ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጆ ባይደን 'በፍጥነት በሚስፋፋ" የፕሮስቴት ካንሰር መያዛቸው ተገለፀ
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን "በፍጥነት በሚስፋፋ" የፕሮስቴት ካንሰር መያዛቸው በሕክምና ተረጋገጠ።
የቀድሞው ፕሬዝደንት ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫው ላይ እንዳለው የ82 ዓመቱ ጆ ባይደን የተገኘባቸው ፕሮስቴት ካንሰር ወደ አጥንታቸው እየተስፋፋ እንደሚገኝ ገልጿል።
ሥልጣናቸውን ጥር ወር ላይ የለቀቁት ባይደን ባለፈው ሳምነት አርብ ባደረጉት የሽንት ምርመራ ካንሰር እንዳለባቸው መታወቁ ተገልጿል።
ጆ ባይደን ሕመማቸው "ከፍተኛ ደረጃ" በሚል የተለየ ሲሆን ይህም እንደ ዩኬ የካንሰር ምርምር ማዕከል ከሆነ በፍጥነት የሚዛመት ነው።
ባይደን እና ቤተሰባቸው የሕክምና አማራጮችን እየፈተሹ መሆኑን አስታውቀዋል።
የቀድሞ ፕሬዝደንቱ ጽሕፈት ቤት ካንሰሩ ሆርሞን ሴንሴቲቭ መሆኑን አስታውቆ በሕክምና በቁጥጥር ስር ሊውል ይችላል ማለት እንደሆነ አብራርቷል።
ጆ ባይደን የምርመራ ውጤታቸው ይፋ ከሆነ በኋላ ከደጋፊዎቻቸውም ሆነ ከተቀናቃኞቻቸው ወገን መልዕክቶችን ተቀብለዋል።
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ እርሳቸው እና ሜላኒያ ትራምፕ "የጆ ባይደን የሕክምና ውጤት ሲሰሙ ማዘናቸውን" ገልጸዋል።
"ለጂል እና ለቤተሰባቸው መልካም ምኞታችንን መግለጽ እንወዳለን" ሲሉ የቀድሞዋን ቀዳማይ እመቤት ጠቅሰው መልዕክታቸውን አስፍረዋል።
"ጆ በፍጥነት እና በጥሩ ሁኔታ እንዲሻለው እንመኛለን።"
የቀድሞዋ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ በበኩሏ በኤክስ ገጿ ላይ እርሷ እና ባለቤቷ ዳግ ኤምሆፍ የባይደንን ቤተሰብ በፀሎታቸው እንደሚያስቡ አስፍራለች።
"ጆ እጅ መስጠት አይወድም፤ ይህንን ተግዳሮት ሁል ጊዜም ሕይወትን እና አመራርን በሚጋፈጥበት ተመሳሳይ ጥንካሬ፣ የመቋቋም ብቃት፣ እና ተስፋ እንደሚጋፈጠው አውቃለሁ" ብላለች ሃሪስ።
ባራክ ኦባማ በኤክስ ገጻቸው ላይ እርሳቸው እና ባለቤታቸው ሚሼል "የባይደን መላው ቤተሰብን እንደሚያስቧቸው" ጽፈዋል።
ባራክ ኦባማ እአአ ከ2009 እስከ 2017 ድረስ ፕሬዝደንት ሆነው አሜሪካን ሲያስተዳድሩ ጆ ባይደን ምክትላቸው ሆነው አገልግለዋል።
ኦባማ እንዳሉት "ለካንሰር የተሻሻለ ሕክምና ለማግኘት ከጆ የበለጠ የጣረ የለም፣ እናም ይህን ፈተና ለብዙዎች አርዓያ በሚሆን መልኩ እና ክብር እንደሚታገለው እርግጠኛ ነኝ። በፍጥነት፣ ሙሉ በሙሉ እንዲድን እንጸልያለን።"
እአአ በ 2016 የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ "ካንሰር ሙንሾት" የተሰኘ ባይደን የሚመሩት ፕሮግራም አስጀምረው ነበር።
ጆ ባይደን በካንሰር መያዛቸው የተሰማው የ2024 ፕሬዝደንታዊ ምርጫን በእድሜ እና በጤና ምክንያት እንዲያቋርጡ በተደረገ በዓመቱ ነው።
ባይደን በአሜሪካ ታሪክ እድሜያቸው ገፍቶ አገሪቱን ያስተዳደሩ ብቸኛ ግለሰብ ናቸው።
ዲሞክራቱ ባይደን የዛሬ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ የምረጡኝ ዘመቻ እያካሄዱ የነበረ ሲሆን በሰኔ ወር ላይ ከዲሞክራት ተቀናቃኛቸው የአሁኑ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ያደረጉት እና በቴሌቪዥን በተላለፈው የምርጫ ክርክር ላይ ያሳዩት የወረደ አቋም በርካታ ትችት አስከትሎባቸው ነበር።
