በዘውዱ ሃፍቱ ግድያ በተሰጠው ፍርድ ቤተሰቧ "ደስተኛ አለመሆኑን" ገለጸ

ከሁለት ዓመት በፊት መቀለ ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ በተገደለችው ዘውዱ ሃፍቱ ሞት የተጠረጠሩ ሁለት ተከሳሾች የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ሲፈረድባቸው ቤተሰቧ በውሳኔው ደስተኛ አለመሆናቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።

በትግራይ ክልል የመቀለ ከተማ መካከለኛ ፍርድ ቤት ዛሬ ሐምሌ 4/2017 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በአንደኛ ተከሳሽ ያሬድ ገብረሥላሴ በላይ እና በሁለተኛ ተከሳሽ አንገሶም ኃይለማሪያም ንጉሥ ላይ ብይን ሰጥቷል።

የመቀለ ከተማ መካከለኛ ፍርድ ቤት በዘውዱ ሃፍቱ ግድያ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ሲሰጥ የቤተሰብ አባላት ወደ ችሎት እንዳይገቡ ተከልክለው እንደነበር እህቷ ብርቱካን ለቢበሲ ትግርኛ ተናግራለች።

ዛሬው ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ ውሳኔውን ባስተላላፈበት ችሎት ላይ ቤተሰቡ በችሎቱ እንዳይገኝ እንደተደረገ አመልክታ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግን ከመግለጽ ተቆጥባለች።

ብርቱካን በተሰጠው ብይን ቤተሰቡ "ደስተኛ አለመሆናቸውን" ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የከሳሽም የተከሳሽም ቤተሰቦች ወደ ችሎት እንዳይገቡ መከልከላቸውን ቢቢሲ ማወቅ ችሏል።

ብይኑን ያስተላለፈው የመቀለ መካከለኛ ፍርድ ቤት አንደኛ እና ሁለተኛ ተከሳሾች ያሬድ ገብረሥላሴ በላይ እና አንገሶም ኃይለማርያም በወንጀሉ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።

የዘውዱ ሃፍቱ ታናሽ እህት የሆነችው ብርቱካን ለቢቢሲ እንደተናገረችው "ከዚህ የበለጠ የቅጣው ውሳኔ ሊሰጥ ይገባ ነበር" በማለት በብይኑ ላይ ቤተሰቧ ያለውን ቅሬታ ገልጻለች።

የተፈጸመው "የጭካኔ ግድያ በመሆኑ የሞት ፍርድ ያሰጥ ነበር " ያለችው የሟች ሃፍቱ እህት፣ ቤተሰብም ለሁለት ዓመታት በቆየው የፍርድ ሂደት ይህንኑ ሲጠብቅ ነበር ብላለች።

የፍርድ ቤቱን ብይን ችሎቱን ተከታትለው ከወጡ ጋዜጠኞች ቤተሰቧ የፍርድ ውሳኔውን መስማቱን የተናገረችው ብርቱካን፣ ተከሳሾቹ በዘውዱ ላይ ለፈጸሙት "አሰቃቂ ግድያ የዕድሜ ልክ እስራት ሳይሆን ከዚያ በላይ መቀጣት አለባቸው ብለን ነው የምናምነው" ብላለች።

የዘውዱ ሃፍቱ ቤተሰብ ከፍርድ ቤቱ ከዕድሜ ልክ እስራት በላይ በተከሳሾቹ ላይ ቅጣት ያስተላልፋል ብለው ሲጠብቁ እንደነበርም አመልክታለች።

የተፈጸመው "የጭካኔ ግድያ በመሆኑ የሞት ፍርድ ያሰጥ ነበር " ያለችው የሟች ሃፍቱ እህት፣ ቤተሰብም ለሁለት ዓመታት በቆየው የፍርድ ሂደት ይህንኑ ሲጠብቅ ነበር ብላለች።

ዘውዱ ሃፍቱ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለችው ከሁለት ዓመት በፊት በነሐሴ 13/2015 ዓ.ም. መቀለ ከተማ ውስጥ ነበር።

የመቀለ ከተማ ነዋሪ የነበረችው ዘውዱ ሃፍቱ ነሐሴ 13/2015 ዓ.ም. የአሸንዳ በዓል ለመታደም ተዘጋጅታ እንዲሁም የጓደኛዋን ልደት ለማክበር በወጣችበት በከተማዋ አዲ ሓውሲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ምሽት ላይ በሁለት ግለሰቦች ባልተወቀ ምክንያት በተፈጸመባት ጥቃት ለሞት ተዳርጋለች።

ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎ ለፍርድ ቤት ያቀረባቸው ያሬድ ገብረሥላሴ በላይ እና አንገሶም ኃይለማርያም በወረዳ እንዲሁም በዞን ፍርድ ቤት ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን በመግለጽ መከራከራቸውን እህቷ ብርቱካን ለቢቢሲ ተናግራለች።

ዘውዱ ተወልዳ ያደገችው በመቀለ ከተማ ማይ አንበሳ በሚባል አካባቢ ነው። ቤተሰቧ ካሏቸው ሦስት ልጅች መካከልም ናት።

የዘውዱ ታናሽ እህት ብርቱካን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለቤተሰቡ እረፍት "ለሌሎች ደግሞ ማስተማሪያ ይሆናል" የሚል እምነት እንደነበራቸው ገልጻለች።