ባሎች ሚስቶቻቸው በደመወዝ ቢበልጧቸው ደስተኛ ይሆናሉ ወይስ ይከፋሉ?

ሰዎች የሚያገኙት ገንዘብ ከአእምሮ ጤናቸው ጋር ትስስር አለው። ማንኛውም ሰው ራሱን በዙሪያው ካሉ ሰዎች ጋር ማነጻጸሩም አይቀርም።

ዴቭ የተባለው አባት ልጆቹን ቤት ሆኖ ያሳድጋል።

"ሚስቴ ከእኔ በላይ ገንዘብ ማግኘቷ በስሱም ቢሆን ኩራቴን ይጋፋብኛል" ይላል።

ቶም ቤተሰብን ማስተዳደርን በተመለከተ ለሌሎች ወንዶች መናገር "እንደ ሴት" እንድንወሰድ ያደርገናል ይላል።

ዴቭ እና ቶም በጥንዶች መካከል ስላለው የገቢ ልዩነት በተሠራ ጥናት ተሳትፈዋል።

ብራንደን ሚስቱ ከእሱ በላይ ገቢ ስላላት ቤተሰቦቹ እንደሚያጣጥሉት ይናገራል።

ሦስቱ ወንዶች ቤት ሲውሉ፣ ከእነሱ የበለጠ ገቢ የሚያገኙ ሚስቶቻቸው ያስተዳድሯቸዋል።

ወንዶች ዋነኛ የገቢ ምንጭ እና የቤት አስተዳዳሪ ሆነው በሚሳሉበት ማኅበረሰብ ውስጥ ሚስቶቻቸው አስተዳዳሪ መሆናቸው ለማኅበረሰባዊ ትችት እንደዳረጋቸው ሦስቱ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

ከወንዶች የበለጠ ገቢ የሚያገኙ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ ነው። በጥንዶች መካከል ያለው ግንኙነትም እየተለወጠ መጥቷል።

የጥንዶች የኃይል ሚዛን እየተቀየረ ነው። በብዛት ከፍተኛ ገንዘብ የሚያገኝ ሰው የኃይል ሚዛኑ ወደእሱ ያጋድላል።

የኃይል ሚዛኑ ወደ ሴቶች ሲያጋድል ወንዶች እየረበሹ እና አንዳንዴም እየተፋቱ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።

በአጠቃላይ ስናየው አሁንም ወንዶች የገቢ ብልጫ አላቸው። ሴቶች ልጅ ማሳደግን ጨምሮ የቤት ውስጥ ኃላፊነት ይጣልባቸዋል።

ከፍተኛ ገቢ የሚያገኘው ሰው ሥራ ቅድሚያ ሲሰጠው ይስተዋላል። ሴቶች የትርፍ ጊዜ ሥራ የሚመርጡትም ከዚህ ጋር በተያያዘ ይመስላል።

ሴቶች አብላጫውን ገቢ እያገኙ ቤት ማስተዳደራቸው እየተለመደ መጥቷል። ባህላዊ የፆታ ሚና ላይም ለውጥ እየታየ ነው።

ሆኖም ግን ሴቶች ከፍተኛ ገቢ እያገኙም የቤት ውስጥ ኃላፊነትም ይጨመርባቸዋል።

ወንዶች ሴቶች በገቢ ሲበልጧቸው ደስተኛ ሲሆኑ አይታይም። በራስ መተማመናቸው እንደሚቀንስ ጥናት ያሳያል።

ሴቶች በገቢ ሲበልጧቸው ወንዶች ስለ ጉዳዩ ማውራትን እንደ ነውር ይቆጥሩታል።

የትዳር አጋሮቻቸውን የሥራ ሕይወት ቢደግፉም "ቤት የማስተዳደር ኃላፊነታቸውን" በአግባቡ እንዳልተወጡም ይሰማቸዋል።

ያረጁ ያፈጁ የፆታ ሚና ክፍፍሎች አሁንም በማኅበረሰቡ ውስጥ ጎልተው ይታያሉ።

በተለይ ወንዶች ሥራቸውን አጥተው ወይም በሥራ ለውጥ ምክንያት ከሥራ ሲወጡ ይሄ አመለካከት ይንፀባረቃል።

የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪው ሀሪ ቡንተን በሲድኒ፣ አውስትራሊያ ይኖራል።

