ትራምፕ ኤርትራን ጨምሮ በ12 አገራት ላይ የጉዞ ዕገዳ ጣሉ

የጉዞ ዕገዳ ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኤርትራን ጨምሮ የ12 አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይጓዙ የሚከለክለውን አዋጅ መፈረማቸውን ዋይት ሐውስ አስታወቀ።

ፕሬዚዳንቱ የጉዞ ዕገዳ የጣሉባቸው አገራት የአፍሪካ ቀንዶቹ አገራት ኤርትራ እና ሶማሊያን ጨምሮ፣ ሱዳን፣ አፍጋኒስታን፣ ኢራን፣ ቻድ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ (ብራዛቪል)፣ ሄይቲ፣ ሊቢያ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ምንያማር እና የመን ናቸው።

ፕሬዚዳንቱ "የብሔራዊ ደኅንነት አደጋን በመጋረጥ" የወነጀሏቸውን የእነዚህ አገራት ዜጎች ላይ የጣሉት የጉዞ ዕገዳ ከሰኔ 2/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።

ከእነዚህ ሙሉ የጉዞ ዕገዳ ከተጣለባቸው በተጨማሪ ሰባት አገራት ማለትም ቡሩንዲ፣ ኩባ፣ ላኦስ፣ ሴራሊዮን፣ ቶጎ፣ ቱርክሜኒስታን እና ቬንዙዌላ ከፊል የጉዞ እገዳ ተጥሎባቸዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለዚህ የጉዞ ዕገዳቸው መነሻ የሆናቸው በቅርቡ በኮላራዶ የተፈጸመን ጥቃት ዋቢ አድርገው የውጭ ዜጎች ወደ አሜሪካ በሚገቡበት ወቅት "በአግባቡ ማንነታቸው ሳይጣራ" መሆኑን ያሳየ ነው ሲሉ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ በለጠፉት ቪዲዮ ተናግረዋል።

ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ ለእስራኤል ታጋቾች ድጋፋቸውን ለመግለጽ በወጡ ሰልፈኞች ላይ ጥቃት አድርሶ በፖሊስ ተይዟል።

ጥቃቱን ፈጽሟል የተባለው ግለሰብ ግብፃዊ ዜግነት ያለው ሲሆን፤ ግብፅ ግን አሁን ፕሬዚዳንቱ በጣሉት በዚህ የጉዞ ዕገዳ ውስጥ አልተካተተችም።

ትራምፕ በተጨማሪም በጊዜያዊ (ቱሪስት) ቪዛ ወደ አገሪቱ መጥተው ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ የሚቆዩ ሰዎችንም በተመለከተ "አንፈልጋቸውም" ሲሉ ተናግረዋል።

ዋይት ሐውስ እነዚህ ገደቦች አሜሪካውያንን "ከውጭ አገራት አደገኛ አካላት" ይጠብቋቸዋል ብሏል።

ምንም እንኳን አገራቱ ሙሉ የጉዞ ዕገዳ ቢጣልባቸውም በኢራን ውስጥ በእምነታቸው እና በጎሳቸው ምክንያት ጭቆና እየደረሰባቸው ያሉ ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዲጓዙ ተፈቅዶላቸዋል።

በተጨማሪም በታላላቅ ስፖርታዊ ዝግጅቶች ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች እና ውስን የሆኑ የአፍጋኒስታን ዜጎችም ዕገዳው እንደማይመለከታቸው ተጠቅሷል።

ይህ የጉዞ ዕገዳ ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ወቅት ሰባት በአብዛኛው ሕዝባቸው ሙስሊም ከሆኑ አገራት ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ያስተላለፉት ትዕዛዝ ጋር የሚመሳሰል ሆኗል።

በአሁኑ ወቅት በጣሉት የጉዞ ዕገዳም በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት የገቡትን ቃል የፈጸሙበት ሆኗል።

በቅርቡ ተግባራዊ የሚሆነው የጉዞ ዕገዳ ሕጋዊ ተግዳሮቶች እንደሚገጥመውም ይጠበቃል።

የጉዞ ዕገዳ የተጣለባቸው አገራት ውሳኔውን ኮንነውታል። ቬንዙዌላ የትራምፕ አስተዳደርን "ዓለም በእኛ ዛቢያ ብቻ ትዞራለች ብለው የሚያስቡ እብሪተኞች" በማለት ገልጾታል።

ጎረቤት አገር ሶማሊያ በበኩሏ "የተነሱ ስጋቶችን ለመፍታት ውይይት እንደምታደርግ" ቃል ገብታለች።

ከዋይት ሐውስ የተሰማው ትልቁ ውሳኔ ይሄ ብቻ አይደለም፤ ትራምፕ በሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ ለሚማሩ የውጭ አገራት ተማሪዎች ቪዛቸውን የሚገድብ ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ ፈርመዋል።

በተጨማሪም የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የጤናቸው ማሽቆልቆልን ለመሸፈን "ሴራ" ተፈጽሟል ባሉት ላይም ማጣራት እንዲካሄድ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።