ከዚያ በኋላም ምክትላቸው ካማላ ሃሪስ የዲሞክራት እጩ በመሆን እንድትተካቸው ተደርጓል።
ፕሮስቴት ካንሰር ወንዶችን በስፋት ከሚያጠቁ የካንሰር ዓይነቶች መካከል ሁለተኛው ነው።
የአሜሪካ በሽታ መቆጣጠር እና መከላከል ማዕከል (ሲዲሲ) ከ100 ወንዶች መካከል 13ቱ ፕሮስቴት ካንሰር እንደሚያዙ ያሳያል።
እንደ ሲዲሲ መረጃ ከሆነ ዕድሜ ለዚህ ካንሰር አጋላጭ ከሆኑት ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው።
የአሜሪካ ካንሰር ሶሳይቲ የበላይ ኃላፊ እና የፕሮስቴት ካንሰር ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ዊሊያም ዳህኡት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ይፋ በሆነው የባይደን የምርመራ ውጤት መሰረት ያለባቸው ካንሰር በባህሪው በፍጥነት የሚስፋፋ ነው
"በአጠቃላይ ካንሰር ወደ አጥንት የተዛመተ ከሆነ የሚድን ነው ብለን አናምንም" ብለዋል ዶ/ር ዳህኡት።
የሕክምና ባለሙያው ይሁን አንጂ በርካታ ሕሙማን ለሚሰጣቸው የመጀመርያ ሕክምና የተሻለ ምላሽ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
"ሰዎች ካንሰሩ እንዳለባቸው ከታወቀ በኋላ በርካታ ዓመታት ይኖራሉ" ብለዋል።
ዶ/ር ዳህኡት እንደ ቀድሞው ፕሬዝዳንት ያለ ምርመራ የተደረገለት ግለሰብ ምልክቶቹን ለመቀነስ እና ካንሰር ያለባቸውን ህዋሶች እድገት አዝጋሚ ለማድረግ ሆርሞናል ቴራፒ ሊታዘዝለት እንደሚችል ጠቅሰዋል።
ባይደን ዋይት ሐውስን ከለቀቁ በኋላ ከሚዲያ ዓይን ርቀው የቆዩ ሲሆን በጣም ውሱን ጊዜያቶች ብቻ ለሕዝብ ታይተው ነበር።
በሚያዝያ ወር ለአካል ጉዳተኞች መብት የሚሰራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በቺካጎ ባዘጋጀው ጉባዔ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር አድርገው ነበር።
በግንቦት ወር ዋይት ሐውስን ከለቀቁ ለመጀመርያ ጊዜ ከቢቢሲ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ጆ ባይደን የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳውን ለማቋረጥ የወሰኑት ውሳኔ "ከባድ" እንደነበር ተናግረዋል።
ባይደን የጤናቸውን ሁኔታ በሚመለከት በቅርቡ ጥያቄዎች ቀርቦላቸው ነበር።
በግንቦት ወር ዘ ቪው በተሰኘው የቴሌቪዥነ ፕሮግራም ላይ በቀረቡበት ወቅት ዋይት ሐውስ በነበሩባቸው የመጨረሻ ጊዜያት አእምሯቸው እንደ ከዚህ ቀደሙ የሰላ እንዳልነበር እና የማስታወስ ችግር (cognitive decline) አጋጥሟቸው ነበር የሚለውን አስተባብለዋል።
"ያንን የሚያሳይ ምንም ነገር የለም" ነበር ያሉት።
ባይደን ለበርካታ ዓመታት በካንሰር ላይ ለሚደረግ ጥናት እና ምርምር በርካታ አስተዋጽኦዎችን አድርገዋል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022 እርሳቸው እና ባለቤታቸው ካንሰር ሙንሾት ኢንሼቲቭ የተሰኘ ድርጅት አቋቁመው በ2047 በካንሰር ምክንያት የሚሞቱ ከ4 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለመከላከል የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮችን ለመደገፍ ሲሰሩ ነበር።
ባይደን የመጀመርያ ልጃቸውን በ2015 በሞት ያጡት በጭንቅላት ካንሰር ምክንያት ነው።