መጀመሪያ ላይ ሥራውን ሲያጣ "እንደ ወንድ፣ ባል እና አባት" ያለው ዋጋ "እንደቀነሰ" እንደተሰማው ተናግሯል።

ሥራ ማጣት "ወንድነትን" የሚገዳደር ተደርጎ እንደሚወሰድ ገልጾ "ይሄ አመለካከት ግን ትክክል አይደለም። ዋጋችን የሚለካው በሥራ እና መሰል ነገሮች አይደለም። ጥሩ አባት መሆን የበለጠ ኃይል ይሰጣል" ይላል።

በቅርቡ በስዊድን የተሠራ ጥናት የ10 ዓመት የጥንዶች ገቢን ከግምት ያስገባል።

ሚስቶች ከባሎቻቸው የበለጠ ገቢ ማግኘት ከጀመሩ በኋላ የባሎች የአእምሮ ጤና ላይ ቀውስ መከሰቱን ጥናቱ ይጠቁማል።

ከጥናቱ ተሳታፊዎች መካከል የትዳር አጋራቸው በደመወዝ የሚበልጣቸው ሰዎች የአእምሮ ጤና መታወክ ዕድል በስምንት በመቶ ጨምሮ ተገኝቷል።

ደሚድ ጌቲክ በዱርሀም ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው።

በዚህ ዘመን ወንዶች ገቢያቸው የበለጠ ይሁን ብሎ ማሰብ እንደ ድሮው ባይሆንም ይህንን አመለካከት የሚያራምዱ መኖራቸው እሙን ነው።

ወንዶች በግንኙነታቸው ደስተኛ መሆን መቀንሱን በገቢ ሲበለጡ እንደሆነ ባለሙያው አስተውለዋል።

ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ሚስቶች ያሏቸው ባሎች ከሌሎች ሴቶች ጋር በጎን ግንኙነት የመጀመር ዕድላቸው እንደሚጨምር አንድ ጥናት ያሳያል።

ወንዶች የቤት አስተዳዳሪ እንዲሆኑ የሚደርስባቸው ማኅበረሰባዊ ጫና ከፍተኛ መሆኑ ለድባቴ ሲያጋልጣቸው ይታያል።

ሴቶች ማኅበራዊ ትስስራቸው ጠንካራ ስለሆነ በተሻለ ሁኔታ ስሜታቸውን ያብላላሉ።

ሴቶች የተሻለ ገቢ ሲያገኙ "ሥራ እና ኃይል ተኮር" አድርጎ የመመልከት አዝማሚያ አለ።

ሴቶች ብቻ በሚሠሩበት ቤት የሚገኘው ገንዘብ ወንዶች ብቻ ከሚሠሩበት እንደሚያንስ ጥናት ያሳያል።

ፕሮፌሰር ሔለን ኮዋልዊካ እንደሚሉት አገራት የሚሠሩ ሴቶችን ከፍተኛ ገንዘብ መክፈል ላይ ክፍተት አለባቸው።

በዩናይትድ ኪንግደም የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ወንዶች ከሥራ ወጥተው ቤት ሲውሉ ቤተሰባቸው ግንኙነት ላይ አወንታዊ ውጤት አለው።

አባቶች ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ መጨመሩ አንድ ተጠቃሽ ውጤት ነው።

ሆኖም ግን ወደ ቤት ውስጥ ሥራ ስንመጣ ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጫና በየትኛውም የገቢ መጠን ውስጥ ቢሆን ተቀራራቢ ነው።

በሌላ በኩል ሚስቶች ሲወልዱ ለአባቶች የወሊድ ፈቃድ ሲወስዱ ቤተሰብ ውስጥ የሚፈጠረው ደስታ ይጨምራል።

ከልጆቻቸው ጋር ውብ ጊዜ ከማሳለፋቸው ባሻገር የቤት ውስጥ ኃላፊትንም ይካፈላሉ።

በሜክሲኮ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው ሴቶች ብዙ የሥራ ዕድል ሲኖራቸው ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ውሳኔዎችን የማድረግ አቅማቸውም ከፍ ይላል።

