ኪም ጆንግ ኡን፣ ፕሬዝዳንት ፑቲን እና ሌሎች መሪዎች በቻይና የመከላከያ በዓል ላይ ሊገኙ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በሚቀጥለው ሳምንት በቤጂንግ በሚካሄደው የመከላከያ ትርኢት በዓል ላይ እንደሚታደሙ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ይህም ኪም ጆንግ ኡን የሚያደርጉት የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የመሪዎች ግንኙነት እንደሆነ ታምኗል።
"የድል ቀን" እየተባለ የሚጠራው የቻይና የመከላከያ ትርኢት በዓል ከጃፓን ጋር ያደረገችው ጦርነት እና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት 80ኛ ዓመት መታሰቢያ ነው።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበዓሉ ላይ ይታደማሉ ከተባሉ የ26 አገራት መሪዎች ውስጥ አንዱ ናቸው።
መሪዎቹ የሚሰባሰቡት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኪም ጆንግ ኡንን ለማግኘት እንደሚሹ ባሳወቁ በቀናት ውስጥ ነው።
ቻይና በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር አውሮፕላኖችን፣ ታንኮችን እንደሁም የፀረ ድሮን ስርዓቷን ጨምሮ የታጠቀቻቸውን ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች በበዓሉ ላይ ታሳያለች።
በመከላከያ በዓሉ የቻይና ጦር ሠራዊት አባላት እና ጡረታ የወጡ ወታደሮችን ጨምሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ከቲያንመን አደባባይ ተሰልፈው ትርኢት ያሳያሉ ተብሏል።
ለ70 ደቂቃ የሚቆየው ወታደራዊ ትርኢት በተንታኞች እና በምዕራቡ ዓለም ጥብቅ ክትትል የሚደረግበት እንደሆነ ይጠበቃል።
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ የቤጂንግን የቅርብ አጋር ፒዮንግያንግን አስርት ዓመታትን ለዘለቀው ወዳጅነታቸው ያሞገሰ ሲሆን፤ ሁለቱ አገራት "ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት" መተባበራቸው ይቀጥላሉ ብሏል።
የኪም ጆንግ ኡን በበዓሉ መታደም ትልቅ አንድምታ ያለው ሲሆን፤ እ.አ.አ በ2015 በተደረገው የቻይና የድል ቀን ፒዮንግያንግ ከፍተኛ ሹሟን ቾ ሪዮንግ-ሂን ልካ ነበር።
ኪም በቤኪንግ መሀል ከተማ በመከላከያ ትርኢት ላይ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን እና ከቻይናው ዢ ጋር አንድ ላይ መታየት ከዓይን የማይጠፋ ምስል እንደሚያስቀር እሙን ነው።
ከዚህም ባሻገር ግን የመሪዎቹ በበዓሉ መታደም ለፕሬዝዳንት ዢ ቁልፍ የዲፕሎማሲ አሸናፊነት ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ስምምነት ለማውረድ እየጣሩ ነው።
ባለፈው ሳምንት ደግሞ ኪም ጆንግ ኡንን ለማግኘት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
የቻይናው ፕሬዝዳንት የጂኦፓለቲካ ጨዋታው ላይ ቁልፍ ተጨዋች መሆናቸውን በተፅዕኗቸው እያመላከቱ ነው።
መሪዎቹ የሚገናኙበት ወቅትም ቁልፍ ሲሆን፤ በመጪው ጥቅምት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቀጣናው ጉብኝት ሲያደርጉ ፕሬዝዳንት ዢን የማግኘት ፍላጎት እንዳላቸው ዋይት ሐውስ ጠቁሟል።
ኪም ቤጂንግን ከጎበኙ ስድስት ዓመት የሆናቸው ሲሆን፤ እ.አ.አ በ2019 የአገራቱን 70ኛ ዓመት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማክበር ቤጂንግ ከትመው ነበር።
ዓለም አቀፍ ጉብኝት ላይ እምብዛም የሆኑት ኪም በ2018 ግን ቤጂንግን ሦስት ጊዜ ጎብኝተዋል።
የቻይናን ድል ቀን የመከላከያ ትርኢት አብዛኞቹ የምዕራባዊያን አገራት በከፊል በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከፑቲን ጋር ባላቸው ልዩነት ምክንያት ይታደሙታል ተብሎ አይጠበቅም።
ጃፓን ቀደም ብላ በዓሉ "ፀረ ጃፓን መልዕክት ያለው" ነው በሚል የዓለም መሪዎች እንዳይታደሙ አሳስባለች።















