ትራምፕን "ነጩ አምባገነን" ሲሉ የተቹት ናይጄሪያዊው የኖቤል ሎሬት ዎሌ ሾይንካ ቪዛቸው ተሰረዘ

ዎሌ ሾይንካ

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እአአ በ2016 የትራምፕ መመረጥን ተከትሎ ዎሌ ሾይንካ ግሪን ካርዳቸውን ቀዳድደው ጥለዋል

ናይጄሪያዊው የኖቤል ሎሬት ዎሌ ሾይንካ አሜሪካ ቪዛቸውን መሰረዟን እና ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ መታገዳቸውን አስታወቁ።

የ91 ዓመቱ ደራሲ እና እአአ በ1986 በሥነ ጽሑፍ የኖቤል ሽልማት ያሸነፉት ዎሌ ሾይንካ የአሜሪካ ቆንስላ ግልጽ ያላደረገው አዲስ መረጃ በማግኘቱ ፓስፖርታቸውን አንዲያመጡ እና ቪዛቸው እንዲሰረዝ መጠየቃቸውን ተናግረዋል።

ሾይንካ ማክሰኞ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ከኤምባሲው የደረሳቸውን ደብዳቤ "ከኤምባሲው የተጻፈ የፍቅር ደብዳቤ" በማለት የገለፁት ሲሆን፣ ወደ አሜሪካ ሊጋብዛቸው የነበረውን ድርጅት "ጊዜያቸውን እንዳያባክኑ" መናገራቸውን አስታውቀዋል።

በናይጄሪያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ስለ ጉዳዩ ተጠይቆ በግለሰብ ጉዳይ ላይ አስተያየቱን እንደማይሰጥ ተናግሯል።

የኖቤል ሎሬቱ ዎሌ ሾይንካ እአአ በ2016 የዶናልድ ትራምፕ ፕሬዚዳንት ሆኖ መመረጥን በማስመልከት ግሪን ካርዳቸውን ቀድደው እስኪጥሉ ድረስ በአሜሪካ መኖር የሚያስችል ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ነበራቸው።

ሾይንካ ማክሰኞ ዕለት የአሜሪካ ግሪን ካርድ እንደሌላቸው ተናግረው "በመቀስ አፎች መካከል ገብቶ ብጥስጣሽ ሆኖ ወድቋል" ሲሉ ቀልደዋል።

ዝነኛው ደራሲ ላለፉት 30 ዓመታት ከተለያዩ የአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች ጋር የማስተማር ግንኙነት ነበራቸው።

ማክሰኞ ዕለት በመግለጫቸው ላይ "ቪዛ የለኝም። ታግጃለሁ" ብለዋል ።

ሾይንካ የትራምፕ አስተዳደር ባለው ፀረ ስደተኛ አቋም ላይ የከረረ ተቃውሞ የሚያሰሙ ሲሆን ለቪዛቸው መሰረዝም ይህ ምክንያት ሊሆን ይችላል ተብሏል።

በቅርቡ ትራምፕን ከኡጋንዳው አምባገነን ጋር በማነጻጸር "ኢዲ አሚን በነጭ ፊት" ያሉ ሲሆን፣ ይህ ንግግራቸውም አሁን ኤምባሲው ለወሰደው እርምጃ አስተዋጽኦ አድርጎ ሊሆን ይችላል።

"ዶናልድ ትረምፕን ኢዲ አሚን ብዬ ስጠራው እያደነቅቁት መስሎኝ ነበር" ያሉት ሾይንካ "ባህሪው እንደ አምባገነን ነው" ሲሉ አክለዋል።

ኢዲ አሚን የኡጋንዳ ወታደራዊ መኮንን የነበረ ሲሆን እአአ ከ1971 እስከ 1979 ድረስ ኡጋንዳን ያስተደደረ አምባገነን መሪ ነው።

ኢዲ አሚን በጭካኔ በተሞላው አገዛዙ እና በሰብዓዊ መብቶች ጥሰቱ ይታወቃል።

ወደ አሜሪካ ዳግም ለመሄድ ያስቡ እንደሆን የተጠየቁት ሾይንካ "ዕድሜዬ ስንት ነው?" ሲሉ መልሰው ጠይቀዋል።

በሐምሌ ወር የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለናይጄሪያውያን እና ሌሎች አፍሪካ ዜጎች ስደተኛ ላልሆኑ ዜጎች የሚሰጥ ቪዛ ፖሊሲ ላይ ለውጥ ማድረጉን አስታውቋል።

በዚህ የፖሊሲ ለውጥ መሠረት ስደተኛ እንዲሁም ዲፕሎማት ላልሆኑ የቪዛ አመልካቾች የሚሰጡ ቪዛዎች ለአንድ ጊዜ መግቢያ ብቻ የሚያገለግሉ እና የሦስት ወር ቆይታ ብቻ ያላቸው እንዲሆኑ ተደርገዋል።

ከዚህ በፊት ይህ ቪዛ ለአምስት ዓመት የሚያገለግል እና ደጋግሞ ወደ አገሪቱ መግባት የሚሰችል ነበር።