ሴቶች የተሻለ ገቢ ሲኖራቸው የሚኖረውን አወንታዊ ሚና ጥናቶች ይጠቁማሉ።

በኪንግስ ኮሌጅ ለንደን የተሠራው ጥናት እንደሚያሳየው ከ18 እስከ 28 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች በጉዳዩ ላይ የተለያየ ምልከታ አላቸው።

ከመላው ዓለም መጠይቅ የተደረገላቸው 24 ሺህ ሰዎች ወንዶች ልጆችን ለመንከባከብ ቤት ከዋሉ "ያነሰ ወንድነት" አላቸው ብለው ያስባሉ።

በዚህ አስተያየት 28 በመቶ ወንዶች እና 19 በመቶ ሴቶች ተስማምተዋል።

የሥራ እና ቅጥር ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ሄዩንግ ቹንግ እንደሚሉት ሴቶች የተሻለ የትምህርት ዕድል እያገኙ መምጣታቸው የአመለካከት ለውጥ አምጥቷል።

ለምሳሌ በዩናይትድ ኪንግደም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወንድ ሐኪሞች ይልቅ የሴት ሐኪሞች ቁጥር ከፍተኛ ሆኗል።

"ፆታን መሠረት ያደረጉ ልዩነቶች እየጠበቡ እና መሻሻል እየታየ ነው" ይላሉ ባለሙያው።

የፖለቲካ መምህርት ፕሮፌሰር ሮዚ ካምቤል እንደሚሉት ወንድነት በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚታይበት መነጽር በተለይ በወጣቶች ዘንድ እየተለወጠ ነው።

ስለ ፆታ እኩልነት በትምህርት ቤቶች እና በሌሎችም ቦታዎች ውይይቶችን በግልጽ ማድረግ ፕሮፌሰር ሮዚ ይመክራሉ።

"ወንድ መሆን ምን ማለት እንደሆነ ለወጣት ወንዶች ማስረዳት አለብን። ወጣት ወንዶች አርአያም ያስፈልጋቸዋል" ይላሉ።

በበይነ መረብ ፆተኛ አመለካከቶች እየተስፋፉ ከመምጣታቸው አንጻርም ወንድነትን በጤናማ መንገድ መሳል ያለውን ሚና ያስረዳሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ወንዶች ስለ ወንድነት እና ስለ አባትነት ያላቸውን አመለካከት እየለወጡ እና የበለጠ በፍቅር እና እንክብካቤ የተሞላ ማንነትን መላበስን እያዳበሩ እንደሆነ የሚያሳዩ ውስን ጥናቶች ይጠቀሳሉ።

"ወንድ መሆን" ማለት ከፍተኛ ገቢ አምጥቶ ቤተሰብ ማስተዳደር ማለት አለመሆኑን በመረዳት ረገድም መሻሻል አለ።

የሥነ ፆታ ባለሙያ ካርላ ኤልየት እንደሚሉት ወንዶች የተለያዩ ዓይነት ሥራዎችን ለመሥራት መፍቀዳቸው አንድ የለውጡ አካል ነው።

እንክብካቤ መስጠትን የሚጠይቁ ሥራዎች ላይ ወንዶች መሰማራታቸው የበለጠ ለውጥ እያመጣ እንደሆነ ያስረዳሉ።

የአባቶች የወሊድ ፈቃድ መውሰዳቸው ያለው ሚናም አይዘነጋም።

አጠቃላይ ማኅበረሰባዊ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ጊዜ ቢወስድም ባሎች የቤት ውስጥ ኃላፊነትን ሲወጡ፣ ሴቶች ደግሞ ከፍተኛ ደመወዝ እያገኙ ቤተሰብን ማስተዳደራቸው በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እየተለመደ መምጣቱ አይካድም።