስፈላጊ እብሪት እና ጭካኔ ነበር" ሲል ይህም ወደ አላስፈላጊ የሕይወት መጥፋት መርቷል ብሏል።
የሰብዓዊ ተሟጋች ቡድኑ ረቡዕ ዕለት ሦስት የፖሊስ መኮንኖች መጎዳታቸውን ገልጿል።