ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትራምፕ አስተዳደር ለሐርቫርድ የሚሰጠውን ገንዘብ ለማቋረጥ የወሰነውን ውሳኔ ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገ
የአሜሪካ የፌደራል ፍርድ ቤት የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ላይ ያደረገውን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ቅነሳ ውድቅ አደረገ።
ዳኛ አሊሰን ቡሮውስ መንግሥት ለምርምር የሚውለው 2 ቢሊየን ዶላርን ሲያግድ የአይቪ ሊግ ኮሌጅን የንግግር ነጻነት መብቶች ጥሷል ብለዋል።
ውሳኔው ለሐርቫርድ ትልቅ ድል ሲሆን ዋይት ሐውስ ደግሞ ይግባኝ እንደሚያቀርብ ተናግሯል።
የትራምፕ አስተዳደር በሚያዝያ ወር የገንዘብ ድጋፉን ሲያግድ ኮሌጁን ፀረ ሴማዊ እና በ"አክራሪ ግራ ክንፍ" ርዕዮተ ዓለሞች እና በዘር መድልኦ ከሷል።
ሌሎች ሦስት የአይቪ ሊግ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ኮሎምቢያ፣ ፔን እና ብራውን፣ ወደ ፍርድ ቤት ከመሄድ ይልቅ አስተዳደሩ ባቀረባቸው ተመሳሳይ ውንጀላዎች የተነሳ ለአደጋ የተጋለጠውን የገንዘብ ድጋፍ ለማስቀጠል ከትራምፕ ጋር ስምምነት ፈጥረዋል።
ቦስተን መቀመጫቸውን ያደረጉት ዳኛ ቡሮውስ ረቡዕ ዕለት በሰጡት ብይን "ፍርድ ቤቱ የእገዳ ትዕዛዞችን እና የማቋረጫ ደብዳቤዎችን የአሜሪካን ሕገመንግሥት ስለሚጥስ እንዲነሱ እና እንዲሻሩ ወስኗል" ብለዋል።
አስተዳደሩ ለካምብሪጅ፣ ማሳቹሴትስ ኮሌጆች የሚሰጠውን ተጨማሪ የፌደራል የገንዘብ ድጋፍ እንዳያቆም ያገዱ ሲሆን መንግሥት በተሰጡ የጥናት እና ምርምር ድጋፎች ላይ ያስቀመጠውን ክልከላ አንስተዋል።
ዋይት ሐውስ ወዲያውኑ ይህንን "አስደንጋጭ ውሳኔ" እንደሚቃወም ገልጾ፣ ዳኛው በቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የተሾሙ "አክቲቪስት" መሆናቸውን እና የውሳኔ ሀሳቡን የሚደግፍ ምንም ዓይነት ውሳኔ ሊያደርጉ የማይችሉ ሲል ተችቷቸዋል።
ረዳት የፕሬስ ፀሐፊ ሊዝ ሁስተን "ሐርቫርድ የግብር ከፋይ ገንዘብን የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት የለውም፤ እናም ለወደፊቱ በድጋፍ ለሚሰጥ ገንዘብ ብቁ አይደለም" ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አላን ጋርበር በድረ ገጻቸው ላይ በሰጡት መግለጫ "ፍርዱ የሐርቫርድ ሕገ መንግሥታዊ እና የአሰራር መብቶችን ያረጋግጣል" ብለዋል።
"የውሳኔውን አንድምታ መገምገማችንን እንቀጥላለን፣ ተጨማሪ የሕግ ሂደቶችን እንከታተላለን እንዲሁም ተልዕኳችንን ለመወጣት የምንፈልገውን ከባቢያዊ ለውጥ በማስታወስ ሥራችንን እንቀጥላለን" ሲሉም አክለዋል።
ዳኛ ቡሮውስ በ84 ገፆች ባስተላለፉት ውሳኔያቸው ላይ ሐርቫርድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተቋሙን "አስቸግሮታል" ያለውን ፀረ ሴማዊነት ለመቋቋም የበለጠ መስራት ነበረበት ብለዋል።
ዳኛው "ሐርቫርድ የጥላቻ ባህሪን በመታገሱ ተሳስቷል" ሲሉ በውሳኔ ደብዳቤያቸው ላይ አስፍረዋል።
ነገር ግን ፀረ ሴማዊነትን መዋጋት የትራምፕ አስተዳደር የአገሪቱን አንጋፋ እና ሀብታም ዩኒቨርሲቲ ለመቅጣት ያለው "እውነተኛ ዓላማ" እንዳልሆነ ተናግረዋል።
መንግሥት "በዚህች አገር ዋና ዋና ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ለታለመ፣ ርዕዮተ ዓለም ተኮር ጥቃት ፀረ ሴማዊነትን እንደ ጭምብል ተጠቅሞበታል" ሲሉ ተችተዋል።
ዳኛ ቡሮውስ ከዚህ ቀደም ሐርቫርድ ዓለም አቀፍ ተማሪዎችን እንዳያስተናግድ ትራምፕ የሚያደርጉትን ጥረት አግደዋል።
ዩኒቨርሲቲው በሚያዝያ ወር የተጣለበትን የገንዘብ ድጋፍ እገዳ በማስመልከት የትራምፕ አስተዳደርን የከሰሰ ሲሆን ፀረ-ሴማዊነትንም ለመዋጋት ቃል ገብቷል ።
የሐርቫርድ ፕሬዝዳንት ምንም ዓይነት መንግሥት "የግል ዩኒቨርስቲዎች የሚያስተምሩትን፣ ማንን ተቀብለው መቅጠር እንደሚችሉ፣ የትኛውን የጥናት ዘርፍ መከተል እንደሚችሉ መወሰን የለበትም" ብለዋል።
ትራምፕ የሐርቫርድ ከቀረጥ ነፃ መብት ለመሻር እና ዩኒቨርሲቲው በፌዴራል የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኘውን የባለቤትነት መብት እንደሚቆጣጠሩ ዝተዋል።
መንግሥት የፌደራል መንግሥቱን እገዳ ለማስቆም የሚያስችል ስምምነት ከሐርቫርድ ጋር ሲወያይ ቆይቷል።
ትራምፕ ዩኒቨርሲቲው ከ500 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ክፍያ እንዲከፍል እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።